ሀ ለ ሐ መ ሠ ረ ሰ ሸ ቀ በ ተ ቸ ኀ ነ ኘ አ ከ ኸ ወ ዐ ዘ ዠ የ ደ ጀ ገ ጠ ጨ ጰ ጸ ፀ ፈ ፐ
ሠ ፤ ፲፭ኛ ፊደል በግእዝ አልፍ ቤት በአበገደ ፤ ስሙ ሠውት ፥ ቍጥሩ ስሳ ፤ አኃዝ ሲኾን (ሠ–፷) ስሳ ፤ ወይም ሥልሳ ይባላል ፤ ሠለሰንና ሰደሰን እይ። ጸሐፍት ግን ነግሠ የሚጣፍ በርሱ ስለ ኾነ ስሙን ንጉሥ ይሉታል። በዐረብና በዕብራይስጥ አንዱ ኅርመት ፊደል ሠ በነቍጣ ምክንያት ሲን ሺን እንዲባል ፥ በጥንታዊም ግእዝ ሰና ሸ የሚባል ይህ ሠውቱ ሠ እንጂ ሳቱ ሰ አይዶለም። ሳቱ ሰ ግን እንደ ሳምኬት ሰ በስምና በመልክ ተለይቶ ተራውና ቍጥሩ ሳይፋለስ ስሳነቱን ሳይለቅ ሰ ብቻ ኹኖ ሰ ከመባል በቀር እንደ ሠውት ሠ ሸ መባል የለውም ፤ አልነበረውም። ፪ ዐይነት ሠ ሰ በግእዝ በሱርስት በዕብራይስጥ እንጂ በዐረብ የለም ፤ ጻዴ ግን ሳድ እየተባለ እንደ ሰ ይጠራል ፤ለሠና ለጸ ከመልክ በቀር የድምጥ ልዩነት የላቸውም። ሸ ደግሞ በቅበጥ እንጂ በጽርእ አይገኝም ፤ ከግእዝም ጽርኣዊው ሰላማ መጻሕፍትን ከጽርእ ወደ ግእዝ ሲመልስ ያን ጊዜ አውጥቶት ከዚያ ወዲህ በግእዝ ቃላት ውስጥ መጣፉና መነገሩ ቀርቷል። ይኸውም ሊታወቅ ዕብራይስጥና ዐረብ ሱርስትም ሸ የሚሉትን ፥ ይልቁንም ዐረብ በሺን የሚጥፈውን ፤ ዲልማን ለይቶ በሠውት ጥፎታል። (ዐረብ) ሻበ ሸሐጸ ሸረበ ሸረዐ ሸረጸ ሸረቀ ነገሸ። ሤበ ሥሕጸ ሠረበ ሠርዐ ሠረጸ ሠረቀ ነግሠ። የሳቱ ሰን ፍች እይ።
ሠሀለ ፡-ሳለ አሰላ፤–ስሒል ሰሐለ።
ሠሐለ [1]፡-ራራ ይቅር አለ፤–ሥሂል ሠሀለ።
[2]፡-ሳለ ሰነገለ፤–ስሒል ሰሐለ።
ሠሀቀ ፡-ሣቀ፤–ሥሒቅ ሠሐቀ።
ሠሓቂ ሥሑቅ ፡-(ቃን ቃት ሕቅት) የሚሥቅ ሣቂ፤ የሣቀ ሣቃም።
ሠሐቅ ፡-(አው ሣሕቅ፤ ሥሓቅ ሥሐቅ) በቁሙ፤ ሣቅ ፥ ሥቆሽ፤ አሣሣቅ። መሪር ሠሐቅየ ዘእሥሕቅ። ወለሠሐቅክሙ ሚጥዎ ውስተ ላሕ። እምሑረቱ ወእምሠሐቁ ይትዐወቅ ግዕዙ ፡-(ኤር፳ ፡-፰። ያዕ፬ ፡-፱። ሢራ፲፱ ፡-፴)።
ሠሀተ ፡-ዐረፈ ዕረፍት አገኘ፤–ሥኂት ሠኀተ።
ሠኃቲ ሥኁት ፡-(ታን ታት ኅት) የሠከተ፤ ያረፈ ዐራፊ፤ ዕረፍት ያገኘ፤ ዝም ዕክም ያለ ጸጥተኛ ፡-(ማቴ፲፩ ፡-፳፪)።
ሠሀነ ፤–ሞቀ ፤–ስሒን ሰኀነ።
ሠሐነ ፡-ሞቀ ተኰሰ፤–ስኂን ሰኀነ።
ሠሐገ ፡-ጮኸ አሞሸ ሳገ፤–ስሒግ ሰሐገ።
ሠሐጠ ፡-ነካ ጫረ፤ ቈነጠጠ፤–ስሒጥ ሰሐጠ።
ሠሓጺ ሥሑጽ ፡-(ጻን ጻት ሕጽት) ደፋር ፥ ዕቡይ፤ አላጋጭ አሽሟጣጭ ተሳዳቢ ፡-(ሆሴ፯ ፡-፭። ሮሜ፩ ፡-፴። ፪ጢሞ ፡-፫ ፡-፫)። መኰንን ሥሑጽ። ዕልዋን ወጽልሕዋን ወሥሑጻን። ልሳን ሥሕጽት ፡-(ስንክ ፡-ሠኔ፲፬። ቀሌ። ቄር)።
ሠለለ ፡-በቁሙ፤–ሰሊል ሰለ፤ ሰለለ።
ሠለመ ፡-በቁሙ፤–ሰላምታ ሰጠ፤–ሰሊም ሰለመ።
ሠለሠ ፡-ሦስት አደረገ፤–ሠልሶ ሠለሰ።
ሠለስ(ት) ቱ ፡-ሦስት፤ ሦስቱ ፥ ሦስተኛው። ሠለስቱ አቅርንት። በእሉ ሠለስቱ። እንዘ አሐዱ ሠለስቱ ፡-(ዳን፯ ፡-፰። ሢራ፳፮ ፡-፳፰። ሃይ ፡-አበ)።
ሠለቀ [1]፡-(ዕብ ቃሌስ) ዘበተ አፌዘ አላገጠ፤ በነገር መታ ሠለቀ፤ ተሣለቀ። ምስጢሩ እንደ ጤፍ ዶቄት ልዝብነትና ለስላስነት ነው፤ ሣቅና ጨዎት ስላለበት።
[2]፡-(ዕብ ሳሌቅ) ላጠ መለጠ ሸለቀቀ፤ ገፈፈ አነሣ አራቀ። ሸልቋቋ ሸለቆ ማለት ከዚህ የወጣ ነው።
ሠለበ ፡-ገፈፈ፤–ሰሊብ ሰለበ።
ሠለጠ ፡-ፈጸመ ጨረሰ፤–ሰልጦ ሰለጠ።
ሠለፈ ፡-በቁሙ፤–ሰሊፍ ሰለፈ።
ሠሉስ ፡-የዕለት ስምና ቅጽል፤ ማግሰኞ ማግስተ ሰኞ፤ የሰኞ ማግስት የእሑድ ሣልስት፤ በሰኞና በረቡ መካከል ያለው ዕለት። ቅጽልም ሲኾን ሦስት ሦስተኛ ያሰኛል። ምሕዋረ ሠሉስ ዕለት እስከ ሠሉስ መዋዕል። በሠሉስ ዕለት ኣነሥኦ። ሠሉስየ ዮም ፡-(ዮዲ፪ ፡-፳፩። አስቴ፬ ፡-፲፮። ዮሐ፪ ፡-፲፱። ፩ነገ ፡-፴ ፡-፲፫)። ሲበዛም ሠሉሳት ያሰኛል።
ሠሊቅ ቆት ፡-(ሠለቀ ይሠልቅ ይሥልቅ) መሠለቅ፤ ማላም ማድቀቅ።
ሠሊክ ፡-ሽቱ፤–ሰሊኅ ኆት።
ሠሊጥ ጦት ፡-(ሠለጠ ይሠልጥ ይሠልጥ። ዕብ ሻላጥ። ሱር ሽላጥ። ዐረ ሠሊጠ) የጠፈረ ሰርዌ። መሠልጠን፤ ጌታ መኾን፤ ማየል መበርታት፤ ኀይል ክሂል፤ መብት ማግኘት፤ እንደ ወደዱ ለማድረግ። ዐበይቶሙ ይሠልጡ ላዕሌሆሙ። ወአልቦ ዘእሬሲ ይሠለጥ በላዕሌየ መኑሂ ፡-(ማቴ፳ ፡-፳፭። ፩ቆሮ ፡-፮ ፡-፲፪) በሠለጠ ፈንታ ተሠልጠ ተሠለጠ ተሠልጠነ ይላል፤ ስሕተት ነው። አግብርት ተሠልጡ ላዕሌነ። ወሶበ ርእዩ ከመ ዛቲ ኀጢአት ተሠልጠት ላዕለ ብዙኃን። ዘይሤለጥ በመንፈሱ። ለዘይሤለጥ ላዕሌከ። ተሠለጥከ በሥጋከ ፡-(ሰቈ፭ ፡-፰። ፈ ፡-መ ፡-፲፫። ምሳ፲፮ ፡-፴፪። መክ፰ ፡-፬። ሢራ፵፯ ፡-፲፱)።
ሠላሲ ፡-(ሲት ስያን ያት) የሠለሰ የሚሠልስ፤ ሠላሽ ሦስት አድራጊ።
ሠላሳ ፡-(ዕብ ሽሎሽም) በቁሙ፤ የአኃዝና የቍጥር ስም ፡-(ለ–፴) ፫ ጊዜ ዐሥር ወይም ፲ ጊዜ ሦስት። መዋዕለ ላሕ ለሙት የሚለቀስበት። ፡-(ተረት) በሠላሳ እግርኽን አታንሣ፤ ባርባበረኽ ግባ። እየዐርግ እምሠላሳ ፥ ወኢይወርድ እምሠላሳ፤ ወትረ ይከውን ሠላሳ ፡-(መር ፡-ዕዉ)።
ሠላስ ፡-የቍጥር ስም ሦስት፤ በኹለትና ባራት መካከል ያለ ቍጥር፤ ፫ ጊዜ አንድ። ወንድና ሴት ያስተባብራል፤ መደቡ ግን የሴት ብቻ ነው። ሠላስ አኃቲሆሙ ምስሌሆሙ። ወሀሎ ህየ ሠላስ መራዕየ አባግዕ። ሠላስ መዋዕል። በእንተ ሠላስ ኀጢአቶሙ። ሠላስ አርዳኢሁ ፡-(ኢዮ፩ ፡-፬። ዘፍ፳፱ ፡-፪። ፵ ፡-፲፪። ዓሞ፩ ፡-፫። ስንክ ፡-ጥቅ፳፩)።
ሠላጢ መሠልጥ ሥሉጥ ፡-(ጣን ጣት ልጥ) በቁሙ፤ የሠለጠነ፤ ሥልጡን ፥ ሠልጣና፤ ሥልጣኔ ያለው ሥልጣን የተሰጠጥው። ሥሉጥ ውእቱ በዘፈቀደ። ንጉሥ ሥሉጥ። ርእዩ ከመ ኵሉ ሥሉጥ ይሕየውሂ ወይእመንሂ። አንትሙ ሥሉጣን ላዕለ ኵሉ አሕዛብ ፡-(ዮዲ፰ ፡-፲፭። መክ፰ ፡-፬። ኪዳ። ዲድ ፡-፯። ራእ፲፩ ፡-፮)።
ሠሌዳ ፡-በቁሙ፤–ሰለደ።
ሠልሶ ሶት ፡-(ሠለሰ ይሤልስ ይሠልስ። ዕብ ሻሌሽ) መሠለስ፤ ሦስት ማድረግ ከሦስት መክፈል ሦስት ማለት። ይቤሎሙ ሠልሱ ወሠልሱ። ንሤልስ ለከ ዘንተ ስብሐተ። ለዋሕድ አምላክ እንዘ በአካል ይሤልሶ ፡-(፫ነገ ፡-፲፰ ፡-፴፬። ኪዳ። ስንክ ፡-ግን፳፯)።
ሠመርመር ፡-መወደድ ያለው ንስር ቀይና ጥቍር ያንበጣ ፀር። ዖፍ ዘይሰመይ ሠመርመር ዘባኑ ጸሊም፤ ከርሡ ወእገሪሁ ቀይሕ . . . ወሶበ ይመጽእ አንበጣ ውስተ ሀገረ ዐዘም ይመጽኡ እሙንቱ አዕዋፍ ሠመርመር ወይቀትልዎሙ ለእሙንቱ አናብጥ ወያሀጕልዎሙ ፡-(ጊ ፡-ወ ፡-ሐ ፡-ገ፳፩)።
ሠመነ ፡-ስምንት አደረገ፤–ሰምኖ ሰመነ።
ሠመከ ፡-ተጠጋ፤–ሰሚክ ሰመከ።
ሠሚር ሮት ፡-(ሠምረ ይሠምር ይሥመር። ዕብ ሻማር፤ጠበቀ) መሥመር፤ መውደድ ቍርጥ ፈቃድ ማድረግ፤ እሺ በጎ ይኹን ሠመርኩ ማለት፤ ልመናን ነገርን ወዶ መቀበል። እመ ሠምረ እግዚ። ሥመር እግዚኦ ከመ ታድኅነኒ። ዘትጸልእ ለርእስከ ጽላእ ለካልእከ፤ ወሥመር ለሰብእ ዘትሠምሮ ለርእስከ። ነዋ ሠምረ በዝንቱ እምድኅረ ሰአልዎ ሎቱ። መሥዋዕተ አቤል ዘሠምረ ፡-(ያዕ፬ ፡-፲፭። መዝ ፡-፴፱። ፈላስ። ፍ ፡-ነ ፡-፬። ድጓ)።
ሠማሪ ፡-(ሪት ርያን ያት) የሚሠምር፤ የሚወድ ወዳጅ። ንሕነ ኵልነ መዋትያን ዘጸላኢኒ እምኔነ ወሠማሪ ፡-(ግንዘ)።
ሠምረ ፡-አፈራ በጀ፤–ሰሚር ሰምረ።
ሠምዐ [1]:-ሰማ መሰከረ፤–ሰሚዕ ሰምዐ።
[2]፡-ሠም ኾነ ጦፈ፤ ቀለጠ ነጠረ። ረጋ ጸና ተጋገረ።
ሠምዕ ፡-(ዓት። ዐረ ሸመዕ) ሠም፤ ጧፍ የጧር ሰፈፍ፤ ንጥሩ ግግሩ፤ ልጥልጡ ነጋሪቱ፤ ፋናው መብራቱ። ለእመ ሰረቀ ምንተኒ እምንዋየ ቤተ ክርስቲያን፤ አው ሠምዕ አው ዘይት። ነደ ከመ ሠምዕ። መኃትው ብሩሃት ወሠምዓት ንጹሓት ፡-(ፈ ፡-መ ፡-፲፯ ፡-፮። ግንዘ። አፈ ፡-ተ፬)።
ሠሥዖ ዖት ፡-(ሠሥዐ ይሜሥዕ ይሠሥዕ። ዐረ ሸሠዐ) መሣሣት፤ መራራቅ፤ ዘር ዘር ማለት፤ የቡቃያ የዘር፤ ያታክልት የጠጕር።
፡-መሣሣት መርቀቅ፤ ሥሥ ረቂቅ መኾን ፡-(ዐማርኛ)።
፡-መሠሠት መንፈግ፤ ሆዳም ሥሥታም መኾን። ኢትሠሥዕ ለኵሉ መብልዕ። ካህናት ዘሠሥዐት ነፍሶሙ በረኀብ ርኩስ። ይሤሥዑ ለበሊዕ ፡-(ሢራ፴፯ ፡-፳፱። ቀኖ ፡-ኒቅ። ዲድ ፡-፯። ፪ተሰ ፡-፫ ፡-፯)።
ሠረረ ፡-በረረ መጠቀ፤–ሰሪር ሰረረ)
ሠረቀ ፡-(ዐረ ሸረከ) አሰረ ቋጠረ፤ አዋሰበ ጐነጐነ። ሠረከን ተመልከት።
ሠረቃዊ ፡-(ዕብ ጼማሕ) ሠርጽ፤ ቡቃያ ለጋ ወጣት፤ ገና የሚያድግ። ገብርየ ሠረቃዊ። ናሁ ብእሲ ሠረቃዊ ስሙ፤ ወይሠርቅ ፡-(ዘካ፫ ፡-፰ ፡-፮ ፡-፲፪)።
ሠረበ ፡-ፈሰሰ ጐረፈ፤–ሰሪብ ሰረበ።
ሠረከ ፡-(ዐረ ሸረክ) አዋሰበ፤ ጐነጐነ፤ አሰረ፤ ዐዘበ፤ የቶታን የጫማ፤ የወጥመድ። አሠመረ፤ አስነበረ፤ የሢር የብራና። ኹለተኛውን ሠረቀን ተመልከት፤ ከዚህ ጋራ ፩ ነው፤ ከ ለቀ ተለውጦ ወደዚያ ኺዷል።
ሠረዝ [1]፡-ዐጥር፤ የስሕተት ምልክት፤ ከማንበብና ከመነበብ የሚከለክል።
