ሀ ለ ሐ መ ሠ ረ ሰ ሸ ቀ በ ተ ቸ ኀ ነ ኘ አ ከ ኸ ወ ዐ ዘ ዠ የ ደ ጀ ገ ጠ ጨ ጰ ጸ ፀ ፈ ፐ
ሐዊዝ ዞት ፡ (ሖዘ፤ ሐወዘ የሐውዝ ይሑዝ) ማወዝ፤ ዐዋዜ መኾን፤ መጣም መጣፈጥ መስማማት፤ ማማር መወደድ። ደስ ፈቅ ማሰኘት፤ ማስጐምዠት። ለሚያየውና ለሚሰማው ለሚቀምሰው፤ የመልክ የዜማ የምግብ የነገር። ኢየሐውዘኒ ሣእሣአ ቃልክሙ። መሰንቆ ወመዝሙር የሐውዛ ለነፍስ። ሐወዘኒ እስመ ሞቁ። ወባሕቱ ሊተሰ ኢየሐውዘኖ ዝንቱ ፡ (ኢዮ፮ ፡ ፳፮። ሢራ፵ ፡ ፳፩። ኢሳ፵ ፡ ፳፩። አስቴ፭ ፡ ፲፫)። በሐወዘ ፈንታ አሖዘ አስተሐወዘ ይላል፤ አያሰኝም። ይገብር ዘከመ ያሐውዞ። በዕፍረት ወዕጣን ወወይን ያስተሐ(ሔ) ውዙ ልበ ፡ (ሄርማ ፡ ገ፶፱። ምሳ፳፯ ፡ ፱)።
ሐሐርኤል ፡ ምሥዋዕ፤–ሀሀርኤል።
ሐለለ ፡ (ሐረረ) ዐረረ ከሰለ፤ ተቃጠለ። ዘሩ ሐሪር ነው፤ ረ ሲሉ ለ የሚሉ ሰዎች የረ ጸያፎች ያገቡት ነው። ትግሬ ግን ሐለለ ብሎ፤ ደከመ ዛለ ጠወለገ ይላል።
ሐለስ ፡ ዐጃ፤–ዐለስ።
ሐለስት ሐለስትዮ ፡ (ታት። ዕብ ሐላሹት። ዐረ ኀሊስ) ክልስ፤ ቅልቅል ድብልቅ፤ ነጭና ጥቍር ዝንጕርጕር፤ ንጣቱን ጥቍረት ጥቍረቱን ንጣት የተቀላቀለው፤ ዘሩና ጠጕሩ ነጭ ብቻ ወይም ጥቍር ብቻ ያይዶለ፤ ዲቃላ፤ ጦጣ ነጨ ዝንጀር፤ የበዳ አህያ። ቦኑ ለከንቱ ይነቁ ሐለስትዮ ፡ (ኢዮ፮ ፡ ፭ ፡ ፳፩። መዝ፻፫)።
ሐለከ ፡ (ትግሬ) ወደረ ሰነከለ፤ ቀየደ ሸነከፈ፤ የከብት። በቁሙ፤ ተላላከ ሕልከኛ ኾነ ፡ (ዐማርኛ)።
(ጥ) ሐለወ [1]:-ኖረ፤–ሀልዎ ሀለወ።
[2] ፡ (ላ) ሐለወ፤–ጠበቀ፤–ኀሊው ኀለወ ኀላዊ።
ሐለዚዝ ፡ (ዐረ ሐለዞን) ዛጐል ልብሱ፤ ቀንዳም ልጋጋም ትል፤ እንደ ሔለይ ከዛጐሉ ውስጥ የሚከተት፤ ክረምት ሲገባ ደመና ሲዞር ባንድ ቀን ዝናም የሚፈጠር፤ ነጮችና ዐረቦች ቀቅለው አብስለው እንዳሹቅና እንደ በቈልት እንደ ሽንብራ እሸት እየጠረጠሩ የሚበሉት። ቀርነናእን እይ፤ ከዚህ ጋራ አንድ ነው። ባለቅኔዎች ግን ለውዝ ይሉታል፤ ዘሩ ለዚዝ ነውና ለዘን እይ።
(ጥ) ሐለየ ፡ ዐሰበ፤–ኀልዮ ኀለየ ኅሊና።
ሐለደ ፡ ጨረሰ፤–ኀልዶ ኀለደ ኀላዲ።
