ሀ ለ ሐ መ ሠ ረ ሰ ሸ ቀ በ ተ ቸ ኀ ነ ኘ አ ከ ኸ ወ ዐ ዘ ዠ የ ደ ጀ ገ ጠ ጨ ጰ ጸ ፀ ፈ ፐ
ሸጊህ ፡-(ዕብ ሾጌህ) ጊጉይ፤ ስሑት፤ በስሕተት የበደለ ፡-(ሕዝ፵፭ ፡-፳)።
ሺሓታት ፡-መቶ ሺሕ፤ ወይም ሺ ጊዜ መቶ፤ ዐሥር እልፍ። እለ አምኑ ኢኮኑ ሺሓታት ወኢአእላፋተ አላ አህጉርኒ ወበሓውርት ፡-(ፊልክ ፡-፵፩)።
ሺሓት ፡-ዐሥር ሺሕ፤ ወይም መቶ ጊዜ መቶ፤ አንድ እልፍ።
ሺሕ ፡-(ሓት ታት፤ ዐማራና ትግሬ) በቁሙ፤ ሺ፤ ዐሥር መቶ፤ ወይም መቶ ጊዜ ዐሥር። ከሰላማ በፊት በነበረው ባሮጌው ግእዝ መቶ ብሎ እልፍ ነው እንጂ ሺሕ የለም፤ አለመኖሩም በአኃዙ ተራ ይታወቃል ፻ ብሎ ፻፻ በማለቱ። በትግሬም ቢኾን እልፍና ሺሕ አንድ ወገን ናቸው፤ እልፍ የሚባለው ያው ሺሑ ነው። ሺሑን አምኣት ወይም ፲፻ ማለትና ዐሥሩን ሺሕ ፻፻ ማለት ከጽርእና ከቅብጥ የመጣ የሐዲስ ግእዝ ልማድ ነው፤ ጥንታዊው ፊደል ያበገደ ተራ ሲፋለስ አኃዙም ተፋልሷል። ካኹን በፊት ለሺሕ ለአምኣት እንደሌላው ቍጥር አኃዝ ምልክት አልነበረውም፤ ዛሬ ግን ባቡጊዳ ሥርዐት ቀ ምእት እንዲባል ፥ ቈ ደግሞ ስለ ቀለበቱ አምኣት ይባላል፤ ሺሕ ማለት ነው። የአንና የኀን የቀን አፈታት ተመልከት።
ሺዋ ፡-ስመ ሀገር፤ ስመ ብእሲት፤ ሽኋ ሽሒቱ። ምስጢሩ ብዛት ብዙነት ነውና፤ ሺሖ አሸዋ ከማለት ይሰማማል። ፡-(ታሪክ) ጥንታዊው የወሎ ባላባት ሴት ልጁን ለግሼው ባላባት ለወንድ ልጁ በሕግ አጋብቷት ስትኖር ፥ ከብዙ ዘመን በኋላ ልጆቿን ይዛ አባቷን ለማየት ወሎ ኼደች። አባቷም በልጆቿ ብዛት ተደንቆ እነዚህ ኹሉ ምኖችሽ ናቸው ቢላት፤ እኩሉ ልጆቼ ፥ እኩሉም የልጅ ልጆቼ አለችው። ልጄ ሺዋ ፥ ልጄ ሺዋ፤ ቀድሞም ስድርሽ ሺ ኹኚ ፥ ሺ ያድርግሽ ብዬ መርቄሽ ነበረ፤ አኹንም እንደ ምርቃቴ ሺ ስለ ኾንሽ ከንግዴህ ወዲህ ስምሽ ሺዋ ይኹን ፥ ሺዋ ብዬሻለኹ አላት። ርሷም እንደ ሳራ በቡራኬ ላይ ቡራኬ ጨምራ ፥ ሺዋ ተብላ ተመለሰች። ልጆቿም ሺዎች ፥ የሺዋ ልጆች ተብለው በያህጉሩ ተበትነው መንዝን ተጕለትን ይፋትን ፥ ቡልጋን ጠራን መርሐ ቤቴን ፥ ሌላውንም ኹሉ አቀኑ። ከግሼ ከዳዬር እስከ ዝቋላና እስከ የረር ፥ ምሥራቁና ምዕራቡም ሳይቀር በርሷ ስም ሺዋ ተብላል። ፡-(ግጥም ስለ ሰገሌ ጦር) ኋለኛው ባላባት ዝምድና ሊያፈርሱ ከወሎ ገሥግሠው ፥ ሰገሌ ሲደርሱ፤ በቅሎና መጫሚያ ስላልነበራቸው ፥ አዬ ጕድ አዬ ጕድ ያ ፡-(ሺዋ) አሸዋ ፈጃቸው። ውሃ ውሃ ሲሉ ከረሞጫው ላይ፤ መላእክት አንሥተው ወሰዷቸው ዟይ።
ሻሪም ፡-(ዕብራ) ሐለይት፤ መዘምራን። ሕዋራተ ሻሪም ፡-(ሕዝ፵ ፡-፵፬)።
ሻዳይ ፡-(ዕብራ) ስመ አምላክ፤ ኀያል፤ ጽኑዕ፤ ከሃሌ ኵሉ፤ ልዑል ላዕለ ኵሉ። አልሻዳይ፤ ፡-(ኤል ሻዳይ) አምላክ ተስፉ፤ ዘይሴፎ ኵሉ ኪያሁ፤ ወዘያስተሴፋ ፡-(ዘፀ፫ ፡-፲፬ ፡-፲፭። ሕዝ፲ ፡-፭)።
ሽቦሌት ፡-(ዕብራ) ሰብል፤ ዝርዝር እሸት፤ ራስ ዛላ። ወይቤልዎ ሽቦሌት፤ ወይቤ ሲቦሌት ወኢያርትዐ ነቢበ ፡-(መሳ፲፪ ፡-፮)። ባለብሉዮች ግን ንባቡን ሽሖሌት ይሉና፤ ፍችውን ለባሕር ለገደል ያድርገኝ ማለት ነው ይላሉ፤ የተሳሳተ ነው። ሽቦሌት በል ማለት፤ ደቂቀ ኤፍሬም የሸ ጸያፎች ናቸውና፤ ኤፍሬማዊነቱን በገዛ አፉ ለማስመስከር ነው። ሽሖሌት ያሉት ግን ሽሔሌት ነው፤ ፍችውም የሽቱ ቡቃያ ቅጠል፤ የባሕር ዛጐል፤ ባሕረ ወጥ ሽቱ፤ ሰንበልት ማለት ነው።
No comments:
Post a Comment