[2]፡-የቅኔ መንገድ ስም፤ ኹለት አርእስት ያለው፤ ንባቡም ምስጢሩም በዋዌ እየተጫፈረ የሚኼድ። እምከዊነ ካህን ይኄይስ ከዊነ ኖላዊ፤ ወጎለ እንስሳ ትትበደር እምቤተ መቅደስ ዐባይ፤ እስመ ቤተ መቅደስ ኮነት ቤተ ፈያታይ፤ ወበላዕለ ኖሎት ኢሀለ ላዕለ ካህናት ዘሀሎ እከይ፤ ይህን የመሰለ። ይህ ነጠላ ነው፤ ድርብ ሲኾን አርእስቱ ሦስት ይኾናል። አስተብፅዑ ነፍስተ ዓሣ ኢየሱስ ወጴጥሮስ ወሩፋኤል፤ ባሕረ ጥብርያዶስ አኮኑ አመ ኢየሱስ ወፈረ በኅዳጥ ዓሣ አጽገበ ማኅበረ፤ ወእምከርሠ ዓሣ አውፅአ ጸባሕተ ቄሳር ዲናረ ፥ መሠግር ጴጥሮስ አመ አሥገረ፤ ሩፋኤልኒ ሥራየ በዘአእመረ ፥ በዓሣሁ አሕየወ ዕዉረ።
[3]፡-ማእከላዊ ነቍጥ ኹለት ዐይነት ያለው ነጠላና ድርብ፤ የቃል መክፈያ፤ የምስጢር መለያ፤ ከ(።) ነጥብ የሚያንስ የነጥብ እኩሌታ ከ( ፡-) ነቍጥ የሚበልጥ፤ ኹለተኛና ሦስተኛ የጥፈት ምልክት። ነጠላ ሠረዝ ፣ ወይም ፥። ድርብ ሠረዝ፤። ሲመች እንደ አኃዝ ቀይ ይጨመራል፤ ሳይመች ይቀራል። ነጠላ ሠ ልዩ ልዩነት ባለው በማይጫፈር ቃል በስም ይገባል። ቦ ዘምእት ፥ ወቦ ዘስሳ ፥ ወቦ ዘሠላሳ። ወናሁ እነግረክሙ ዘትብሉ በበይናቲክሙ ፥ አነ ዘጳውሎስ ፥ ወአነ ዘአጵሎስ ፥ ወአነ ዘኬፋ ፥ ወአነ ዘክርስቶስ። ድርብ ሠ ባስረጅና በተመሳሳይ ቃልይ ይገባል። ንበር ማእከሌነ፤ እስመ ኪያከ አልሀቀ እግዚ። እስመ ከመ ዝ ይቤ መጽሐፍ፤ አነ ኣሀጕል ጥበቢሆሙ ለጠቢባን፤ ወእሜንን ምክሮሙ ለመካርያን። መኑ እንከ ጠቢብ፤ ወመኑ እንከ ጸሓፊ፤ ወመኑ ዘየኀሥሦ ለዝ ዓለም፤ አኮኑ አእበዳ እግዚ ለጥበበ ዝ ዓለም።
(ላ) ሠረየ ፡-ሠየ፤ ፈተለ፤ አቀጠነ፤ አሾረ፤ አንሻረረ እንዝርቱን።
ሠረገ ፡-በቁሙ፤ ወደ ውስጥ ገባ፤ ተሥረገረገ ፡-(ዐማርኛ)።
ሠረገላ ፡-(ላት) [1]፡-ጋድም፤ የቤት የቤተ ክሲያን ዖፉ ፥ ወይም ምሰሶው ዋልታ ገበታ ተሸክሞ የሚቆምበት ተጋዳሚ መሥመራዊ ዕንጨት። ወገብረ ዐበይተ ማኅፈዳተ እምዕፀ፤ ወታሕቴሁ ሠረገላ ፡-(ዮሴፍ)።
[2]፡-የመንኰራኵር ዘንግ፤ ተጋዳሚው ፥ ተሸካሚው ብረት፤ መንኰራኵሩ እንደ እንዝርት ራስ በኹለት ወገን የሚሰካበት፤ የሚዋደድበት። ከርሱ ጋድምነት የተነሣ ላዩም ታቹም፤ መላው ኹለንተናው፤ ፈረሶች የሚስቡት ኹሉ ሠረገላ ይባላል። ፪ኛም የኼደበት መንገድ፤ መሥመር መምሰሉ የስሙን ምስጢር ያስረዳል። ሠረገላ ሠናይ። በብዙኅ ሠረገላየ። ሰብአ ሠረገላት። በሠረገላ ይረውጹ ፡-(ኢሳ፳፪ ፡-፲፰። ፴፬ ፡-፳፬። ዮዲ፯ ፡-፳። ድጓ)። በመንኰራኵርም ፈንታ ሠረገላ ይላል። ቃለ ነጐድጓድከ በሠረገላት ፡-(መዝ ፡-፸፮)።
ሠረገላዊ ፡-ባለሠረገላ፤ ነጂ፤ ተቀማጭ። ሠረገላዊ ዘእንበለ ድርዐ ኀጺን፤ ፈረሳዊ ዘእንበለ ኵያንው ፡-(መጽ ፡-ምስ)።
ሠሪም ሞት ፡-(ሠረመ ይሠርም ይሥርም) ማረግረግ፤ መቅለጥ፤ መሳብ መዋጥ፤ ማስጠም ማስመጥ፤ የመሬት የውሃ።
ሠሪቅ ቆት ፡-(ሠረቀ ይሠርቅ ይሥርቅ። ዐረ ሸረቀ። ዕብ ዛራሕ። ሱር ድናሕ) መነሣት፤ መውጣት፤ ብቅ ማለት፤ መብቀል መወለድ፤ መብራት መታየት መገለጥ፤ የፀሓይ የጨረቃ። እምከመ ሠረቀ ፀሓይ የአትዉ። ብርሃን ዐቢይ ሠረቀ ላዕሌሆሙ። እገብር ሐዲሰ ዘይእዜ ይሠርቅ። ሠረቀ በሥጋ። ትሬእዮሙ እንዘ ይሠርቁ ፡-(መዝ ፡-፻፫። ኢሳ፱ ፡-፪። ፵፫ ፡-፲፱። ኤፍ። አረጋ ፡-ድ፩)።
፡-መባት፤ መግባት፤ መዠመር፤ የወር ያመት። ታኅሣሥ ለእመ ሠረቀ በሠሉስ። በክልኤቱ ዓመተ መንግሥቱ ሠረቀ መስከረም በዕለተ ሰኑይ ፡-(ሥር ፡-ድጓ። ታሪ ፡-ነገ)።
ሠሪብ ቦት ፡-(ሠረበ ይሠርብ ይሥርብ። ዐረ ሸረበ) መማግ፤ መጠጣት፤ መሳብ መምጠጥ። ይሠርብ ደምየ። ይሠርባ ለኀጢአት ከመ ስታይ። ወሠሪቦ ብሒአ ፡-(ኢዮ፮ ፡-፬። ፲፭ ፡-፲፮። ዮሐ፲፬ ፡-፴)።
ሠሪዕ ዖት ፡-(ሠርዐ ይሠርዕ ይሥራዕ። ዐረ ሸረዐ። ዕብ ሣራዕ) መሥራት፤ ማድረግ፤ ማበጀት፤ ማዘጋጀት፤ መምረጥ፤ ማቅረብ፤ መዘርጋት፤ መሰደር መደርደር፤ የሥራ የማእድ የወጥመድ፤ የሕዝብ የሰራዊት። ሥርዑ ማእደ። ዘሠርዐ መሥገርተ። ብዙኀ ሠርዑ ውስቴቱ። ይሠርዖሙ ለአሕዛብ። ሠርዑ ሰራዊቶ። ኪያሆሙ ሠርዐ ፡-(ዘፀ፳፮ ፡-፴፭። ሢራ፳፯ ፡-፳፮። ፴፬ ፡-፲፪። ኢዮ፲፪ ፡-፳፫። ዮሴፍ። ሮሜ፰ ፡-፳፱)። ዘርዐንና መዝርዕን ተመልከት፤ ዘ በሠ ተለውጧል።
፡-ማዘዝ፤ መወሰን፤ መጣፍ፤ ማኖር፤ የሕግ የሥርዐት። ስንክሳር ዘሠርዑ አበዊነ። ያሬድ ሠርዐ ማሕሌተ ለለ ዘመኑ። ሠራዕኩ ኆጻ ወሰነ ለባሕር፤ አንበርኩ ረሰይኩ ብሂል ፡-(ስንክ ፡-መጋ፩። ግን፲፩)።
(ላ) ሠሪው ዎት ፡-(ሠረወ ይሠሩ ይሥሩ) አው ሠርዎ፤ ዎት፤ ፡-(ሠረወ ይሤሩ ይሠሩ። ዕብ ሻሬሽ) መንቀል፤ ከሥር ማፍለስ፤ ጨርሶ ማጥፋት፤ መደምሰስ። ትሥሩ ወትትክል። ይሤሩ መሠረተ። ንዑ ንሥርዎሙ እምአሕዛብ ፡-(ኤር፩ ፡-፲። ሢራ፫ ፡-፲። መዝ ፡-፹፪)።
፡-ሥር መስደድ፤ ሥር መያዝ፤ ሥራም መኾን፤ መጽደቅ፤ ካፈር ከመሬት መሰማማት፤ የዛፍ የተክል የቡቃያ።
ሠሪዝ ዞት ፡-(ሠረዘ ይሠርዝ ይሥርዝ) መሠረዝ፤ ማጠር፤ የተጣፈን ቃል ስሕተት ስለ ኾነ ቀለም ማልበስ፤ ወይም በላዩ እንደ መሥመር ማሳለፍ፤ ማጋደም።
ሠሪጽ ፡-መሥረጽ፤ አሥራጺውን አኽሎ፤ በባሕርይ በመልክ መስሎ ተካክሎ፤ ከአሥራጺው አካል መውጣት ፥ መገኘት፤ ያው ግን ተድኅሮ ተመትሮ፤ የባሕርይ ተከፍሎ ሳይኖር። ወወሰኩ ላዕለ ሃይማኖት ዘሠርዑ ሠለስቱ ምእት ዐሠርቱ ወሰመንቱ ፡-(፫፻ ፡-፲ወ፰) ወይቤሉ ወነአምን በበመንፈስ ቅዱስ ዘሠረጸ እምአብ እስከ ተፍጻሜታ። ወእሎንቱ አበው ምእት ወኀምሳ አውገዙ ኵሎ ዘይዌስክ እምድኅረ ዝ ላዕለ ሃይማኖት ፥ አው ያሐጽጽ እምኔሃ። ወነአምን በመንፈስ ቅዱስ ዘሠረጸ እምአብ። ከመ መንፈስ ቅዱስ ሠረጸ እምአብ፤ ወነሥአ እምወልድ። ወሞገስ ኢይሠርጽ ዘእንበለ እምኀበ ምግባራት ሠናያት ፡-(ጊ ፡-ወ ፡-ሐ ፡-ገ፻፸፱። ጸሎ ፡-ሃይ። ያዕ ፡-ዘእል። ማር ፡-ይሥ፳ ፡-፭)። በሠረጸ ፈንታ ወፅአ ይላል፤ ፍችው ፩ ነው። ወመንፈስ ቅዱስ ይዜኑ ዘከመ ወፀአ እምአብ፤ ወዘከመ ነሥአ እምወልድ ፡-(ቅዳ ፡-ግሩ)።
ሠሪጽ ጾት ፡-(ሠረጸ ይሠርጽ ይሥርጽ። ዕብ ሻራጽ) መፍላት፤ መውጣት፤ መብቀል፤ ሥር መስደድ፤ መለምለም፤ ማፈጥፈጥ፤ የተሐዋስያን የአዝርዕት የአትክልት። ለታውፅእ ባሕር ባለው፤ ዕብራይስጡ ይሽርጹ ሀማዪም እንዲል ፡-(ዘፍ፩ ፡-፳)። ውእተ ጊዜ ሠረጸ፤ እስመ አልቦ ዕመቅ ለመሬቱ። ይሠርጽ ሥርዎሙ። ዕፀው ሠረጹ። በትር ትሠርጽ። እምሥርወ እሴይ ሠሪጻ ፡-(ማቴ፲፫ ፡-፭። መዝ ፡-፹፬። ኢሳ፴፯ ፡-፴፩። ሉቃ፳፩ ፡-፴። ዘኍ፲፯ ፡-፳። ድጓ)።
ሠራብ ፡-(ዐረ ሸራብ) ዝኒ ከማሁ። እመ አዕረገ ህየንተ አሥራበ ወይን፤ ሠራበ ሦከር ፡-(አብጥ ፡-፫)።
ሠራዒ ፡-(ዒት ዕያን ያት) የሚሠራ፤ የሚያዝ፤ የሚጥፍ፤ የሚወስን። እግዚ ሠራዒሃ ለሰንበት። ሠራዒ ጳውሎስ። ሠራዕያነ ሕጋቲሃ ለቤተ ክር ፡-(ቀሌ። ቂር። ቅዳ ፡-ግሩ)።
(ላጥ) ሠራዊ ፡-(ዊት ውያን ያት) የሚነቅል፤ የሚያጠፋ፤ ነቃይ አጥፊ።
ሠራዪ ፡-(ዪት ይያን ያት) ሥራይ የሚያደርግ፤ ሥራየኛ፤ አስማታም፤ መድኀኒታም
ሠራጺ ፡-(ጺት ጽያን ያት) የሚሠርጽ፤ የሚወጣ፤ ወጪ። መንፈስ ቅዱስ ሠራጺ፤ ወኢአሥራጺ። ከዊነ ሠራጺ ለመንፈስ ቅዱስ ባሕቲቱ ፡-(አትና። ያዕ ፡-ዘእል)። መሥረጽ ግብሩ፤ ሠራጺ አካሉ፤ ሠራጺነት ፥ ከዊነ ሠራጺ የአካሉ ባሕርይ፤ ወይም ህላዌ ይባላል፤ የህላዌን ፍች ተመልከት። እነትና ከዊን አንድ ወገን ነው።
ሠር ፡-ቁመት፤–ሰሪር ሰረረ።
(ጥ) ሠርሖ ሖት ፡-(ሠርሐ ይሤርሕ ይሠርሕ። ዐረ ሸረሐ፤ ከሠተ) ማበጀት፤ ማሳመር፤ ማቅናት፤ ማስላት ማሳካት፤ ማከናወን፤ ማሰናበት። ሠርሐ ምግባሮሙ በእደ ነቢዩ። ይሤርሕ እግዚ ፍናዊሁ። ይሤርሐከ በኵሉ ግብርከ። ዘእንበለ ይትፈጸም ዕርገተ ቍርባን ወበረከተ ካህን፤ ወሠርሖት። እምቅድመ ሠርሖቱ ፡-(ጥበ፲፩ ፡-፩። ኩፋ ፡-፳፯። ጦቢ፬ ፡-፲፱። ፍ ፡-ነ ፡-፲፪ና ፡-፲፫። ዘኍ፮ ፡-፳፫–፳፯)። በሠርሖት፤ ፈንታ ሥርሐት ይላል፤ ስሕተት ነው። ንቀድም በረድኤተ እግዚ ወበሥነ ሥርሐቱ ፡-(ያዕ ፡-ዘእል)።
ሠርም ፡-(ዐረ ሸርም) ረግረግ፤ ማጥ፤ የሚያጠልቅ የሚያሰምጥ፤ ያዛባ የጭቃ ጕድጓድ ዐዘቅት። ለእለ ውስተ ሠርም ይትመነደቡ መድኅን። ዕመቀ ሠርመ ኀጢኣት። ረዳኢ ለእለ ውስተ ሠርም ፡-(ኪዳ። ቀሌ። ድጓ)።
ሠርቃዊ [1]፡-የጨረቃ ወር። ወርኅ ሠርቃዊ ፡-(አቡሻ ፡-፴፫)።
[2]፡-(ዕብ ቄዴም) ምሥራቅ፤ ምሥራቃዊ። ደብር ሠርቃዊ ፡-(ዘፍ፲ ፡-፴)።
ሠርቅ [1]፡-መውጫ፤ መገለጫ፤ ምሥራቅ። መንገለ ሠርቀ ፀሓይ። ደብረ ዘይት ዘሀለወት በሠርቀ ኢየሩሳሌም። በከመ ይርሕቅ ሠርቅ እምዐረብ ፡-(ዘፍ፳፭ ፡-፮። ዮሴፍ። መዝ ፡-፻፪)።
[2]፡-መባቻ፤ የወር መዠመሪያ፤ ልደተ ወርኅ፤ መብቀያዋ መወለጃዋ፤ ወር፤ ቀን። ጌሠም ሠርቀ ወርኅ። ሠርቀ ወርኅክሙ። ዕለተ ሠርቅ። አመ ርእሰ ሠርቅ። በኀሙስ ሠርቅ። በዐሡር ሠርቅ ፡-(፩ነገ ፡-፳፭ ፡-፭። ኢሳ፩ ፡-፲፬። መዝ ፡-፹። ዘፀ፵ ፡-፪። ሕዝ፩ ፡-፩። ኤር፶ ፡-፬)።
ሠርብ ፡-መጠጥ፤ የተበጀ የተዘጋጀ። መጽሐፍ ግን በሠርብ ፈንታ አሥራብ ይላል፤ ያንዱን በብዙ። አሥራበ ወይን አሥራበ ሶከር ፡-(አብጥ ፡-፫። አርጋ ፡-፩)።