ሐለጸ ፡ (ዕብ ሐላጽ) መዘዘ አወጣ ከወገቡ፤ የሰይፍ የዘር የአባላ ዘር። ዐለጠ፤ ዐልጫ ኾነ።
ሐለፈ [1] ፡ ዐለፈ፤–ኀሊፍ ኀለፈ።
[2] ፡ (ዐረብ) ማለ ተረገመ፤ ተገዘተ።
ሐሊም ሞት ፡ (ሐለመ የሐልም ይሕልም። ዕብ ወሱር ሐላም። ዐረ ሐሉመ) ማለም፤ በንቅልፍ ልብ ሕልም ራእይ ማየት። ወደገመ ሐሊመ። ሐለምኩ ሕልመ ወደንገፀት ነፍስየ። ወሊቃውንቲክሙ ሕልመ የሐልሙ። ለእመ ሐለመ ኤጲስቆጶስ አንስተ ኢይቅረብ ፡ (ዘፍ፴፯ ፡ ፭። ዳን፪ ፡ ፫። ዮኤ፪ ፡ ፳፰። ኪዳ)። በሐለመ ፈንታ ተሐለመ ይላል፤ ስሕተት ነው። ሐላምያን እለ ይትሔለሙ ለክሙ ፡ (ኤር፴፬ ፡ ፯። ፴፮ ፡ ፰)። መወፈር መግዘፍ ታላቅ መኾን፤ መጽናት መበርታት። ሕልመልሜሌክን ተመልከት።
ሐሊቅ ቆት ፡ (ሐለቀ የሐልቅ ይሕልቅ። ዐረ ሐለቀ) መዞር መክበብ፤ ዙሪያ ክብ ማድረግ። ወይም መክበብ፤ ክቡብ ክበባም መኾን፤ የሥራ።
ሐሊብ ፡ ወተት፤ ነጭ ፈሳሽ ሴትነት ካላቸው ከሕያዎን ፍጥረት ከወላጆች ጡት የሚወጣ የሕፃናት የገላግልት ምግብ። እስመ ኵሉ ዘይትወጋዕ ሐሊበ ሕፃን ወቱ። ወኩኑ ከመ ሕፃናት ወ አፍቅሩ ሐሊበ ነባቤ። ሐሊበ አልሕምት ወአባግዕ ፡ (ዕብ፭ ፡ ፲፫። ፩ጴጥ ፡ ፪ ፡ ፪። ገድ ፡ ዘሚ)። በሴት አንቀጽ ከምትጠራ ከምድር የሚወጣም ፍሬና ማዕደን ጥሩ ነገር ኹሉ ሐሊብ ይባላል፤ የምድር ዐላባ እንዲሉ። ወቦኡ ምድረ እንተ ትውሕዝ ሐሊበ ወመዓረ ፡ (ሢራ፵፮ ፡ ፰)። ለዕፀዋትም ይነገራል። ወያንጸፈጽፍ ሐሊቦሙ ፡ (ራእ ፡ ባሮ)። ሐሊብ ነባቢ፤ ያለውም የወጣኒ የሕፃናት ትምርት ምስጢረ ሥላሌ ይባላል። የሐሊብ መሠረት ምግብነት ሲኾን ፫ ግብር አለው፤ ሕይወተ ሕፃናት ነው፤ ያሳድጋቸዋል፤ ኀይል ይሰጣቸዋል፤ ትምርትም ለነፍስ ምግብነቱ እንደ ሐሊብ ነው።
ሐሊብ ቦት ፡ (ሐለበ የሐልብ ይሕልብ። ዐረብ። ዕብ ሐላብ) ማለብ፤ ከእንስሳት ጡት ወተት ማውጣት። ከመ ሐሊብ ሐለብከኒ። ሕልብ ሐሊበ። የሐልቦሙ ለእንስሳ ፡ (ኢዮ፲ ፡ ፲። ምሳ፳፬ ፡ ፷፰። ስንክ ፡ መስ፲፰። መስረቅ ፥ የሰውን ገንዘብ እንደ ጡትና እንደ ወተት መሳብ፤ ሳይታዩ መውሰድ። ሌባ ማለት ከዚህ ወጥቷል።
ሐላ ሐሊባ ፡ ድንኳን፤–ኦሆላ ኦሆሊባ።