ሠርክ ፡-(ዐረ ሽሪክ ሽርክ፤ ሱቱፍ) በቁሙ፤ ማታ ምሽት፤ ካ፲፩ ሰዓት እስከ ቀዳማይ ሰዓተ ሌሊት፤ የመዓልት ጫፍ መጨረሻ መሰናበቻ፤ የሌሊት መባቻ፤ ሱቱፈ ጽልመት። ዐርብን ተመልከት። መሥዋዕተ ሠርክ። እምነግህ እስከ ሠርክ። ፍና ሠርከ። በበ ሠርክ። ሠርከ ሠርከ ትበልዕ። ሠርከ ሠርከ ይዴረሩ ፡-(መዝ ፡-፻፵። ዮዲ፪ ፡-፯። ዘሌ፮ ፡-፲፫። ፪ዜና ፡-፲፫ ፡-፲፩። ዮዲ፲፪ ፡-፱። ሱቱ ፡-ዕዝ፲፬ ፡-፵፯)።
ሠርዌ [1]፡-(ራዊት። ሱር ሣሪታ) ጕንድ ከሥር የሚወጣ፤ ዐምድ ምሰሶ፤ ወጋግራ፤ የቤት ዕንጨት፤ የድልድይ ጋድም፤ መሸጋገሪያ የመርከ ምሰሶ፤ ደንቀል። ንግዝም ሠርዌ። ወናሁ ሠርዌ። ታሕተ ሠርዌ ቤትከ። ዕፀው ለጠፈረ ቤት ወለሠራዊት። ሠርዌ ተንከተም። ሠርዌ ሐመር ፡-(፬ነገ ፡-፮ ፡-፪። ማቴ፯ ፡-፬። ሢራ፳፱ ፡-፳፱። ፪ዜና ፡-፳፬ ፡-፲፩። ፪ነገ ፡-፳፫ ፡-፳፩። አርጋ)።
[2]፡-ጥራጊ፤ ጕድፍ፤ ጭራሮ። ከመ ሠርዌ ይውዕዩ ፡-(ተረ ፡-ኤር)።
[3]፡-ሉሕ፤ ጠርብ፤ ዝርግ ጠፍጣፋ ዕንጨት፤ ሳንቃ። መስመክተ ሠርዌሁ። ሠራዊተ ዐጸድ ፡-(ዘፀ፳፮ ፡-፲፯። ፴፱ ፡-፳)።
፡-የሸማኔ ዕቃ፤ መጠቅለያው። ሠርዌ አነምት ፡-(፩ዜና ፡-፲፩ ፡-፳፪)።
[4]:-አለቃ፤ ጭፍራ፤–ሰሪው ሰረወ፤ ሰርዌ።
ሠርዮ ፡-ቀለም ስባቅ፤ ማናቸውም ዐይነት። ሠርዮ ምስለ ፀምር ፡-(ቄር)።
ሠርዮ ዮት ፡-(ሠረየ ይሤሪ ይሠሪ) መሠረይ፤ ሥራይ ማድረግ፤ አስማት መድገም፤ መጠንቈል ማሟረት፤ ምትሀት ማሳየት፤ የክፉ። እንዘ ይሤርያ መሠርይ ጠቢብ። አንትሙ መሰግላን ዘትሤርዩ ሀገረ ፡-(መዝ ፡-፶፯። ስንክ ፡-ሐም፲፭)።
፡-ማዳን ፥ መፈወስ፤ መድኀኒት ማድረግ፤ ለማዳን። ውእቱ አቍሰለነ ወይሤርየነ። ሥረይ ላቲ ለነፍስየ ፡-(ሆሴ፮ ፡-፩። መዝ ፡-፵)።
ሠርገለ ፡-አጋደመ፤ መሥመር ጣለ፤ አሠመረ፤ በርሳስ በቀለም በወስፌ ነደፈ በገረ፤ አስነበረ፤ የወረቀትና የብራና።
ሠርገል ፡-(ዕብ ሳርጌል) መሥመር፤ ማሥመሪያ፤ አራት ገጽ ያለው፤ ቀጥ ያለ፤ የተካከለ ዐጭር ዘንግ።
ሠርጕ ፡-ጌጥ፤–ሰረገ፤ ሰርገወ።
ሠርግ ፡-(ዐረ ሸርግ) መስኖ፤ የመስኖ ውሃ፤ ቦዩ መትረቡ፤ ታናሽ ወንዝ፤ ኵሬ ዐዘቅት።
ሠርጽ ፡-(ጻት። ዕብ ሼሬጽ፤ ተሐዋሲ) ቡቃያ፤ ዐዲስ ወጣት፤ ለጋ ቀንበጥ፤ ሙሽራ ጫፍ፤ ውልብልቢት። ዘርዕ ምስለ ሠርጽ። ሠርጽነ ዘእንበለ ይጸምሒ። ሠርጸ ሊባኖስ። ሠርጸ ገዳም። ዘሠናይ ሠርጹ ወጽፉቅ ቈጽሉ ፡-(ዓሞ፱ ፡-፲፫። ጥበ፪ ፡-፰። ሢራ፶ ፡-፰። ሕዝ፲፮ ፡-፯። ፴፩ ፡-፫)። ሠርጸ ጢስ ቢል ዐምደ ጢስ ማለት ነው፤ ዐምደ ደመና እንደ ማለት ፡-(ማሕ፫ ፡-፮)።
ሠቀየ ፡-አጠጣ፤–ሰቅይ ሰቀየ።
ሠቂቅ ቆት ፡-(ሠቀ ይሠቅቅ ይሥቅቅ። ዕብ ሣክህ) ማልበስ፤ መክደን፤ መሸፈን። መሠቀቅ፤ ማሠቀቅ።
ሠቅ ፡-ማቅ፤–ሠቂቅ ሠቀ።
፡-(ቃት። ዕብ ሣቅ። ሱር ሣቃእ። ቅብጥ ሦክ) በቁሙ፤ ማቅ፤ ጕራጅ፤ ምንጣፍ፤ ከፀምር የሚሠራ ሸካራ፤ የሚኰሰኵስ፤ የሚያሠቅቅ፤ በሐዘን ጊዜ የሚለብሱት፤ የሚያሸርጡት። ታላቅ ኪስ፤ ከረጢት፤ የማቅ ዐይበት፤ ዳውላ። ጠብለልዎ በሠቅ። ቍሰሊሆሙ መዝመዙ በሠቅ። አልበሱ ምሥዋዐ ሠቀ። ቅንቲ ሠቀ። እግዚ ረበቦ ከመ ሠቅ ለተባዕታይ ማይ። ወገብረ ሠቃተ ምሉአ ኆጻ ፡-(ስንክ ፡-መስ፩። ኅዳ፩። ዮዲ፬ ፡-፲። ኢሳ፫ ፡-፳፬። መቃ ፡-ገ፳፭። ስንክ ፡-መጋ፰)።
ሠቅሠቀ ፡-(ዕብ ሣባኽ። ዐረ ሸበከ) ሸከሸከ፤ ሠራ፤ ታታ፤ በሳሳ፤ የማቅ የመግለቦ ፥ የወንፊት ያይነ ርግብ ሥራ። ከጥፊው በቀር አንቀጹ አይገኝም።
ሠቅሠቅ ፡-ዝኒ ከማሁ፤ የተበሳሳ፤ መግለብ ፥ ዐይነ ርግብ። በሥቅሡቅ ፈንታ ሠቅሠቅ ይላል። ወግበር መጥበስቶ ሠቅሠቀ ከመ መሥገርተ ዓሣ ዘብርት። እንተ ሠቅሠቅ ትሬኢ ፡-(ዘፀ፳፯ ፡-፬። መሳ፭ ፡-፳፰)።
ሠበ ሠበበ ፡-(ሠቢብ። ዕብ ሾቤብ፤ ሻቤብ) ወጋ በሳ፤ አሳለፈ። ሰበረ አጐበጠ፤ ጠመዘዘ። ሽባ ሽቦ ማለት የዚህ ዘር ነው።
ሠበረ ፡-በቁሙ፤–ሰቢር ሰበረ።
ሠበን ፡-በቁሙ ፥ ነጭ ልብስ፤–ሰበን።
ሠበከ [1]:-አስተማረ፤–ሰቢክ ሰበከ።
[2]:-ሠራ ጠፈጠፈ፤–ሰብኮ ሰበከ።
ሠበጠ ፡-(ሠቢጥ፤ ፀበጠ ተፀብጠ) ቀረበ ፥ ተዘጋጀ፤ ዝግጁ ኾነ፤ ለመብላትና ለመበላት ፥ የሰውና የምግብ። ፈንታውን ያዘ ተረከበ፤ እጅ አደረገ፤ ለመቍረስ ለመጕረሥ። ፀበጠንና ኔአን እይ።
ሠቢሕ ሖት ፡-(ሠብሐ፤ ይሠብሕ ይሥባሕ። ትግ ሐባ ሸብሐ) መሥባት ፥ መወፈር፤ መደንደን ፥ ጮማ መኾን። ይሠብሕ መራዕይከ። ሠብሐ ወገዝፈ ወርሕበ። ዘሠብሐ ትጠብሑ ፡-(ኢሳ፴ ፡-፳፫። ዘዳ፴፪ ፡-፲፭። ሕዝ፴፬ ፡-፫)።
(ጥ) ሠብሐ አመሰገነ ፡-አመሰገነ፤–ሰብሖ ሰብሐ።
ሠብል ፡-በቁሙ፤–ሰቢል ሰብለ።
ሠብሠበ ፡-(ሰበበ፤ ወሰበ። ዕብ ሻብሼብ) ታጠረ ተከበበ ፥ ተቀዳጀ፤ በዐጽቅ በሐረግ የሥራ የጌጥ። ሸበሸበ አሸበሸበ፤ ሽብሽቦ ሽብሸባ አደረገ፤ የስፌት የማሕሌት። ሰበበንና ወሰበን እይ።
ሠብሣብ [1]፡-(ባት። ጽር ሳርጋኒ። ዐረ ዘንቢል። ዕብ ሳል) ታላቅ ቅርጫት አፈ ሰፊ፤ የጐታ ዐይነት ፥ ከዐጽቅ ከሐረግ የተሠራ። ወአውረዱኒ በሠብሣብ እንተ መስኮት እምአረፍት ፡-(፪ቆሮ ፡-፲፩ ፡-፴፫)።
[2]:-ጋብቻ ግቢ፤–ወሰበ ሰብሳብ።
ሠብእ ፡-ሰው፤–ሰቢእ ሰብአ።
ሠተረ ፡-ዘረጋ፤–ሰቲር ሰተረ።
ሠትር ፡-መሥመር፤ ወስፌ ርሳስ ቀለም ያለፈበት፤ ሰንበሩ ንድፋ ቢጋሩ።
ሠቲር ሮት ፡-(ሠተረ ይሠትር ይሥትር። ዕብ ሣታር። ዐረ ሸተረ) መሠንተር፤ መቅደድ፤ መሠንጠቅ፤ መክፈል፤ መቍረጥ መበጠስ መቈንጸል፤ መግረፍ መግጠብ ማቍሰል። ለገብር እኩይ ሥትሮ ገበዋቲሁ። አዘዘ ይሥትርዎሙ እስከ ያስተርኢ ንዋየ ውስጦሙ። አዘዘ ይስቅልዋ በሥዕርታ ወይሥትርዋ ሠለስተ ሰዓተ ፡-(ሢራ፵፪ ፡-፭። ዲድ ፡-፳፪። መቃ። ስንክ ፡-ጥቅ ፡-፭ና ፡-፲፰ ፡-፳፭)። ዘትርን ተመልከት፤ የዚህ ዘር ነው።
ሠነነ ፡-እሾለ፤–ሰኒን ሰነነ።
ሠኑይ ፡-ኹለት፤–ሰንይ ሰነየ።
ሠኒቅ ቆት ፡-(ሠነቀ ይሠንቅ ይሥንቅ። ዐረ ሸነቀ፤ ዐነቀ። ሱር ሥናቅ፤ ዐጣ ተቸገረ) መሠነቅ፤ ሥንቅ መያዝ፤ መውሰድ፤ ለመንገድ የሚኾንን ነገር ማከት፤ ማሰናዳት። ኢሠነቀ እምንዋይከ ዘእንበለ መግነዝ ፡-(ግንዘ። ኢያ፱ ፡-፪። ማር፱ ፡-፰)።
ሠናይ ፡-(ይት ያን ያት) መልካም፤ ውብ፤ ደግ በጎ፤ ቅን፤ ደስ የሚያሰኝ፤ የመልክ የጠባይ። ሠናይ ለርእይ። ሠናይት በራእይኪ። ምግባር ሠናይ። ሠናይት ለሠናያን ተፈጥረት። ሠናይ ልብ። መክፈልት ሠናይ። ዐስብ ሠናይ። ዜና ሠናይ። ቃል ሠናይ ፡-(ዘፍ፪ ፡-፱። ዮዲ፲፩ ፡-፳፫። ማቴ፭ ፡-፲፮። ሢራ፴፱ ፡-፳፬። ሉቃ፰ ፡-፲፭። ፲ ፡-፵፪። መክ፬ ፡-፬። ሮሜ፲ ፡-፲፭። መዝ ፡-፵፬)። ሠናይ ቅጽልና በቂ እየኾነ እንዳወራረዱ በብዙ ዐማርኛ ይፈታል፤ ምስጢሩ ግን ከመልካምነት አይወጣም። ውስተ እዴሆሙ ሀለወት ሠናይቶሙ ቢል፤ ብዕል በረከት ድልብ ገንዘብ ያሰኛል ፡-(ኢዮ፳፩ ፡-፲፮)።
ሠኔ ፡-(ቅብጥ ፓዎኒ። ዕብ ሲዋን) የወር ስም፤ ዐሥረኛ ወር፤ በግብጽና በኢትዮጵያ። ሠናየ ዘርዕ፤ ወርኀ ዘርዕ ሠናይ ማለት ነው። ፡-(ተረት) ለሞኝ ሠኔ በጋው መስከረም ክረምቱ። ጋላም ዘር ሲል ሠኚ ይላል።
ሠንአ ፡-ገጠመ ተስማማ፤–ሰኒእ ሰንአ።
(ጥን) ሠንዮ ዮት ፡-(ሠነየ ይሤኒ ይሠኒ። ዐረ ሠነዐ፤ ሐሡነ። ዕብ ሻናህ፤ መልኩን ለወጠ፤ ሌላ ኾነ) ማማር፤ መዋብ፤ ሐዲስ መልክ ማውጣት፤ ጥሩ ውብ ደመ ግቡ መኾን፤ በመልክና በጌጥ ደስ መስኘት። ሠባሕኪ ወሠርይኪ ጥቀ ፈድፋደ። ሕሥምት እንተ ሠነየት። ይሤኒ ላሕዩ። ሠነየት ራእዮሙ ፡-(ሕዝ፲፮ ፡-፲፫። ማሕ፯ ፡-፯። አርጋ ፡-፩። መዝ ፡-፵፬። ዳን፩ ፡-፲፭። መሳ፲፭ ፡-፪)።
፡-መብለጥ፤ መሻል፤ ደግ ፥ ደኅና ፥ መልካም መኾን፤ የጠባይ። ቦ ብእሲት እንተ ትሤኒ እምብእሲት። ዘይሤኒ ወይነ። ይሠርሕክሙ በእንተ ትሤኒ። በእከየ ገጽ ይሤኒ ልብ ፡-(ሢራ፴፮ ፡-፳፮። ዮሐ፪ ፡-፲። ጦቢ፯ ፡-፲፩። መክ፯ ፡-፬)።
ሠዐለ [1]:-ለመነ፤–ስኢል ሰአለ።
[2]:-ሳለ፤–ሰዐለ።
ሠዐረ ፡-ሻረ፤–ስዒር ሰዐረ።
ሠዓሊ ፡-(ሊት ልያን ያት) የሚሥል፤ የሚፈጥር፤ ሣይ ሣዪ፤ ፈጣሪ። ሠዓሊና እንዘ እሬኢ ባማርኛ ይተባበራሉ። ፡-(ግጥም፤ ሚስቱን ሠዓሊ የቀማው) ባላየው ነው እንጂ ተኝቼ ሌሊት፤ ሚስቴን ሳይ በወሰዳት። ፡-(የሠዓሊው መልስ) እንቅልፋምነትኽን ይልቅ እኔ ዐውቃለኹ፤ ብሥል ሰው እንጂ ነኝ ምን መስዬኽ አለኹ። ሠዓሌ ሕፃናት ፡-(ቅዳ። ድጓ)።
ሠከረ ፡-(ሠኪር። ዕብ ሣካር) ተከራየ፤ በቍርጥ ገዛ ተዋዋለ፤ የከብት የጕልበት የመሣሪያ። ዐሰበንና ዐሰየን እይ፤ አሽከር ማለት፤ ከዚህ ወጥቷል። ሻከረ፤ ሸካራ ኾነ ፡-(ዐማርኛ)።
ሠክረ ፡-ሰከረ፤–ሰኪር ሰክረ።
ሠወን ፡-ልጋግ ቈበር፤ ሐረፋ የአፍ ዛሕል።
ሠዊት ፡-(ዕብ ሽቦሌት) እሸት ጐምር፤ ዛላ ዘለላ እንቡጥ፤ ታሽቶ ተፈልፍሎ የሚበላ፤ የእክልና የተክል። ወናሁ ሰብዐቱ ሠዊት። ወአኀዙ ይምሐዉ ሠዊተ ፡-(ዘፍ፵፩ ፡-፭–፯። ማቴ፲፪ ፡-፩)። ሦታ ወጣት ፥ ጐበዝ ጕልማሳ ፥ ልጅ እግር። እሸቴ ውብ እሸት እንዲሉ። በኵር በኵራት ቀዳምያት ማእረር በማለት ፈንታ ሠዊት ይላል፤ የመላሽ ስሕተት ነው። አመ ዕለተ ሠዊት ፡-(ዘኍ፳፰ ፡-፳፮። ዘዳ፳፫ ፡-፳፭። መሳ፲፭ ፡-፭)።
ሠዊን ኖት ፡-(ሦነ፤ ሠወነ ይሤውን ይሡን) ማልገግ ፥ መቈበር ፥ ማዝረብረብ፤ ልጋጋም ቈበራም መኾን ፥ ሐረፋት መድፈቅ። ሐረፈንና ሤነን እይ። ይሤውኑ በአፉሆሙ ፡-(አዋል)።
ሠዊዕ ዖት ፡-(ሦዐ ይሠውዕ ይሡዕ፤ ይሣዕ፤ ይሧዕ፤ ይሥዋዕ። ዕብ ሻዌዐ፤ ጮኸ ጠራ። ዐረ ሸወይ፤ ጠበሰ) መሠዋት ፥ መሥዋዕትና ጸሎት ማቅረብ፤ ማረድ መግደል ፥ ማንደድ ማቃጠል፤ ማሳረር ማጤስ ፥ መጥበስ ማንጠስጠስ፤ ለማሳረግ፤ ሰረፈን እይ። ለሠዊዕ መሥዋዕተ፤ ዘአምጽአ ለሠዊዕ። ዐርገ ከመ ይሡዕ። ወሦዐ መሥዋዕተ። ሡዕ ለእግዚ መሥዋዕተ ስብሐት ፡-(ዘሌ፩ ፡-፫ ፡-፬። ፩ነገ ፡-፩ ፡-፳፩። ዘፍ፵፮ ፡-፩)።
ሠዊክ ኮት ፡-(ሦከ ይሠውክ ይሡክ። ዕብ ሳኽ ያሱኽ፤ ወደየ፤ መስሐ) መውጋት ፥ ጠቅ ማድረግ፤ ማሳመም። እሾኽ ማብቀል፤ እሾኽ መባል፤ እሾኻም ሸውከኛ መኾን።
ሠዊጥ ጦት ፡-(ሦጠ ይሠውጥ ይሡጥ። ወሰጠ፤ ሶጠ፤ ሠጠየ) መመለስ መቀለስ፤ መልሶ ማምጣት ማግባት ፥ ቀድሞ ወደ ወጣበት ወደ ነበረበት። እሠውጦሙ ውስተ ዛ ምድር። አመ ሣልስት ዕለት ሦጣ ለነፍሱ ውስተ ሥጋሁ። ብዉሕ ሎቱ ሠዊጠ መንፈስ ኀበ ማኅፈደ ሥጋሁ ፡-(ኤር፳፬ ፡-፮። ቅዳ ፡-አፈ። መጽ ፡-ምስ)። በሦጠ ፈንታ አሦጠ ይላል፤ ስሕተት ነው። ወአሦጡ ቀሣውቲሆሙ ዕራቆ። ወርቀ አሦጥነ እምድረ ከነዓን። አሡጥ ለካልእከ ፡-(ኤር፲፬ ፡-፫። ኩፋ ፡-፵፫። ዘዳ፳፪ ፡-፩)።
ሠዋዒ ፡-(ዒት ዕያን ያት፤ ዕት) የሚሠዋ ፥ አቃጣይ ዐጣኝ የምሥዋዕ አገልጋይ። አብርሃም አቅረበ ወልዶ ወኢሦዖ ወተዐሰየ ዕሴተ ሠዋዒ ፡-(አፈ ፡-ተ፴፬)። ካህን ካህናት በማለት ፈንታ ሠዋዒ ሠዋዕት ይላል ፡-(ዘፅ፲፰ ፡-፩። ፲፱ ፡-፳፪ ፡-፳፬። ፩ቆሮ ፡-፱ ፡-፲፫)።
ሠዋዪ ሥዉይ ፡-የሸተ የበሰለ፤ ነፍስ ያዋለ።
ሠዋጢ ፡-(ጢት ጥያን ያት፤ ሠወጥ) የሚመልስ፤ መላሽ ቀላሽ።
ሠውር ፡-ኮከብ፤–ተውር ቶር።
ሠውት ፡-ስመ ፊደል ሠ፤ ሠዊት ሠዒት፤ ሠወስት ራስ ፥ ሦስት ዛላ ባለሦስት ጣት ማለት ነው፤ መሥዔ እንደ ማለት። ከሠለሰና ከሠዐየ ጋራ ይሰማማል፤ በዕብራይስጥም እንደዚሁ ሦስት ጣት አለው።
፡-ሠውት፤–ስመ ፊደል፤–ሠወየ።
ሠውይ ዮት ፡-(663) ፡-(ሠወየ ይሠዊ ይሥወይ። ዐረ ሸወይ፤ ጠበሰ። ዕብ ሻዌህ፤ መሰለ ተካከለ፤ አማረ ተዋበ ተወደደ) መሸት ፥ መጐምራት፤ መብሰል፤ ሰብለን እይ። አመ ይሠዊ ሥርናይ ፡-(ኢያ፫ ፡-፲፭። ያዕ፭ ፡-፯። መጽ ፡-ምስ)። በሠወየ ፈንታ አሥወየ ይላል፤ ስሕተት ነው ፡-(ስንክ ፡-ታኅ፯)።
ሠውጥ ፡-ጅራፍ፤–ሰወጠ።
ሠዝይ ዮት ፡-(ሠዘየ ይሤዚ ይሥዚ። ዐረ ሸዘ፤ ሸዘእ) መለየት ፥ መነጠል፤ መከልከል፤ ማድላት። እንዘ ትሤዚ። ኢይሤዚ እንበይነ ንዴቱ ለነዳይ። ምሕረተ ነዳያን እለቡ ዘእንበለ እሥዚ ፡-(ተረ ፡-ቄር። ሲኖዶ ፡-፲፪። ሢራ፴፪ ፡-፲፮። ስንክ ፡-መጋ፲፪)።
ሠዪም ሞት ፡-(ሤመ ይሠይም ይሢም። ዕብ ሢም። ሱር ሣም። ዐረ ሣመ፤ አኖረ) መሾም መሸለም፤ ማሠልጠን፤ መቀደስ ማክበር። እሠይመከ ውስተ ኵሉ ምድር። ሤሞ ለዮሴፍ ዲበ ኵሉ ንዋዩ። አንትሙ ጳጳሳት ኢትሢሙ ኵሎ ዘረከብክሙ። ሶበ ትሠይሞ ለጻሕል ወለጽዋዕ ፡-(ዘፍ፵፩ ፡-፵፩። ኩፋ ፡-፴፱። ቀሌ። ሥር ፡-ቅዳ)።
፡-ማስቀመጥ ማኖር፤ መምላት ማሳደር፤ ማቅረብ ማዘጋጀት፤ የምግብ የልብስ ለትንባኾም ሳይቀር ለጠላ ለምርት ይነገራል። ህየ ይሠየማ። ወሤሞ ህየ። ሤመ ላዕሌሆሙ መንፈሶ ቅዱሰ። ሤመ ውስቴቲ ምስጢራተ ብፅዓን ፡-(ቅዳ ፡-ግሩ። ዘፍ፪ ፡-፰። ኢሳ፷፫ ፡-፲፩። ማር ፡-ይሥ፩ ፡-፲፫)።
ሠዪብ ቦት ፡-(ሤበ ይሠይብ ይሢብ። ዕብ ወሱር ሣብ። ዐረ ሻበ) መሸበት፤ ማርጀት፤ መጨበር ነጭ ጠጕር ማውጣት። መሻገት፤ መበላሸት። ሣህበን እይ፤ የዚህ ዲቃላ ነው።
ሠዪን ኖት ፡-(ሤነ ይሠይን ይሢን። ዐረ ሻነ፤ አሳደፈ። ዕብ ሀሽቴን ሸነ) መሸኘት፤ ሸኝታ መኾን። መሸን መሽናት፤ ማውጣት ማፍሰስ፤ ፊር ዠረር ጭርቅ ማድረግ። ዘይሠይን ላዕለ መንጸፉ። ዘይሠይን ማየ። በሊዕየ እኰስሕ ወሰትይየ እሠይን ፡-(ፍ ፡-ነ ፡-፴፫ ፡-፫። ቄድር። ፈላስ)።
ሠዪጥ ጦት ፡-(ሤጠ ይሠይጥ ይሢጥ። ቅብጥ ሾት፤ ንግድ) መሼጥ መለወጥ፤ መቸርቸር መሸቀጥ፤ መስጠት፤ መቀበል ከገዢ። ነገደ የሩቅ ሤጠ የቅርብ የመደብር። ሠዪጥ ወተሣይጦ። ዘሤጠ ብኵርናሁ ፡-(ራእ፲፫ ፡-፲፮። ዕብ፲፪ ፡-፲፮)። በሤጠ ፈንታ አሥየጠ ይላል፤ የጣፊ ስሕተት ነው። አሢጠኒ ኪያሁ በሤጥ ፡-(፩ዜና ፡-፳፭ ፡-፳፪)።
ሠያሚ ፡-(ሚት ምያን ያት) የሚሾም ሿሚ፤ አስቀማጭ አኗሪ። ሠያሜ ካህናት። ሠያሜ ሕግ ፡-(ሲኖዶ። ድጓ። አፈ ፡-ድ፴፪)።
(ጥ) ሠያብ ሥዩብ ፡-ሥዩብ፤ የሸበተ ሽበታም፤ አሮጌ ሽማግሌ፤ ሻጋታ ብልሹ።
ሠያን ሠያኒ ፡-(ኒት ንያን ያት፤ የንት) የሚሸኝ፤ ሸኝታ። የሸነ የሚሸን፤ ሻኝ ሽንታም፤ ሽንት የማይቋጥር፤ ፈሪ።
ሠያጢ ፡-(ጢት ጥያን ያት፤ የጥ) የሼጠ የሚሼጥ ሸያጭ፤ ዐጣሪ ነጋዴ ቸርቻሪ ሸቃጭ። ሠያጢ ወተሣያጢ። ይሁዳ ሠያጤ እግዚኡ። ሠየጠ አሕዛብ ተፋጸዩኪ። ሠየጥኪ በነፍሰ ሰብእ ፡-(ፍ ፡-ነ ፡-፴፫። መጽ ፡-ምስ። ሕዝ፳፯ ፡-፴፮። ራእ፲፰ ፡-፫)።
ሠይእ ፡-ከንቱ ሥራ፤–ሰይእ።
ሠገል ፡-ጥንቈላ፤–ሰጊል ሰገለ።
ሠገም ፡-ገብስ፤–ሰጊም ሰገመ።
ሠገረ ፡-(ዕብ ሳጋር፤ ሳካር) ሸጐረ፤ ዘጋ ቈለፈ፤ የመዝጊያ የቅናት። ጐተተ አሰረ፤ ከሐብስ አገባ። አጠመደ ፥ ወጥመድ አኖረ፤ በወጥመድ ያዘ። መጽሐፍ ግን በሠገረ ፈንታ አሥገረ ይላል፤ ስሕተት ነው። አሥግሩ ለነ ቈናጽለ። አሥጋሬ ዖፍ። ያሠግሩ ሰብአ። ከመ ኢታሥግርከ በማሕሌታ። አሥግረኒ እምባሕረ እሳት ፡-(ማሕ፪ ፡-፲፭። ፍ ፡-ነ ፡-፴፫ ፡-፬። ኢሳ፰ ፡-፲፭። ሢራ፱ ፡-፬። ስንክ ፡-መጋ፴)።
ሠገራ ፡-በቁሙ፤ ዐዘቅተ ኵስሕ፤ ሰው ሲገባበት የሚዘጋና የሚሸጐር።
ሠገራዊ ሠገራዋታዊ ፡-የዘበኛ ወገን በረኛ ፥ እስር ጠባቂ ፡-(ስንክ ፡-ታኅ፲፪። መጋ፯)።
ሠገር ፡-(ራት) ወታደር፤ የሐብስ ዘበኛ፤ እስሮች እንዳይወጡ እንዳያመልጡ በሩን ዘግቶ ሸጕሮ የሚጠብቅ። ትካፈሉ አልባሲሁ ሐራ ሠገራት። ንሥኡ ሠገራተ ፡-(ድጓ። ማቴ፳፯ ፡-፷፭)።
ሠገኖ ፡-ሰጐን፤–ሰገኖ ሰገነ።
ሠጕዐ ፡-ሳገ ሰነገ፤–ሰጕዕ ሰጕዐ።
ሠጊር ሮት ፡-(ሠግረ ይሠግር ይሥገር። ዕብ ሻጋር) መሥገር፤ ቶሎ ቶሎ መኼድ ፥ ኵል ኵል ድቅ ድቅ ማለት፤ የበቅሎ የሕፃን። መሻገር ፥ ሽግር ማለት፤ መራመድ እያለፉ መርገጥ፤ ሖረንና ሄደን ኬደን እይ። ወሶበ ሠግረ ምዕረ ወካዕበ። ወሖረ ምስሌሆሙ እንዘ ይሠግር። ክህለ ሠጊረ ዘእንበለ በትር። ወበዘባነ ባሕር ይሠግር፤ ሐዊሮ ወሠጊሮ ፡-(፩ነገ ፡-፲፯ ፡-፴፱። ግብ፫ ፡-፰። ቀሌ። ተረ ፡-ቄር)።
ሠጊው ዎት ፡-(ሠገወ ይሠጉ ይሥጉ። ዕብ ሣጋህ) አው ሠግዎ ዎት፤ ፡-(ሠገወ ይሤጉ ይሠጉ) መብቀል ፥ ማደግ፤ መግዘፍ መግነን፤ መጽናት መበርታት፤ መብዛት መርባት። መሥጋት ፥ ማሰብ መፍራት ፥ ሥጉ መኾን፤ ረገበን እይ።
ሠጋሪ [1]፡-ሠጋር፤ በቁሙ፤ ኸያጅ ተራማጅ።
[2]፡-መሠግር፤ ፡-(ራን) ዘጊ ሸጓሪ፤ የሚያጠምድ አጥማጅ፤ ወጥመድ ሠሪ ፥ ዓሣ ወጋሪ። መሠግር ጴጥሮስ አመ አሥገረ። እስመ መሠግራን እሙንቱ ፡-(ቅኔ። ማቴ፬ ፡-፲፰። ማር፩ ፡-፲፮)።
ሠግላ ፡-ሾላ፤–ሰጊል ሰገለ።
ሠግራዊ ፡-(ዊት ውያን ያት) የሠግር ፥ ሠግራም፤ ሠግር ያለበት ባለሠግር። ዓመተ ፀሓይ ሠግራዊት ፡-(አቡሻ ፡-፲፯)።
ሠግር ፡-በቁሙ፤ የዕለት የብተት ሥግሪያ እርምጃ፤ የጨረቃ ወር መተላለፍ፤ ወይም ትርፍ ፍድፋጅ። ይገብሩ ሠግረ አሐደ ወርኀ ለለ ሠለስቱ ዓመት። በራብዕት ዓመት ይገብሩ ሠግረ አሐዱ ዕለት፤ ወይሰምይዋ ለወርኀ ሠግር ጳግሜን፤ ወትከውን ይእቲ ዓመት ሠግረ ፡-(አቡሻ ፡-፪)።
ሠጠመ ፡-በቁሙ፤–ሰጢም ሰጠመ።
ሠጠቀ ፡-(ሠጢቅ። ሠጠጠ። ዕብ ሳዳቅ። ሱር
ስዳቅ። ዐረ ጸደዐ) ፤ ሠነጠቀ ፤ ፈለጠ ተረተረ ፤
ቀደደ ዐረሰ ፤ ለየ ከፈለ ፤ በቁመት እንዳክርማ እንደ
ቄጠማ። ኢሳይያስ ዘሠጠቅዎ ለክልኤ ክፍል በሞሠርተ ዕፅ። መሠርይ ተናገረ ላዕለ ከይሲ ወሠጠቆ ለክልኤ። መባርቅት እለ ይሠጥቁ አብያተ። ወይሠጥቅ ምድረ አፍላግ። ሠጠቁ ትዕይንተ ኢሎፍሊ ፡-(መጽ ፡-ምስ። ስንክ ፡-ሠኔ፯። ዮሴፍ። ዕን፫ ፡-፬። ፪ነገ ፡-፳፫ ፡-፲፮)።
ሠጠወ ፡-ሰጠ፤ መለሰ፤–ሰጢው ሰጠወ።
ሠጢጥ ጦት ፡-(ሠጠ፤ ሠጠጠ ይሠጥጥ ይሥጥጥ። ዕብ ሻጥ፤ ቀዘፈ) ሠጠጥ ማድረግ መቅደድ፤ መሠንጠቅ፤ መሠንተር፤ መለየት መክፈል። ሠጠቀን እይ፤ የዚህ መንቲያ ነው። ሠጠጠ አልባሲሁ። ኦትሥጥጥ ልብሰተ ሥጋዌሁ። እሠጥጥ መጽሐፈ ኀጣውኢከ። ሠጠጡ ከርሦ። ሠጠጣ ለመንግሥትከ ፡-(ማቴ፳፮ ፡-፷፭። ተረ ፡-ቄር። ስንክ ፡-ሐም፰። ዮሴፍ። ፩ነገ ፡-፲፭ ፡-፳፰)። ሢጥ ሢጢጥ ማድረግ፤ ማንሚያጠጥ። ማሾጠጥ፤ ሾጣጣ ማድረግ።
ሠጣጢ ፡-(ጢት ጥያን ያት) የሚቀድ ቀዳጅ፤ ሠንጣቂ።
ሠጥሐ ፡-አሰጣ ዘረጋ፤–ሰጢሕ ሰጥሐ።