ሐላሚ ፡ (ሚት ምያን ያት፤ ለምት) በቁሙ፤ የሚያልም፤ ሕልም ራእይ የሚያይ፤ ሕልማም ባለሕልም። ነቢይ አው ሐላሜ ሕልም። ይትኀፈሩ ሐላምያነ ሕልም ፡ (ዘዳ፲፫ ፡ ፩። ሚክ፫ ፡ ፯)።
ሐላቢ ፡ (ቢት ብያን ያት፤ ለብት) የሚያልብ ዐላቢ፤ ባለጥገት።
ሐላዪ ፡ (ዩት ይያን ያት፤ ለይት) የሚዘፍን ዘፋኝ፤ አመስጋኝ ገጣሚ፤ ባለቅኔ ባለዜማ። ወፅኣ ሐላይያት ወተቀበላሁ። ሐለይት ወሐላይያን ፡ (፩ነገ ፡ ፲፰ ፡ ፮። መክ፪ ፡ ፰)።
ሐልቀ ፡ ዐለቀ፤–ኀሊቅ ኀልቀ።
ሐልዘዘ ፡ አፈራ ሐለዞን ወለደ፤ ዝናቡ ምድሩ።
ሐልይ ዮት ፡ (ሐለየ የሐሊ ይሕሊ። ዐረ ሐሊየ) መለዘብ መለስለስ፤ መላም መጣም መጣፈጥ፤ የግብር የነገር። መዝፈን ማመስገን፤ መቀኘት መግጠም፤ መወረብ ማለዘብ፤ እያዜሙ ምስጋና ማቅረብ። ለዘብ ማለት ከዚህ የወጣ ነው፤ የዜማውን ጣዕም ማማሩን መተባበሩን ያሳያል። አሐሲ ማሕሌተ። ንሕሊ ማሕሌተ መንፈሳዊተ። ሕልዩ ለእግዚ በጸናጽል። ምሕረተ ወፍትሐ አሐኢ ለከ። ሐለያሁ ወዘመራሁ። ኪያየ የሐልዩ እለ ይሰትዩ ወይነ ፡ (ኢሳ፭ ፡ ፩። ፈ ፡ መ ፡ ፴፪ ፡ ፯። ዮዲ፲፮ ፡ ፩። መዝ ፡ ፻። ሢራ፵፯ ፡ ፮። መዝ ፡ ፷፰)።
፡ መጐባት፤ ጕቦ መማለጃ መስጠት። ምስጢሩ ማለዘብ ካለው ይገባል፤ ያልበላ ዳኛ እውነት ለመፍረድ የማይፈራ ካክራ ሸካራ ነውና። ወሐለይኪዮሙ ይምጽኡ ኀቤኪ። ወመሰሎ ለፊልክስ ዘይሁቦ ጳውሎስ ወየሐልዮ ንዋየ ፡ (ሕዝ፲፮ ፡ ፴፫። ግብ፳፬ ፡ ፳፮)።
ሐመል ፡ (ዐረ እልሐመል) ኮከብ፤ የኮከብ ስም፤ አውራ በግ። ከፀሓይ ጋራ በመጋቢት ፴ ዕለት ፵፫ ኬክሮስ ይመግባል ፡ (አቡሻ ፡ ፬) የስሙ ምስጢር ማስረገዝና ማሸከም ነው፤ መጋቢት በወዲያ እንደ መስክረም ነውና፤ ቅጠሉና ልምላሜው ሳይቀር መዋዕለ ፅንስ መኾኑን ያሳያል።
ሐመልሚል ፡ (ላን ላት ማል) የለመለመ፤ ርጥብ ቅጠላም፤ ቅጠልማ ቅጠልያ፤ ቅጥልጣል፤ ዐይነቱ ቅጠል አረንጓዴ የሚመስል። ወይም ብጫ፤ የወራ ቅጠል የበሰለ ፍሬ ሊወድቅና ሊደርቅ የቀረበ፤ ወይባ ዐደይ አበባ የሚመስል የሎሚ የብርትኳን ዐይነት። የሚያበራ የሚበርቅ የሚያብረቀርቅ የወርቅና የንሓስ ዐይነት። ነሥአ በትረ ልብን ሐመልሚለ፤ ርጥብ። ዕንቍ ሐመልሚል። ፈረስ ሐመልሚል ፡ (ዘፍ፴ ፡ ፴፯። ፪ ፡ ፲፪። ራእ፮ ፡ ፰)። በሐመልሚል ፈንታ ሐመልማል ይላል፤ አያሰኝም ፡ (ራእ፰ ፡ ፯)።