ሠጥይ ዮት ፡-(ሠጠየ ይሠጢ ይሥጢ። ዕብ ሣጣህ። ሱር ሥጣእ) መጽነን መሳብ መዘንበል፤ ማድላት ማጋደል። መለወጥ ማበድ፤ ከሕግ ከመንገድ መውጣት። ባለመጽሐፎች ግን አሰጣ ዘረጋ ብለው በሰጥሐ ዘይቤ ይፈቱታል። ኢይትቀነያ ለስቴ ወኢይሠጠያ ውስተ ስካር ፡-(ቲቶ፪ ፡-፫)። ብዙው መጽሐፍ ደግሞ በሠጠየ ፈንታ ተሠጥየ ይላል፤ አያሰኝም። እመ ቦ ዘተፈግዐ ወተሠጥየ፤ ዘይፌግዕ ወይሠጠይ። ብዙኃን እለ ተሠጥየ ልቦሙ በእንተ አንስት። ተመስወ ልቦሙ ወተሠጥየ ፡-(ሄርማ። ፩ዕዝ ፡-፬ ፡-፳፮። ኢያ፭ ፡-፩)።
ሠጺር ሮት ፡-(ሠጸረ ይሤጽር ይሥጽር። ዐረ ሸጸረ፤ ወጋ በሳ። ሸጠረ ከፈለ) መሠንጠር፤ መሠንጠቅ፤ መክፈል መፍለጥ፤ በቁመት። የጸዐለ ቤት ነው። ዘይሤጽር ዕፀወ። ምሣር ዘይሤጽር ፡-(መክ፲ ፡-፱። ዲድ ፡-፲)።
ሠፈረ ፡-በቁሙ፤–ሰፊር ሰፈረ።
ሡሩር ሥሩር ፡-የተመሠረተ፤ የተሠራ የተፈጠረ። እስመ ሰብእ ሡሩር እምነፍስ ወሥጋ። ሥሩራት ዲበ መንበረ ወርቅ ፡-(ፊልክ። ማሕ፭ ፡-፲፭)።
ሡራኄ ፡-(ኅያት) መብራት፤ ብርሃን፤ ጸዳል፤ ክብር፤ ጌጥ። ወሡራኄ እግዚ ተርእየ በደመና። ለክብር ወለሡራኄ። በርሀ ገጹ በሡራኄ መለኮት። ሡራኄ ወጸዳል ፡-(ዘፀ፲፮ ፡-፲። ፳፰ ፡-፪። ገድ ፡-ተክ። መጽ ፡-ምስ)።
ሡራሬ ፡-ሥራ፤ አሠራር። ሕንጼሃ ወሡራሬሃ አዳም ፡-(ድጓ)።
ሡዐት ፡-(ላ ጥ ሠዋ) መሠዋት፤ መሥዋዕት መኾን ፥ መሥዋዕትነት። ሥምረተ አብ በሡዐተ ወልዱ ፡-(መጽ ፡-ምስ)።
ሡዕ [1]፡-(ብ ሥዋዕ) ማቀጣጠያ፤ ጭራሮ ገለባ ኵበት፤ ጧፍ ጋዝ ክብሪት፤ የተልባ እግር ፈትል ፥ የፋኖስ ቋድ ከጋዝ የሚዋሐድ ዐብሮ የሚነድ። ሡዐ ዘይጠይስ ኢያጠፍእ። ወጠፍኡ ከመ ሐመደ ሡዕ። ይልበሱ ለቢጦነ ዘሡዕ ፡-(ኢሳ፵፪ ፡-፫። ፵፫ ፡-፲፯። ሥር ፡-ጳኵ)።
[2]፡-(ሦዕከ ትሠውዕ ትሡዕ) ትእዛዝ አንቀጽ፤ ስላንድ የቅርብ ወንድ። ሠዋ ፥ መሥዋዕት አቅርብ። ሡዕ ሊተ ወልደከ ፡-(ዘፍ፳፪ ፡-፪)።
ሡጠት ፡-መመለስ፤ አመላለስ ምለሳ፤ ምልስነት።
ሢመት ፡-መሾም፤ ሿሚ ወይም ተሿሚ መኾን ሹምነት፤ አሿሿም። ሹመት፤ ሥልጣን፤ ማዕርግ። ጸሎተ ሢመት። ከመ ኢይንሣእ ሢመተከ። በመዋዕለ ሢመትከ። ይሰዐር እምሢመቱ። ሢመተ ክህነት። አቀምክዎሙ በበ ሢመቶሙ። ሢመታት ወሥልጣናት ፡-(ኪዳ። ሢራ፲፪ ፡-፲፪። ስንክ ፡-ግን፲፪። ቀሌ። ቅዳ። ነሐ፲፫ ፡-፲፩። ዲድ)።
ሢሩይ ፡-(ያን ያት ሪት፤ ርይት) የታለለ ቀለም የገባ፤ ያደፈ የተኵለፈለፈ። ሢሩያነ በምሕረትከ አንጽሕ ፡-(ኪዳ)።
ሢራክ [1]፡-(ካት። ዐረ ሺራክ። ዕብ ሥሮኽ) ሢር፤ ማዘቢያ፤ ቶታን። መሥመር ወስፌው ርሳሱ ቀለሙ ያለፈበት፤ ንድፉ፤ ሰንበሩ፤ የቆመው የተጋደመው፤ ወይም ቀለም የሚወድቅበት ተለላው መዛሪያው። ወለለ ኍልቁ አኃዙ ቦቱ አኃዝ ዘበሢራኩ፤ ዘይኤምር ውስተ አይ። አእሚረከ አኃዘ ኍልቁ ዘበሢራኩ ፡-(መቅ ፡-ወን)።
[2]፡-የጸሎት የመዝሙር ክፍል፤ ቃሉ በመሥመር በመሥመር የተለየ፤ የሚያዜሙት የሚያስተዛዝሉት፤ እንደ ዳዊት ያለ ፡-(መጽ ፡-ምስ። ሄርማ)።
[3]፡-የሰው ስም። ጥበበ ኢያሱ ወልደ ሢራክ። ወኮኑ በመዋዕሊሁ ለሰሎምን እምነቢያት ናታን ወአክያ፤ወሊቀ ካህናት ሳዶቅ። ወኮነ ሊቀ ሐራሁ ኢያሱ ወልደ ሢራክ ወውእቱ ዘአስተጋብኦሙ ለመጻሕፍተ ሰሎሞን ወረሰዮሙ ኀምስተ መጻሕፍተ፤ ወእሉ እሙንቱ ምሳልያት ፥ ወተግሣጽ ፥ ወጥበብ ፥ ወጉባኤ ፥ ወማሕልየ መሓልይ፤ ወለኢያሱ ሊቀ አሐዱ መጽሐፍ ዘዕዉቅ ቦቱ ምሉእ እምጥበብ ወዕንቈ ባሕርይ ነገር ፡-(ጊ ፡-ወ ፡-ሐ ፡-ገ፹)።
ሢራይ ፡-(ያት። ሱር ሺራእ) ጥሩ ልብስ፤ ሐር፤ ፀምር ክታን፤ ቀለም የገባ የታለለ። አልባሲሆን ዘሜላት ወሢራይ። ግልቡባን በሢራያት ፡-(ኢሳ፫ ፡-፳፩–፳፫። መጽ ፡-ምስ)። በሢራይ ፈንታ ሢርዮን ሢራ ይላል፤ ፍችው ፩ ነው ፡-(ገድ ፡-አዳ። ፍ ፡-ነ ፡-፵፫ ፡-፲፪)። ሤራ ዐድማ፤ ክፉ ዱለት።
ሢበት ፡-ሽበት፤ ነጭ ጠጕር የርጅና አበባ፤ እርጅና ሽምግልና። በቈለ ሢበቱ። ሢበተ ልሂቅ። ቅድመ ዘሢበት ተንሥእ። ይደልዋ ኩንኖ ለሢበትከ። ዘየሐፅኖ ለሢበትኪ ፡-(ሆሴ፯ ፡-፱። ጥበ፪ ፡-፲። ዘሌ፲፱ ፡-፴፪። ሢራ፳፭ ፡-፪። ሩት፬ ፡-፲፭)።
ሢጠት ፡-(ላጥ ሼ) መሼጥ አሻሻጥ ሽጦሽ። ይሁዳ መከረ ለሢጠተ እግዚኡ ፡-(መጽ ፡-ምስ)።
ሣሃሊ ፡-(ሊት ልያን ያት) ልበ ሰፊ ፥ ነገር ዐላፊ፤ ይቅር ባይ ፥ ዐዛኝ ርሩ። ሥሂል ሠሀለ ባለው በቀተለ ቤት ግን፤ ሠሃሊ ፥ ሠሀልት ያሰኛል።
ሣህል ፡-(ላት) ይቅርታ ፥ ርኅራኄ ምሕረት፤ ዕርቅ ፍቅር። ኢይከውን ሣህል ላዕሌሆሙ። አልቦ ሣህል ለዘያወፅእ ምክረ ቢጹ። ዘበእንቲኣሁ ረከብነ ሣህሎ ፡-(ሔኖ፩ ፡-፰። ሢራ፲፫ ፡-፲፪። ሮሜ፭ ፡-፲፩)። ንዴት ኀሳር ሕርትምና በማለት ፈንታ ሣህል ይላል፤ የመላሽ ስሕተት ነው ፡-(፩ቆሮ ፡-፲፭ ፡-፲፱)። ፪ኛም ፥ ጽርኡ ምክንያት ያለውን ሣህል ይላል፤ ባለብሉዮች ግን ምግብ ይሉታል ፡-(ሢራ፵፬ ፡-፲፯)። እስመ ይኄይስ እምሐዪው ሣህልከ ያለውንም ፥ በሕይወት አንጻር ሞት ይሉታል ፡-(መዝ ፡-፷፪)።
ሣህሎ ፡-(ሣሀለ ይሣህል) መስፋት መዘርጋት፤ ቀጥ ለጥ ማለት መተካከል፤ መለዘብ መለስለስ ፥ እንደ ነትና እንደ መሳል መኾን። ማዘን ፥ መራራት፤ ይቅር ማለት መታረቅ፤ ቂምን ድርቅናን ሸካራነትን መተው። መጽሐፍ ግን በሣህለ ፈንታ ተሠሃለ ተሣህለ ይላል፤ አያሰኝም። ተሠሃለኒ እግዚኦ። ይክል ተሣህሎ። ወለዘሂ ተሣሀልክዎ እሣህሎ ፡-(መዝ ፡-፶። ሢራ፲፮ ፡-፲፩። ሮሜ፬ ፡-፲፭)። መንገዱ የቀተለና የባረከ ነው።
ሣህር ፡-(ብ አሥህርት። ሱር ሣህራ። ዐረ ሸሀር) ሠርቀ ወርኅ ፥ ልደተ ወርኅ፤ የጨረቃ ወር መባቻ ፥ ጨረቃ የምትበቅልበት ቀን። በበዓላቲክሙ ወበአሥህርቲክሙ ፡-(ዘኍ፲ ፡-፲። ኢሳ፩ ፡-፲፫። ሆሴ፪ ፡-፲፬። ቆላ፪ ፡-፲፮)።
ሣህበበ ፡-(ሠዪብ ሤበ። ዐረ ሸሂበ) ሻገተ ፥ ተበላሸ፤ ዐመድማ ቅጠልማ ኾነ። ሤበን እይ ፥ አባቱ ርሱ ነው፤ ከቅጽሉ በቀር አንቀጹ አይገኝም።
ሣኅት ፡-ዕረፍት፤ ኅድእት፤ ረድኤት። ይረክባ ሣኅተ። እሁቦሙ ሣኅተ ንስቲተ ለመድኀኒት ፡-(ማቴ፳፮ ፡-፲፮። ማር፮ ፡-፲፩። ሉቃ፳፪ ፡-፮። ፪ዜና ፡-፲፪ ፡-፯)።
ሣሉሲም ፡-(ዕብ ሻሊሺም) ኀያላን ያርብሓን፤ አለቆች የጦር ሰዎች፤ ሦስተኛ ማዕርግ ያላቸው፤ ወይም ኀይላቸው ሦስቲዮ የኾነ የተጐነጐነ። ባለብሉዮች ግን ሢሶ ይሉታል። ርእሰ ሣሉሲም ፡-(፩ዜና ፡-፲፪ ፡-፲፰)።
ሣልሲት ፡-የቍጥር መደብ፤ የኬክሮስ ፫ኛ። ኣንዱ ሣልሲት ፷ ራብዒት ይኾናል፤ ኬክሮስን እይ ፡-(አቡሻ ፡-፲፩)።
ሣልሳዊ አው ሣልሳይ ፡-(ዊት ዪት ሲት) ሦስተኛ፤ ከሦስት አንድ ሢሶ። በሣልሳዊ ልደት እምአቡሁ፤ ሀለወነ ተዘምዶ ምስሌሁ። በእንተ ተዋስቦ ሣልሲት። ሣልሲተ ኢን ፡-(ቅኔ።ፈ ፡-መ ፡-፭ ፡-፮። ሕዝ፵፮ ፡-፲፬)።
ሣልስ ፡-(ስት) ሦስተኛ፤ ሦስት ፥ በስቲያ ወዲያ። ናሁ ሣልሶሙ ዮም እንዘ ይጸንሑኒ። አመ ሣልስት ዕለት ከብካብ ኮነ። እስከ ሣልስ ወራብዕ ትውልድ። ትማልመኒ ወሣልስተኒ ፡-(ማር፰ ፡-፪። ዮሐ፪ ፡-፩። ዘፀ፳ ፡-፭። ፩ዜና ፡-፲፩ ፡-፪)።
ሣራሪ ፤ (ሪት ርያን ያት) ፤ የሚመሠርት ፤ መሥራች
፤ ሠሪ ፈጣሪ። ሣራሪሃ ለምድር ፤ ሣራሪሃ
ለነፍስ (ኪዳ)።
ሣራብ ፡-(ዕብራ) ሳማ ፥ ዶቢ፤ ናጫ፤ አለብላቢት፤ ሲያበዛ ሣራቢም፤ ይላል። እስመ ሣራቢም ወአሥዋክ ምስሌከ ፡-(ሕዝ፪ ፡-፮)።
ሣሬት [1]፡-(ርያት) ሸረሪት፤ ፈታይ ፥ አቅጣኝ። ዘሣሬት ውእቱ ተመይኖ ግብር። ፈትለ ሣሬት እንመተ ሣሬት። ለሣሬት ፈትለ እዱ እምነ ዕርቃን ኢያትረፎ ፡-(ፈላስ። አፈ ፡-ተ፴፬። ቅኔ)።
[2]፡-ሣሬት፤–ሸረሪት፤–ሠረየ።
ሣርኅ ፡-(ኃት) ዝኒ ከማሁ። ወአርኣያ ሣርኁ ለእግዚ ከመ ነደ እሳት ፡-(ዘፀ፳፬ ፡-፲፯)።
ሣርኆ ኆት ፡-(ሣርኀ ይሣርኅ። ዐረ ሸረኀ። ዕብ ዛራሕ) መብራት፤ መጽደል፤ መሸብረቅ፤ መፍለቅ ማንጸብረቅ፤ መንደድ መቃጠል፤ ቦግ ማለት።
ሣርሮ ሮት ፡-(ሣረረ ይሣርር። ዕብ ሻራር፤ ነግሠ፤ ኀየለ። ያሣድ) መመሥረት፤ አጥልቆ ቈፍሮ መሠረት መጣል፤ ማቆም መትከል፤ ከዚያ በኋላ መንደቅ፤ መሥራት፤ መናስ መገንባት። አቅደምከ ሣርሮታ ለምድር። ሣረሩ ቤተ ፡-(መዝ ፡-፻፩። ሐጌ፪ ፡-፲፱)።
ሣሮን ፡-(ዕብ ሻሮን) ስመ ሀገር፤ የባሕር የወንዝ ዳር፤ ሜዳ ረባዳ፤ ከኢዮጴ እስከ ቀርሜሎስ ያለ፤ በምሥራቅም ከዮርዳኖስ ማዶ ሮቤልና ጋድ የወረሱት ፡-(ኢሳ፴፫ ፡-፱። ፩ዜና ፡-፭ ፡-፲፭)። ባለብሉዮች ግን ችፍርግ ታናሽ ዛፍ ይሉታል፤ ፍችው አይዶለም።
ሣቃዪ ፡-(ዪት ይያን ያት) የሚሣቅይ፤ መከራ የሚያሳይ፤ አስጨናቂ። ሣቃዪተ አህጉር ፡-(፩ዕዝ ፡-፪ ፡-፳፪)።
ሣቅዕ ፡-የምድር ማእዝን፤ አንዲት ክፍል ምድር። እስመ ደቂቀ እስራኤል ኢነበሩ ውስተ ኵላ ምድር፤ ዳእሙ ውስተ ሣቅዕ ዘውእቱ ማእዘንት። ውስተ ኵሉ ሣቅዕ ፡-(ግብ ፡-ሕማ ፡-ገ፶፱። ፻፭)።
ሣቅዮ ዮት ፡-(ሣቀየ ይሣቂ። ዐረ ሸቂየ፤ ተጨነቀ) መሣቀይ፤ ማስጨነቅ፤ ማስጠበብ፤ ባለመከራ ማድረግ። እለ ይሣቅዩኒ። ሣቀይዋ ወአልሐውዋ ፡-(መዝ ፡-፫። ራእ፲፰ ፡-፯)።
ሣባጥ ፡-(ዕብ ወሱር ወዐረ ሽባጥ) ስመ ወርኅ፤ የዕብራውያን ፲፩ኛ ወር የካቲት ፡-(ዘካ፩ ፡-፯)።
ሣቤቅ ፡-ጽፍቅ ዱር ዐጽቅ ሐረግ፤–ሰቢቅ ሰበቀ።
»ሣእሣእ ፡-መልስ ምላሽ፤ የሚበቃ አፍ የሚያሲዝ ቃል፤ ኀይልና ጣዕም ያለው የሚደነቅ፤ የነገር ጣዕም ለዛ፤ አጣጣል አሰካክ። ወሰው ውሽን፤ ዋሽንት ማለት ከዚህ ወጥቷል። ሞገሰ ቃሉ ወጣዕመ ነገሩ ወሣእሣአ አፉሁ። ወአንከሩ ሣእሣኦ። ሣእሣአ ቃልክሙ። ጥበብ ለርእይ አዳም ለሰሚዕ ፥ ጥዑም ለአፍ ሣእሣእ ለከናፍር ፥ ላሕይ ለአዕይንት ፡-(ሉቃ፬ ፡-፳፪። ፳ ፡-፳፮። ኢዮ፮ ፡-፳፮። ቀሌ)።
»ሣእሥአ ፡-(ተቀ ግ) ሰበቀለ ቀለጠፈ ቅልጥፍጥፍ አለ፤ ተባ ረታ፤ ሾለ ሰላ፤ ያንደበት።
ሣዕሥዐ ፡-ተባ ቀለጠፈ፤–ወሢእ ወሥአ፤ ሣእሣእ።
ሣዕር ፡-ሣር፤ ቡቃያ፤ የብር ያገዳ እኽል፤ የሚታጨድ ኹሉ፤ ገለባ ቈሻሻ፤ ድርቋ ፥ ድርቆሽ፤ ነፋስ የሚወስደው። ወብዙኅ ሣዕሩ ለውእቱ መካን። ሣዕረ ምድር። ሣዕር ዘያነሥኦ ነፋስ ፡-(ዮሐ፮ ፡-፲። ዘፀ፲ ፡-፲፪። ኢዮ፲፫ ፡-፳፭)።
፡-የስፌት ዕቃ፤ ማለቢያ ቄጆ ጮጮ። የውሃ የወተት የማር የቅቤ ስልቻ፤ ጠጕሩ ያልተነጨ ያልተመለጠ ቀርበታ። ሣዕረ ማይ። ሣዕረ ሐሊብ ፡-(ዘፍ፳፩ ፡-፲፬ ፡-፲፭ ፡-፲፱። መሳ፬ ፡-፲፱)።
ሣዕሮ ፡-(ትግሬ) ወገርት፤ ቅጠሉ ሣር የሚመስል።
ሣእን ፡-(ብ አሣእን። ዕብ ስኦን። ሱር ሴናእ) ጫማ ፥ መጫሚያ፤ የውስጥ እግር ቤዛ፤ ክፍት ወይም ኩፍ። ፈትሐ ሣእኖ። ከመ ይሑርዎ በአሣእን። ዘእንበለ አሣእን። ፍታሕ አሣእኒከ። ቶታነ። አሣእን ፡-(ሩት፬ ፡-፯። ኢሳ፲፩ ፡-፲፭። ፳ ፡-፪። ዘፀ፫ ፡-፭። ማር፩ ፡-፯)።
ሣውዕ ፡-(ዓን ዓት) ዝኒ ከማሁ፤ ካህን ፥ የሚጠብስ የሚያጤስ ፡-(ኩፋ ፡-፴ ፡-፵ ፡-፵፬)። በትረ ሌዋዊ ሣውዕ። ሚካኤል ሣውዕ ፡-(ደራሲ)።
ሣጹን ፡-(ናት። ዐረ ሻጹነት። ዕብ ጺንጼኔት፤ የሸክላ ዕቃ) ሣጥን፤ የልብስ የገንዘብ የሬሳ መክተቻ፤ ማኖሪያ፤ የንጨት የብረት። እምወርቀ መባእ ዘሣጹን። ገብረት ክልኤተ ሣጹነ ከመ ሣጹነ ምዉታን ወቦአት ውስተ አሐዱ፤ ወወልዳ ቦአ ውስተ ካልኡ ፡-(ፈ ፡-መ ፡-፲፯ ፡-፩። ዮሴፍ)።
ሤመተ አውሠይመተ ፡-(ሤመ) ሸመተ፤ እኽል ገዛ።
ሤራዪ ፡-(ዪት ይያን ያት፤ ረይት) የሚያሤር፤ ሤረኛ ዐድመኛ። የሚያልል ዐላይ፤ ቀለም አግቢ ፡-(ፍ ፡-ነ ፡-፴፮)።
ሤሬቅ ፡-(ዕብ ሦሬቅ። ጽር ሶሬክ) ጥሩ ወይን፤ ዘረ መልካም፤ አስካሉ ሕንባቡ ታላላቅ፤ ጣዕሙ ምቱቅ የኾነ። ባለብሉዮች ግን ስመ ሀገር፤ የወይን ቦታ ይሉታል። ተከልኩኪ ሤሬቀ። ወይን ኅሩይ ዘሤሬቅ። መረ ወይን ዘሤሬቅ ፡-(ኤር፪ ፡-፳፩። ኢሳ፭ ፡-፪። ደራሲ)።
ሤርዮ ዮት ፡-(ሤረየ ይሤሪ ይሤሪ) ማሤር፤ ሤራ መቍረጥ፤ ሰክተተንና ተሰካተየን እይ። ማለል ማቅለም፤ ቀለም ማግባት፤ መንከር ማራስ ማጥለቅ መዝፈቅ። ቀብዖ በሕጕሬ ወሤረዮ። ለእመ ተዐገለ ልብሰ ጸዐዳ ወሤረዮ። ፀምር ዘተጠምዐ በሤርዮ። ሤርዪዮን ለመላትሕኪ በአንብዕ ፡-(ጥበ፲፫ ፡-፲፬። ፍ ፡-ነ ፡-፴፭። መጽ ፡-ምስ። ማር ፡-ይሥ፲፫)።
ሤጥ ፡-(ጣት) ሸያጭ ዋጋ፤ ገንዘብ ገዢ ለሸያጭ የሚሰጠው። ዘብዙኅ ሤጡ። ዘእንበለ ሤጥ። ወሀቦ ሤጦ ለውእቱ መካን። ሤጠ ዚኣሁ። ሤጠ ግንዘት ፡-(ኢዮ፴፩ ፡-፳፬ ፡-መዝ ፡-፵፫። ፩ዜና ፡-፳፩ ፡-፳፭። ፍ ፡-ነ ፡-፳፯። ፵፪)።
ሥሁል ፡-(ላን ላት ህልት) ይቅር የተባለ ፥ ይቅርታ ያገኘ፤ የተማረ። ዕደው ሥሁላን። ኢሥህልት ፡-(ሢራ፵፬ ፡-፲። ሆሴ፩ ፡-፮። ፪ ፡-፫)።
ሥሂል ፡-(ሠሀለ ይሥህል ይሥሀል። ዐረ ሠሁለ) አው
ሥሒቅ ቆት ፡-(ሠሐቀ ይሥሕቅ ይሥሐቅ። ዕብ ሣሐቅ፤ ጻሐቅ። ዐረ ፀሒከ) መሣቅ መፍካት፤ ማሽካካት ፥ ከንፈርን መሰቅጠጥ ጥርስን መግለጥ፤ ከደስታና ከጨዎታ ብዛት ከማየት ከመስማት የተነሣ። ብፁዓን እለ ይበክዩ ይእዜ፤ እስመ ይሥሕቁ። አሌ ለክሙ እለ ትሥሕቁ ይእዜ፤ እስመ ትበክዩ። ኢትሥሐቅ ሎቱ ፡-(ሉቃ፮ ፡-፳፩ ፡-፳፭። ሢራ፴ ፡-፲)።
ሥኂት ቶት ፡-(ሥኅተ ይሥኅት ይሥኀት፤ አው ሠኀተ፤ ይሤኅት ይሥኅት። ዐረ ሠከተ። ዕብ ሣካት። ሱር ሥካት) መሠከት፤ ዝም ዕክም ጸጥ ሠክ ሹክክ ማለት፤ ለመስማትና ለማድመጥ፤ ለኈሰን እይ። ማረፍ ፥ ዕረፍት ማግኘት፤ ከመከራ። እሥኅት እምሕምዝ። ከመ ታዕርፍ ምድር ወትሥኀት እምኵሉ ሕማም። ይሥኅታ ምድረ ሰዶም ወገሞራ ፈድፋደ እምይእቲ ሀገር ፡-(ኢዮ፲፫ ፡-፲፫። ሱቱ ፡-ዕዝ፲፩ ፡-፵፮። ማቴ፲ ፡-፲፭)። በሥኅተ ፈንታ ተሥኅተ ይላል፤ አያሰኝም። ወበዝየኒ ኢተሥኅትኩ ፡-(ጸሎ ፡-ምና)።
ሥሒጽ ጾት ፡-(ሥሕጸ ይሥሕጽ ይሥሐጽ። ዐረ ሸሐጸ። ዕብ ሻሔጽ) መታበይ መኵራት፤ መድፈር አላቅሙ መናገር፤ መስደብ ማዋረድ ፥ መናቅ መሣለቅ። ከሰው ነገር መግባት ፥ ጥልቅ ማለት፤ እንደ ወገሜት ዝንብ። ሰሐጠንና ሠጠጠን እይ፤ የዚህ ጎሮች ናቸው። ይሥሕጹ ዘእንበለ ዐቅም። እለ እንበለ ጥበብ ሥሕጹ ላዕለ ትሥጉተ መድኀኒነ። ለምንት ይሥሕጹ ላዕለ ስብሐት መለኮት ፡-(ቄር ፡-ጰላ፤ ተረ)።
ሥህቡብ ፡-(ባን ባት ብብት) የሻገተ ፥ ሻጋታ፤ ብልሹ ዐመድማ። ኅብስት ሥህቡብ ወንቁዝ ፡-(ኢያ፬ ፡-፭። ኢዮ፰ ፡-፮)።
ሥህተ ፡-ሳተ፤–ስሒት ስሕተ።
ሥሕተ ፡-ሳተ፤–ስሒት ስሕተ።
ሥሕከ ፡-ሻከረ፤–ስሒክ ስሕከ።
ሥሕወ ፡-ተሳበ፤–ስሒው ስሕወ።
ሥሕጸት ፡-(ታት) መናቅ ማቃለል፤ ትዕቢት ድፍረት፤ ቅለት ጠለቅላቅነት፤ የስድብ ኀይለ ቃል። ቃለ ሥሕጸታት ያወፅእ እምአፉሁ። ወበዘያጽሕ ርእሶ እምሥሕጸታት ዘሰምዐ። ሥሕጸታት ላዕለ ክርስቶስ ፡-(ቄር ፡-እስት። ጰላ)።
ሥሉስ ፡-(ሳን ሳት ልስት) በቁሙ፤ የተሠለሰ ሦስት የኾነ፤ ሦስቲዮ ሥሉሴ። ፈትል ሥሉስ። ቅዱስ ሥሉስ። ሥሉሰ አካል ፡-(መክ፬ ፡-፲፪። ኪዳ። ደራሲ)።
ሥላሴ ፡-መሠለስ፤ ሥለሳ። ሦስትነት፤ ሦስት መኾን። ኀበ ሀለዉ ሠለስቱ ኤጲስቆጶሳት ይቄድሶ እግዚእነ ለሥላሴሆሙ ፡-(መጽ ፡-ምስ)። በቁሙ፤ የአካላት ስም፤ ሦስቶች፤ ሦስቶ ሦስቲዮ ሦስት ብቻ፤ ተውሳክና ሕጸጽ የሌለው ዘላለማዊ ሦስት። ባንድም በብዙም በወንድም በሴትም ይነገራል። ዓዲ ናቄርብ ለከ ዘንተ አኰቴተ ዘለዓለም ሥላሴ። አለብዉኒ ሥላሴ ቀትለ መስተቃትል መጽሐፍ። ሥላሴ እንተ እምቅድመ ዓለም ሀለወት ወኢኮነት በመዋዕል ፡-(ቅዳ ፡-ኪዳ። ደራሲ። ተረ ፡-ቄር፲፱)።
ሥላቅ ፡-(ቃት) በቁሙ፤ ሣቅ ጨዎት፤ ለግጥ ቧልት፤ ዋዛ ፈዛዛ፤ ዘበት ዘበታ ወዘበሬታ። ነገረ ሥላቅ። ሠሐቀ ወሥላቀ ኮንክዎሙ ፡-(ሢራ ፡-፳፫ ፡-፲፫። ኢዮ፲፯ ፡-፮)።
ሥላት ፡-ለግጥ ፌዝ፤–ሰልቶ ሰለተ።
ሥልሳ ፡-(ስሳ ስድሳ፤ ሰደሰ) ፪ ሠላሳ፤ ወይም ፫ ኻያ ፡-(ዐማርኛ)።
ሥልስ ፡-ሦስት ጊዜ፤ ሦስት እጅ፤ ሦስት ክፍል ሦስት ብቻ። ወሰገደ ሎቱ ሥልሰ። ትክሕደኒ ሥልሰ። ዘዘርዐ ስድሰ ያአቱ ሥልሰ ፡-(፩ነገ ፡-፳ ፡-፵፩። ማር፲፬ ፡-፸፪። ኢሳ፭ ፡-፲)። በቁሙ እሳት ያልነካው መባያ፤ እንደ ሰላጣ ያለ ሹሮና ድልኽ ቅባኑግ የመሰለው ኹሉ፤ ሦስትነት ያለው ፡-(ዐማርኛ)።
ሥልቅ ፡-ስመ ሀገር፤ በግዳድ የምትባል የባቢሎን ክፍል ፡-(ፍ ፡-ነ ፡-፬)።
ሥልጣናዊ ፡-ንጉሣዊ፤ የንጉሥ የጳጳስ ወገን፤ ሥልጣን ያለው ባለሙሉ ሥልጣን። የሹመት ሥራ ዳኝነት። አቅምተ ውሳንያት ሥልጣናውያት ዘፍትሕ ፡-(ፍ ፡-ነ ፡-፲፱)።
ሥልጣኔ ፡-በቁሙ፤ መሠልጠን ፥ ማሠልጠን፤ አሠለጣጠን ሥልጥንና፤ ሥልጡንነት ጠፍተኛነት፤ በሥራ በነገር።
ሥልጣን ፡-(ናት) [1]፡-በቁሙ፤ ችሎት መብት፤ ሹመት ጌትነት። ለሕይወት ወለሞት ሥልጣን ብከ። ከመ ዘሥልጣን ቦ። ወሀቦሙ ሥልጣነ። መኳንንት ወእለ በሥልጣናት ፡-(ጥበ፲፮ ፡-፲፫። ማቴ፯ ፡-፳፱። ፲ ፡-፩። ቅዳ ፡-ኪዳ)።
፡-ገዥ አለቃ፤ ንጉሥ መልአክ። ሥልጣናተ ሰማይ። ሥልጣናት ወኵሉ ኀይል። መናብርት ወሥልጣናት ፡-(ሔና፹፰ ፡-፰። ፩ጴጥ ፡-፫ ፡-፳፪። ዲድ)።
[2]፡-(ብ ሠላጢን) ሹል ስል መውጊያ፤ የንጨት የብረት፤ ሽብዳ ዐንካሴ ምዥራጥ። ሠላጤ ማለት ከዚህ ወጥቷል፤ ኹሉም ዐማርኛ ነው።
ሥሙር ፡-(ራን ራት ምርት) የተሠመረ፤ የተወደደ ወብ መልካም። ሥሙር ወኅሩይ። ሥሙር ለንጉሥ። ዐጽቀ በለስ ሥሙር ጥቀ። ምድር ሥምርት ፡-(ሮሜ፲፪ ፡-፩። ምሳ፲፬ ፡-፫። ኤር፳፬ ፡-፪። ሚል፫ ፡-፲፪)።
ሥምረት ፡-(ታት) መውደድ፤ መወደድ፤ አወዳደድ ውድነት፤ እሺታ ውዴታ፤ ውድ ቍርጥ ፈቃድ። ገበርኩ ቅድሜከ ሥምረተከ። ሥምረቱ ለአምላክነ ላዕሌነ። እንበለ ፈቃዳ አው በሥምረተ ልባ። ከመ ይኩን ቦቱ ሥምረት ፡-(ኢሳ፴፰ ፡-፫። ባሮ፬ ፡-፬። ፈ ፡-መ ፡-፭ ፡-፲፫። ፍ ፡-ነ ፡-፳፬ ፡-፪)።
ሥሡዕ ፡-(ዓን ዓት ሥዕት) የሣሣ፤ ሥሡ፤ ሆዳም፤ ሥሥታም። ብእሲ ሥሡዕ ዘኢይጸግብ። ሥሡዐ ልብ። ሥሡዓን በላዕያን ፡-(ሢራ፴፬ ፡-፳። መዝ ፡-፻። መቃ)።
ሥሣዔ ፡-መሣሣት፤ መሠሠት፤ ሥሥ ሥሡ መኾን፤ ሥሥት፤ ሥሡነት።
ሥሥዕት ፡-በቁሙ፤ ሥሥት፤ ንፍገት ሆዳምነት። እመ ኢይፈደፍድ ሥሥዕትከ። ምርዓት ወዝሙት ወሥሥዕት። ያበዝኆ ለገብጥ ሥሥዕት፤ ብዙኃን እለ ቀተሎሙ ሥሥዕት ፡-(አፈ ፡-ተ፫። ቀሌ። ሢራ፴፯ ፡-፴ና ፡-፴፩)።
ሥረው ፡-ሥሮች፤ ዥማቶች። ይየብስ ሥረዊሁ። እንተ በምድር ሥረዊሃ ፡-(ኢዮ፲፰ ፡-፲፮። ሆሴ፱ ፡-፲፮)።
ሥሩሕ ፡-(ሓን ሓት ርሕት) ያማረ የበጀ፤ የቀና የሰላ፤ የተከናወነ። ከመ ሥሩሐ ይኩን ፍኖትከ። ለገባሬ ሠናይ ኵሉ ፍናዊሁ ሥሩሕ ፡-(ጦቢ፬ ፡-፲፱። ፈላስ)።
ሥሩኅ ፡-(ኃን ኃት ኅት) የበራ፤ ብሩህ፤ ጽዱል።
ሥሩዕ ፡-(ዓን ዓት ርዕት) የተሠራ፤ የተበጀ፤ የተዘጋጀ፤ የቀረበ የተጣፈ የተወሰነ፤ የቆመ የተተከለ። ጽጌ ረዳ ሥሩዕ። ማእድ ሥሩዕ። ሥሩዕ ወዕቁም። ወሥሩዕ ከመ ወርኅ ለዓለም ፡-(አስቴ፩ ፡-፮። ሕዝ፳፫ ፡-፵፩። ፩ቆሮ ፡-፲፬ ፡-፵። መዝ ፡-፹፰ )።
፡-የተመረጠ፤ የተሾመ፤ ኅሩይ ሥዩም፤ ጽዉዕ። ሥሩዕ ጴጥሮስ፤ ሥሩዕ ጳውሎስ ፡-(ቄር)።
ሥሩጽ ፡-(ጻን ጻት ርጽት) የሠረጸ፤ የወጣ፤ የበቀለ፤ የለመለመ፤ ለምለም ጨፌ፤ መስክ። ወተርእየት ማይ እምዘቀዲሙ ርግዕተ፤ ወሥርጽተ ምድር ይብስት ፡-(ጥበ፲፱ ፡-፯)።
ሥራሕ ፡-ድካም፤–ሰሪሕ ሰርሐ።
(ጥ) ሥራዕ ፡-(ዓት። ዐረ ሺራዕ) የመርከብ ሸራ፤ መጋረጃ፤ መዝርዕ። አውረዱ ሥራዐ። ወሰቀሱ ሥራዐ ዘይንእስ። ሐመር እንተ አልባቲ ሥራዓት ፡-(ግብ፳፯ ፡-፲፯ ፡-፵። ማር ፡-ይሥ፬ ፡-፪)። በመልሕቅ ፈንታ ሥራዕ፤ ሥራዓት ይላል፤ የመላሽ ስሕተት ነው። ወአልዐሉ ሥራዓት ፡-(ግብ፳፯ ፡-፲፫)።
ሥራይ ፡-(ያት) መድኀኒት፤ የሚዋጥ የሚላመጥ፤ የሚጠጣ የሚቀባ። ሥራይ ዘቀብዕዎ። ይጠይዕዎ ሥራየ። ዐቃቤ ሥራይ ፡-(ጥበ፲፮ ፡-፲፪። ኢሳ፩ ፡-፮። ሢራ፲ ፡-፲)።
፡-ጥንቈላ፤ ሟርት፤ ምትሀት። ዘሥራይ ብእሲሁ። እለ ሥራይ። ሰብአ ሥራይ። መጽሐፈ ሥራያት ፡-(ግብ፰ ፡-፱። ራእ፳፪ ፡-፲፭። ዘፀ፱ ፡-፲፩። ፈ ፡-መ ፡-፲፭)።
ሥርቀት ፡-መውጣት፤ አወጣጥ፤ መታየት። ሥርቀተ ፀሓይ ሥርቀተ ከዋክብት። ሥርቀተ ቤዝ ፡-(ዮሴፍ። ጥበ፲ ፡-፲፯። ገድ ፡-ተክ)።
ሥርቅ ፡-ስርቆት፤–ሰሪቅ ሰረቀ።
ሥርቆ ፡-ሸምቀቆ፤ ገመድ፤ ወጥመድ። ቆቃሕ ተሠግረ በቈጽለ አሥርቆ ፡-(በቈጽለ ሥርቆ) ቈጽል ልጡ ገመዱ፤ ሥርቆ ውሉ ሸምቀቆው ፡-(ሢራ፲፩ ፡-፴)።
ሥርናይ ፡-(ያት) ስንዴ፤ የስንዴ ወገን፤ ዐጃ። አመ ማእረረ ሥርናይ። እክለ ሥርናይ። ኅጠተ ሥርናይ። ሥርናያት ፡-(ዮዲ፪ ፡-፳፮። ሢራ፴፱ ፡-፳፮። ዮሐ፲፪ ፡-፳፬። ስንክ ፡-ጥር፳፱።
፡-ስንዴ፤–ሥዒር ሥዕረ።
ሥርዐት ፡-(ታት) መሥራት፤ መሠራት፤ አሠራር፤ ሥራት፤ ደንብ፤ አገባብ፤ ሕግ ትእዛዝ፤ ዐዋጅ ፍርድ ልማድ፤ የሥራ መንገድ። መኰንን ለባዊ ይገብር ሥርዐተ። ዐቃቤ ሥርዐት። ሥርዐተ ዲያቆን ዐቀበ ወኢተዐደወ። ንሕነ ወለጥነ ሥርዐተ። ንሥተተ ሥርዐተ ሰብሳብ። ሥርዐተ ምሥዋዕ። ሥርዐተ አውራኅ። ሥርዐተ አባ ጳኵሚስ ፡-(ሢራ፲፮ ፡-፳፮። ፩ዜና ፡-፲፰ ፡-፲፭። መዋሥ። አፈ ፡-ተ፰። ጥበ፲፬ ፡-፳፮። ዕብ፱ ፡-፬። ኩፋ ፡-፬። ሥር ፡-ጳኵ)።
፡-መኖር፤ አናዎር፤ ኑሮ። ይኄይስ ሥርዐተ ብሕትውና እምሥርዐተ ማኅበር። ቦ ብዙኃን እለ ያስተካብዱ ሥርዐተ ንዴት ፡-(ፊልክ ፡-፩። አፈ ፡-ተ፲፰)።
ሥርወ ሕሩም ፡-የሹልዳ ዥማት ፡-(ዘፍ፴፪ ፡-፴፫)።
ሥርዋጽ ፡-ሽብልቅ፤–ስርዋጽ።
ሥርው [1]፡-(ዕብ ሾሬሽ። ሱር ሽርሻ። ዐረ ሢር) ሥር ዥማት። ወደየ ሥርወ። አኀዘ ሥርወ። ዘኀጺን ሥርወ ክሣድከ። ይሌሊ ሥርወ እመሌሊት ፡-(ሱቱ ፡-ዕዝ፰ ፡-፳፯። ኩፋ ፡-፴፯። ኢሳ፵፰ ፡-፬። ዕብ፬ ፡-፲፪)። ሥርውና ዥማት ልዩ ሲኾን፤ በመትን ፈንታ ሥርው ይላል፤ የመላሽ ስሕተት ነው።
[2]፡-ሥሮች፤ ዥማቶች። ይየብስ ሥረዊሁ። እንተ በምድር ሥረዊሃ ፡-(ኢዮ፲፰ ፡-፲፮። ሆሴ፱ ፡-፲፮)።
[3]፡-መዠመሪያ፤ መነሻ፤ መውጫ፤ መብቀያ። ሥርዋ ለጥበብ ፈሪሀ እግዚ ፡-(ሢራ፩ ፡-፳። ጥበ፲፭ ፡-፫። ፩ጢሞ ፡-፮ ፡-፲)።
፡-የትንቢት መነሻ፤ ትንቢት አንቀጽ የሚነሣባቸው ፊደላት፤ የተአነ። የ ለ፫ መደብ፤ ተ ላ፭፤ አ ለአነ፤ ነ ለንሕነ አሥራወ ትንቢት ይባላሉ፤ የይቤንና የየራሳቸውን አፈታት ተመልከት።
[4] ፤ ዘር፤ የትውልድ ምንጭ፤ ሐረግ። ሥርወ እሴይ። ሥርወ ዳዊት። ወአንተሰ እምነ ዐቢይ ሥርው። ሥርውኪ ወዘመድኪ ፡-(ኢሳ፲፩ ፡-፩ና ፡-፲። ራእ፭ ፡-፭። ጦቢ፭ ፡-፲፬። ሕዝ፲፮ ፡-፫)።
[5] መዠመሪያ መጽሐፍ፤ ሐዲስ የወጣ፤ የተፈጠረ፤ ረቂቅ፤ መዝገብ፤ ቅዱስ መጽሐፍ፤ ብሉይ ሐዲስ። መጽሐፈ ሥርው ፡-(ዮሴፍ። ፍ ፡-ነ ፡-፶፩)።
[6]፡-(ዋን ዋት ሩት) የተነቀለ ንቁል፤ የጠፋ ጥፉ፤ የተተከለ፤ ሥር የያዘ፤ የሰደደ።
ሥርየት [1]፡-ማለል፤ መታለል፤ መነከር ማደፍ ፡-(ዘፀ፳፭ ፡-፭። ፴፫ ፡-፳፫)።
[2]:-በቁሙ፤–ሰርይ ሰረየ።
ሥርጸት ፡-መሥረጽ፤ መውጣት፤ መብቀል፤ አበቃቀል፤ ቡቃያነት ፡-(መጽ ፡-ምስ)።
ሥቁይ ፡-(ያን ያት ቅይት) የተሣቀየ፤ የተጨነቀ፤ ሥቃይ የጸናበት። ወትከውን ጽዑረ ወሥቁየ በኵለ መዋዕል ፡-(ዘዳ፳፰ ፡-፴፫)።
ሥቃይ ፡-(ያት) በቁሙ፤ ጭንቅ፤ መከራ ፥ መቅሠፍት፤ ግፍ ቅጣት። ኣበዝኆ ለሕማምኪ ወለሥቃይኪ። ወሣቀዮ ለፈርዖን ዐቢየ ሥቃየ። ይትዔገልዎሙ፤ ወይቀንይዎሙ በሥቃይ። ሥቃያተ ኵነኔ ፡-(ዘፍ፫ ፡-፲፮። ፲፪ ፡-፲፯። ዘፀ፩ ፡-፲፫ና ፡-፲፬። አፈ ፡-ድ፮)።
ሥቅሡቅ ፡-(ቃን ቃት ሥቅት) የተበሳሳ፤ የተነዳደለ። መሳክዊሁ ሥቅሡቅ እስከ መልዕልት። ወመሳክው ሠናያን ወሥቅሡቃን ፡-(፫ነገ ፡-፯ ፡-፮። ገድ ፡-ላሊ)።
ሥቡሕ ፡-(ሓን ሓት ብሕት) የሠባ የወፈረ፤ ወፍራም ደንዳና። ከመ ዘእምሥቡሕ። ሥቡሓኒሆሙ። ልሕድ ወሥብሕት ፡-(መዝ ፡-፷፪። ዘፍ፬ ፡-፬። ኢሳ፴፯ ፡-፩)።
ሥባጥ ሥበጥ ፡-ሽባጥ ሽብልቅ፤ ሠላጤ ወሽመጥ፤ ፡-(ዐማርኛ)። ጕርሻ ፥ ምግብ፤ የበሰለ የተዘጋጀ፤ ወይም ገንዘብ ፥ የገንዘብ ሥንቅ፤ የምግብ መግዣ። ሥበጠ መብልዕ። ኤልያስ በልዐ ሥበጠ ኅብስት ዘወሀቦ መልአከ እግዚ፤ ወሖረ በኀይለ ውእቱ እክል አርብዓ መዓልተ ወአርብዓ ሌሊተ ፡-(መጽ ፡-ምስ)።
ሥብሐት ፡-፥ ሥባት፤ ሥብነት ፥ አሠባብ አወፋፈር ፥ ወፍር ድንዳኔ።
ሥብሕ ፡-(ሓት) ሥብ ጮማ ሞራ፤ ትርፍ ነጭ ሥጋ ላት። ወፍር ድንዳኔ። ለመሧዕት የሚቀርብ ጥሩ ነገር ኹሉ ሥብሕ ይባላል። ዘእንበለ ይጢስ ሥብሕ። ሥብሐ ከርሡ ወሥብሐ ኵሊቱ። ሥብሐ ሥርናይ ፡-(፩ነገ ፡-፪ ፡-፲፭። ዘፀ፳፱ ፡-፲፫። መዝ ፡-፹)።
ሥቱር ፡-(ራን ራት ትርት) የተሠነተረ፤ ግርፍ፤ ገጣባ።
ሥትረት ፡-መቅደድ፤ መቀደድ፤ አቀዳደድ፤ ግርፋት፤ ቍስል፤ ሰንበር።
ሥኑይ ፡-ያማረ የተዋበ ውብ። ሥኑይ ወርጉፍ በሜላት። ወከመ ዝ ቤቱ ሥኑይ ወአዳም። ወሢመትክሙኒ ድልው ወሥኑይ ፡-(አስቴ፩ ፡-፮። መቃ ፡-ገ፫። ቄር ፡-፩)። በሥኑይ ፈንታ መሠንይ ይላል፤ ፍችው አንድ ነው። መሠንየ እንስሳ። መሠንየ ማእሰር። መሠንየ ቃለ ትንቢት ፡-(፩ነገ ፡-፲፭ ፡-፱። ሢራ፳፪ ፡-፲፮። አርጋ ፡-፭)።
ሥን ፡-(ናት) [1]፡-መልክ፤ ውበት፤ ደም ግባት፤ ጌጥ ሽልማት፤ ጥራት፤ ጥዳት፤ ጠፍታ። በሥንከ ወበላሕይከ። ሥነ ስብሐቲሁ። ሥነ ዜና ዘለዓለም። ሥና ለብእሲት። ኢትዘኀር በሥነ አልባሲከ ፡-(መዝ ፡-፵፬። ፵፱። ሢራ፱ ፡-፰። ፲፩ ፡-፬)።
[2]፡-መልካምነት፤ ደግነት፤ በጎነት። ሥነ ምግባሩ። ሥነ ግዕዙ ፡-(ሢራ፮ ፡-፲፭። ያዕ፫ ፡-፲፫)።
[3]፡-ፍጥረት፤ አዝርዕት አትክልት፤ እንስሳት አራዊት። ምስጢሩ ጌጥ ሽልማት ካለው ይገባል። እሳት አኅለቀ ሥነ ገዳም። ወሥነ ገዳምኒ ኀቤየ ሀሎ ፡-(ዮኤ፩ ፡-፲፱ና ፡-፳። መዝ ፡-፵፱)።
ሥንቅ ፡-በቁሙ፤ የመንገድ መሣሪያ፤ ልብስ ምግብ፤ ገንዘብ። ወአስተዳለወ ሥንቀ ለፍኖት። ወሀቦ ክልኤተ ምእተ መካልየ ወርቅ ከመ ይኩን ሥንቀ ለፍኖት። ቍርባን ቅዱስ ሥንቀ ነፍስ ፡-(ኩፋ ፡-፵፪። ጦቢ፭ ፡-፲፮። ታሪ ፡-ነገ። ፈ ፡-መ ፡-፳፮ ፡-፭)።
ሥንት ፡-(ዕብ ሻይን፤ ሽታን) ሽንት፤ የሽንት ውሃ ፈሳሽ ፥ የመጠጥ ሐሠር ከሆድ የሚወጣ። እኂዘ ሥንት። ይስተዩ ሥንቶሙ ፡-(ፈላስ ፡-ገ፴፯። ኢሳ፴፮ ፡-፲፪። ፬ነገ ፡-፲፰ ፡-፳፯)። ባማርኛ ግን የቍጥር ጥያቄ ይኾናል፤ ስንት ፥ በቁሙ ምን ያኽል። ስፍንና እስፍንቱን እይ።
ሥዑል ፡-(ላን ላት ዕልት) የተሣለ፤ የተቀረጸ፤ የተፈጠረ ፍጡር። ሥዑል ዲበ አረፍት። ታስተርእዮሙ ሥዕልታ። ህየ ሀሎ መልክአ ገጹ ሥዑል። እለ ሥዑላን በነደ እሳት ፡-(ሕዝ፰ ፡-፲። ጥበ፮ ፡-፲፯። ቅዳ። ሳታት)።
ሥዑር ፡-(ራን ራት ዕርት) የሻረ፤ የዳነ። የበቀለ፤ የለመለመ ለምለም፤ ሣርማ ሣራም፤ ምቹ ቦታ። ብሔር ሥዑር። መካን ሥዑር ፡-(መዝ ፡-፳፪። ኢሳ፴ ፡-፳፫። ግንዘ)። በሥዑር ፈንታ መሥዕር ይላል፤ አያሰኝም።
ሥኡብ ፡-(ባን ባት እብት) ያደፈ ፥ የተዳደፈ፤ እድፋም ርኩስ ፡-(ዘሌ፲፭ ፡-፲፮። ፲፰ ፡-፴፪። ሐጌ፪ ፡-፲፫። ኩፋ ፡-፴፪)። ቤትኩ ሥኡብየ። እመ ቦ ሥኡብ ወዘኢኮነ ንጹሕ። ርኩስ ወሥኡብ ውእቱ። ሥኡባነ ነፍስ ፡-(ጦቢ፪ ፡-፬። ቅዳ። ቀሌ። አርጋ ፡-፬)።
ሥኡን ፡-(ናን ናት እንት) የተጫማ፤ ጫማ የለበሰ፤ ወይም የተለበሰ። ሥኡናን እገሪሆሙ ወግልቡባን አርእስቲሆሙ ፡-(ታምረ ማር)።
ሥዒል ሎት ፡-(ሠዐለ ይሥዕል ይሥዐል። ዕብ ያጻር። ዐረ ጸወረ) መሣል፤ ማስመሰል፤ መንደፍ መበገር። መፍጠር፤ ማስገኘት፤ መቅረጽ። ንሣእ ግንፋለ ወሠዐል ውስቴቱ ሀገረ ኢየሩሳሌም። ናሁ በእደውየ ሠዐልኩ አረፋተኪ። አዘዘ ይግበሩ ጻሕለ ዘወርቅ ወይሥዐሉ ላዕሌሁ ሥዕለ ምድረ ግብጽ በምልኣ። ለዛቲ ሥዕል ሠዐላ ሉቃስ ወንጌላዊ፤ ሣለ ፡-(ሕዝ፬ ፡-፩። ኢሳ፵፱ ፡-፲፭። ዮሴፍ። ስንክ ፡-መስ፲)። ዘይሥዕሎሙ፤ለሕፃናት በውስተ ማሕፀን። እግዚ ፈጠረ ሥጋክሙ ወመንፈሰክሙ፤ ወሠዐለክሙ በክሂሎቱ ፡-(ድጓ። ዮሴፍ)።
ሥዒር ሮት ፡-(ሥዕረ ይሥዕር ይሥዐር። ዕብ ሣዐር ራደ ታወከ) መብቀል፤ ቡቃያ መኾን፤ መለምለም፤ ማደግ። እምነ ዝናም ይሥዕር ሐመልማል ፡-(፪ነገ ፡-፳፫ ፡-፬)።
፡-መሻር መዳን፤ መፈወስ መታደስ፤ ባለጤና መኾን፤ የቍስል የደዌ ፡-(ዐማርኛ)።
ሥኢብ ቦት ፡-(ሥእበ፤ ሠአበ ይሥእብ ይሥአብ። ሱር ወዕብ ሣኤብ) ማደፍ ፥ መርከስ፤ የሩካቤ የሕልመ ሌሊት የገሲሰ በድን። ወለእመ ሐለመ ኤጲስቆጶስ አንስተ ኢይቅረብ ወኢይትከነስሂ፤ ወአኮ ዘሥእበ አላ በእንተ ክብረ ምሥዋዕ ፡-(ኪዳ ፡-ገ፲)።
ሥዒዕ ዖት ፡-(ሠዕዐ ይሥዕዕ ይሥዐዕ። ዐረ ሸዐ፤ ነቃ፤ ተበተነ) መግፈፍ፤ መቅረፍ፤ ማብነን መበተን፤ ለማጥራት ለመግለጥ፤ የዐይን የብሌን። ሠዐየን ተመልከት፤ ከዚህ ጋራ አንድ ነው።
ሥዓዕ ፡-ግፋፊ፤ ግልፋፊ፤ ብናኝ፤ ርጋፊ። ወድቀ እምነ ምጋሁ ሥዓዐ ቅርፍት ፡-(አዋል)።
ሥዕል ፡-(ላት) በቁሙ፤ መልክ፤ የመልክ ጥላ፤ አምሳል፤ ንድፍ ቢጋር፤ በውሃ በመጽሔት፤ በጥልፍ በስፌት፤ ወይም በቀለም በወረቀት ገዝፎ ተጥፎ፤ ከጽቡር ከእብን ከዕፅ ከማዕደን ታንጦ ተቀርጦ፤ ተሸልሞ አጊጦ የሚታይ፤ የሚዳሰስ ነገር። ሥዕለ ኪሩብ። ሥዕለ ቤት። ሥዕለ ጣዖት። ሥዕላት ወምስላት። ይረቅሙ ሥዕላ ዲበ አልባሲሆሙ። አስተርአየ በአየረ ሰማይ ሥዕለ መስተጽዕናን በአፍራሰ እሳት ፡-(፫ነገ ፡-፳፯። ሕዝ፵፫ ፡-፲፪። ዲድ ፡-፳፭። አፈ ፡-ድ፲፪። ዮሴፍ)።
»ሥእሡእ ፡-(ኣን ኣት ሥእት) የሰበቀለ ስብቅል፤ ትብ ቀልጣፋ፤ በሊኀ ልሳን። ከናፍሪሁ ጥዑም ወአፉሁ ሥእሡእ ፡-(ደራሲ)።
»ሥእሣኤ ፡-መሰብቀል፤ አሰበቃቀል፤ ስብቀላ ቅልጠፋ፤ ያንደበት።
»ሥእሥእና ፡-ስብቅልነት፤ ቀልጣፍነት።
ሥዕር ሥዕርና ፡-ሥዕርና፤ ፡-(ዕብ ሥዖራ። ዐረ ሸዒር) ገብስ፤ የገብስ ዐይነት ፥ ኹሉ፤ ጠመዥ ሌላውም።
ሥዕርት ፡-(ታት። ዕብ ሤዓር፤ ሣዐር። ሱር ሣዕራ፤ ሥዓርታ። ዐረ ሸዕር፤ ሸዕረት) ጠጕር፤ የሥጋ ሣር፤ ቀጫጭን ደቃቅ፤ በቍርበቱ ላይ በዝቶ ጽፍቅ ኹኖ የሚበቅል፤ ራስን ገላን የሚሸፍን፤ የሚያሞቅ የሚያደምቅ፤ ጋማ ጭራ። በዝኀ ሥዕርትኪ። ወኢአሐቲ ሥዕርትነ። ሥዕርት ቀጣን ፡-(ሕዝ፲፮ ፡-፯። ዲድ ፡-፳፭። ፲፫ ፡-፴)።
ሥእበት ፡-(ታት) ማደፍ መርከስ፤ ርኵሰት ርስሐት፤ እድፍ። ዘኢኮነ ንጹሐ እምነ ሥእበቱ ዘሌሊት። አልቦቱ ሥእበት። ዘበሥእበት ፡-(ዘዳ፳፫ ፡-፲፩። ዕብ፲፫ ፡-፬። ቀሌ)።
ሥእነ [1]፡-ሳነ ተሳነ፤–ስኢን ስእነ።
[2]፡-ሠአነ ፡-(ሰንአ። ዕብ ሳአን) ተጫማ ፥ ለበሰ፤ እግሩን ከመጫሚያ ሰካ አገባ አዋደደ አሰማማ። ሰንአን እይ፤ የዚህ ጎር ነው። መጽሐፍ ግን በሥእነ ፈንታ ተሥእነ ተሠአነ ይላል፤ አያሰኝም። ተሥእነት ኤሣእኒሃ። ተሠአን አሣእኒከ። ተሥኢነክሙ ኀይለ ወንጌል ፡-(ዮዲ፲ ፡-፬። ግብ፲፪ ፡-፰። ኤፌ፮ ፡-፲፭)።
ሥዕይ ዮት ፡-(ሥዕየ፤ ሠዐየ ይሥዒ ይሥዐይ) ማዝራት፤ መበተን፤ መመሸን፤ የምርት። ማጥፋት፤ ማባከን፤ የገንዝብ። ከመ ነፋስ ይሥዕዮሙ። እለ ጼና ጢስ ፍጉገ ይሥዕዩ። ትሰድዶሙ በቃልከ ወትሥዕዮሙ በመንፈሰ ኀይልከ ፡-(ጥበ፭ ፡-፳፬። ፲፩ ፡-፲፱ ፡-፳፩)።
ሥኩር ፡-(ራን ራት ክርት) የተገዛ ግዝ፤ የተከራየ የክራይ። መላጺ ሥክርት ፡-(ኢሳ፯ ፡-፳)። ምላጭ የተባለች ሰይፍ ናት ፡-(ሕዝ፭ ፡-፩)። የሻከረ ሸከራ።
ሥውየት ፡-መሸት ፥ መብሰል፤ አሻሻት አበሳሰል፤ እሸትነት። ሰብዐቱ ሰብል ዘሠዊት ሠረጹ እምአሐዱ ብርዕ፤ ወንኩር ሥውየቶሙ ፡-(ዮሴፍ)።
ሥዉጥ ፡-(ጣን ጣት ውጥ) የተመለሰ፤ ምልስ ቅልስ።
ሥዉዕ ፡-(ዓን ዓት ውዕት) የተሠዋ ፥ መሥዋዕት የኾነ።
ሥዩም ፡-(ማን ማት ይምት) የተሾመ ሹም፤ ንቡር ድልው፤ ቅምጥ ዝግጁ። ሥዩማነ ቤተ እግዚ። ኤጲስቆጶሳት ወባዕዳን ሥዩማን። በእንተ ተስፋክሙ ዘሥዩም በሰማያት። እስመ ዝንቱ ሥዩም ለድቀቶሙ ወለተንሥኦቶሙ ፡-(ግብ፲፪ ፡-፩። ዲድ ፡-፮። ቆላ፩ ፡-፫። ሉቃ፪ ፡-፴፬)።
ሥዩጥ ፡-(ጣን ጣት ይጥ) የተሼጠ የተዋጀ፤ ውጁ መሼጦ። አንሰ ሥዩጥ ለኀጢአት። ወለእመ ኮነ ነውር በሥዩጥ ፡-(ሮሜ፯ ፡-፲፬። ፍ ፡-ነ ፡-፴፫ ፡-፮)።
ሥጉር ፡-(ራን ራት ግርት) ከወጥመድ የገባ ፥ የተያዘ፤ የተዘጋ ዝግ፤ የተዘጋበት ፥ የተሸጐረበት።
ሥጋ ፡-(ብ ሥጋው፤ ዋት፤ ሥጋት) በቁሙ፤ ግዙፍ ልሕሉሕ ደማም ፥ ደመ ነፍሳም፤ የሕያዋን ገላ ፥ የኀሙስና የዐርብ ፍጥረት፤ ባጥንትና ነሥር በዥማት የጸና። ለማግሰኞም ፍጥረት ይበገራል፤ ደመወን እይ። አምላክ ለኵሉ ዘሥጋ። እደመስስ ኵሎ ዘሥጋ። እስመ ሥጋ እሙንቱ ፡-(ኤር፴፱ ፡-፳፯። ዘፍ፮ ፡-፲፯። ኩፋ ፡-፭)።
፡-ሰው ፥ የሰው ልጅ ፥ የአዳም ዘር፤ በሥጋነቱ ላይ ነፍስ ያለችው ነባቢና ቀዋሚ ፍጥረት፤ አካሉ ገላው እንደ ዐምድ የቆመ እንደንስሳት ያልተጋደመ፤ ከሞተም በኋላ እንደ ግንድና እንደ ሌላው ነገድ ወድቆና ተጋድሞ ፈርሶ በስብሶ የማይቀር ፥ ረቆ ታድሶ የሚነሣ። እሰውጥ እምነ መንፈስየ ዲበ ኵሉ ዘሥጋ። ቃል ሥጋ ኮነ፤ ወኀደረ ላዕሌነ። ዘይሔድስ ሥጋነ ትሑተ ወይሬስዮ አምሳለ ሥጋ ስብሐቲሁ ፡-(ዮኤ፫ ፡-፩። ዮሐ፩ ፡-፲፬። ፊልጰ፫ ፡-፳፩)።
፡-ወገን ነገድ ፥ የቅርብ ዘመድ ፥ ልጅ ሚስት። ፡-(ተረት) የሥጋ ቍራጭ ያጥንት ፍላጭ። ሰብኡ ወሥጋሁ። አሐዱ ሥጋ ንሕነ በክርስቶስ። ይኩኑ ክልኤሆሙ አሐደ ሥጋ ፡-(ዘሌ፲፰ ፡-፮። ሮሜ፲፪ ፡-፭። ፩ቆሮ ፡-፮ ፡-፲፮)።
፡-ሬሳ በድን አስክሬን ፥ ነፍስ የተለየችው ፥ የሞተ የታረደ። ግድፍ ሥጋየ ላዕለ ሥጋቲሆሙ። እላንቱ ሥጋት ኢይቢታ ዲበ መሳቅሊሆን። ይትጋብኡ ሥጋት እለ ኮኑ ከመ ጸበል። ሥጋ ዘመሥዋዕት። ዐቃቤ ሥጋ ፡-(ዮሴፍ። ዮሐ፲፱ ፡-፴፩። ቀሌ። ሕዝ፵፩ ፡-፵፫። ፩ነገ ፡-፳፰ ፡-፪)።
፡-ግዘፍ፤ ግዙፍንት። እስመ አኮ አምሳለ ኀጺን ዘይትሜሰል በኵለንታሁ ትስብእት፤ አላ በሥጋ ባሕቲቱ ፡-(ሃይ ፡-አበ)።
ሥጋዊ ፡-(ዊት ውያን ያት) በቁሙ፤ የሥጋ ፥ ሥጋማ ሥጋም ግዙፍ። ኵነኔ ዝሙት ሥጋዊ ወመንፈሳዊ። አበው ሥጋውያን። ኀጣውእ ሥጋውያት ፡-(ፍ ፡-ነ ፡-፵፰። አፈ ፡-ድ፳፱። ፈ ፡-መ ፡-፭ ፡-፪)። በጋማች ፥ ሥጉያ ሥጋ ሸያጭ ባለሥጋ፤ ሥጋ ቤት ሥጋ መልከኛ።
ሥጋዌ ፡-ሥጋነት፤ ሥግና ሥጋ መኾን፤ የሥጋ ባሕርይ፤ መወፈር መግዘፍ። ምስጢረ ሥጋዌ። ዓመተ ሥጋዌ። ኢየሱስ ክርስዮስ ፍጹመ ትስብእት ወሥጋዌ ፡-(ደራሲ)። በሥጋ ፈንታ ሥጋዌ ይላል፤ የጣፊ ስሕተት ነው፤ አያሰኝም። ምስለ ሥጋዌ ዘነሥአ እምኔሃ ፡-(አርጋ ፡-፪)።
ሥግረት ፡-መሥገር፤ ሥግሪያ። መሻገር መራመድ፤ አረማመድ፤ እርምጃ፤ አካኼድ እግር አነሣሥ። ኈለቈ ኵሎ ሥግረትየ ፡-(ኢዮ፴፩ ፡-፬)።(662) ሥግረት፤ መዝጋት፤ መዘጋት ፥ ዝግነት፤ አያያዝ አከባበብ።
ሥግው ፡-(ዋን ዋት ጉት) ሥጋ የኾነ፤ ሥጋ የለበሰ፤ ሥጋማ ግዙፍ። እስመ እግዚ ሥግው ውእቱ። አብ ዘኢሥግው ፡-(ቄር ፡-ጰላ። አፈ ፡-ድ፭)።
ሥጠት ፡-(ታት) (መቅደድ፤ መቀደድ አቀዳደድ ቀዳድነት፤ ቅድ ሥንጥቅ። ሥጠተ ልብስ ብሉይ፤ ወይከውን ሥጠቱ ዐቢየ ፡-(ማቴ፬ ፡-፲፮)።
ሥጡቅ ፡-(ቃን ቃት ጥቅት) የተሠነጠቀ፤ ሥንጥቅ ሠንጣቃ ቀዳዳ ሥጡቅ ጽፍሩ እማእከሉ። ምብኳሐ ነሃቢ ሥጡቅ ፡-(ሥጡጥ) ፡-(ዘሌ፲፩ ፡-፫። ኢዮ፴፪ ፡-፲፱)።
ሥጡይ ፡-(ያን ያት ጢት) የጸነነ የተሳበ፤ የተለወጠ ፡-(ሄርማ)።
ሥጡጥ ፡-(ጣን ጣት ጥጥ) የተቀደደ፤ ቀዳዳ ሠንጣቃ ክፍት። ሥጡጥ አልባሲሁ። ሥጡጥ መታክፉ በሰይፍ። ዝቅ ሥጡጥ ይለብስ ሥጡጠ ወአጽርቅተ ኵሉ ነዋሚ ፡-(፩ነገ ፡-፬ ፡-፲፪። ስንክ ፡-ጥር፪። ኢያ፱ ፡-፪። ምሳ፳፫ ፡-፳፩) የሾጠጠ ሾጣጣ፤ ሞጥሟጣ።
ሥጥቀት ፡-(ላጥ ሠ) መሠንጠቅ፤ መቀደድ ሠንጣቅነት፤ ሥንጥቃት ንቃቃት። ሥጥቀተ ገቦ በመጥባሕት። እንተ ሥጥቀተ አረፍት። ከመ ሥጥቀተ ፈለግ፤ ውስተ መሬት ፡-(ስንክ ፡-ሠኔ፳፯። አቡሻ ፡-፶። ኢዮ፳፰ ፡-፬)።
ሥጥየት ፡-እብደት፤ ስካር፤ ጥጋብ፤ የእብደትና የስካር የጥጋብ ሥራ። ስክረት ወሥጥየት ፡-(፩ጴጥ ፡-፬ ፡-፫)።
ሥጹር ፡-(ራን ራት ጽርት) የተሠነጠረ የተከፈለ፤ የተሠነጠቀ። ሥጹር ለክልኤ ፡-(መጽ ፡-ምስ)።
ሥጻር ፡-(ራት) ሥንጣሪ ፥ ሥንጥር፤ ሥንጣቂ። ሥጻረ ዕፅ ፡-(ገድ ፡-ተክ)።
ሦር ፡-በሬ፤–ሰውሮ ሰወረ ሶር።
ሦቀ ፡-ደገፈ፤–ሰዊቅ ሶቀ።
ሦካዊ ይ ፡-የሾኽ ዐይነት ፥ ወገን፤ እሾኻም ፥ ሹካ። ሹላፍ እሾኻፍ፤ ሸውከኛ አሻዋኪ ፥ ሾካካ።
ሦክ ፡-(ብ አሥዋክ። ዕብ ሶክ ፥ ሱካ፤ ዐጽቅ። ዐረ ሸውክ ፥ ሸውከት) ሾኽ እሾኽ የሾኽ ዛፍ። ወግዐኒ ሦክ። አክሊል ዘሦክ። ይቀሥሙሁ እምአሥዋክ አስካለ ፡-(መዝ ፡-፴፩። ማር፲፭ ፡-፲፫። ማቴ፯ ፡-፲፮)።
ሦጠ ፡-ጨመረ፤–ሰዊጥ ሶጠ።
No comments:
Post a Comment