ሐመልማለ ሐምል ፡ የበሰለ የገረጣ ቅጠል፤ ወይም የጐመን ፡ (መዝ ፡ ፴፮)።
ሐመልማለ ሣዕር ፡ መስክ ጨፌ ለቆ፤ ርጥብ ሣር ፡ (ማር፮ ፡ ፴፱)።
ሐመልማለ አቍጽል ፡ ርጥበት ልምላሜ፤ ልብስነት ፡ (ሔኖ፭ ፡ ፩)።
ሐመልማለ ወርቅ ፡ የወርቅ ሽቦ፤ ወይም ቅጠል ሥሥ ረቂቅ ፡ (መዝ ፡ ፳፯)።
ሐመልማለ ዘርዕ ፡ ቡቃያ፤ ተክል፤ ተዘርቶ የሚበቅል ኹሉ ፡ (ሢራ፵ ፡ ፳፪)።
ሐመልማል ፡ (ላት) ለምለም፤ ቋያ ቡቃያ ሣር ቅጠል፤ እኽል ተክል፤ ዛፍ ቋጥቋጦ፤ ለጋ ቀንበጥ ሙሽራ፤ ለባልብ ውልብልቢት፤ መላው የማግሰኞ ፍጥረት። ለታብቍል ምድር ሐመልማለ ሣዕር። ኵሉ ሐመልማለ ሐቅል ወኵሉ ሐመልማለ ምድር። እምቅድመ ያስተርኢ ገጸ የብስ ወእምቅድመ ይብቍሉ ሐመልማላት ፡ (ዘፍ፩ ፡ ፲፩። ፪ ፡ ፭። ቅዳ)። አመልማሎ የጥጥ ነዶ፤ የንድፍ ጥቅል ፡ (ዐማርኛ)።
ሐመረ ፡ (ሐመለ፤ ጾረ፤ ሰከመ) ተጫነ ተሸከመ፤ ተሸክሞ ኼደ ተነዳ።
ሐመር ፡ (ብ አሕማር ራት። ዐረ ሒማር። ዕብ ሐሞር፤ አህያ) መርከብ የባሕር እህያ፤ የሚጫን የሚሸከም ተጭኖ፤ የሚኼድ የሚነጕድ በጢስ በነፍስ የሚነዳ፤ ከብረት ከንጨት የተሠራ የተሰናዳ። ረከበ ሐመረ ዘይነግድ፤ ወተዐሰበ ሐመረ ወዐርገ ውስቴቱ። አሕማረ ተርሴስ። ነገሥት አሕማር ፡ (ዮና፩ ፡ ፫። መዝ ፡ ፵፯። ሔኖ ፡ ፻፩)። ሐመረ የብስ፤ የምድር ባቡር፤ ሌላውም በእሳት ኀይል የሚኼድ ኹሉ። ረከበንና መርከብን እይ።
ሐመዳ ፡ ዐመዳይ፤ ብትን ውርጭ፤ ዐመድማ ነጭ፤ ከውሃ ላይ ሲያርፍ የሚረጋ፤ ዋግ እየኾነ እኽል የሚያበላሽ። የስሙ ምስጢር ፪ ነው፤ ንጣትና አጥፊነት። አስሐትያን እይ፤ ከዚህ ጋራ አንድ ነው። ቍር ወበረድ ወአስሐትያ ወሐመዳ። እምአይቴ ይወፅእ ሐመዳ፤ ወመኑ ይወልዶ ለሐመዳ ሰማይ ፡ (ሔኖ፴፬ ፡ ፪። ኢዮ፴፰ ፡ ፳፬ ፡ ፳፱)። ለብትን በረዶም ይነገራል ፡ (፩ዜና ፡ ፲፩ ፡ ፳፪)።
ሐመዳዊ ፡ (ዊት ውያን ያት) ዐመዳም፤ ዐመድማ ቡላ ዐፈርቻ፤ ዐይነቱ ሕብሩ ሐመድ የሚመስል። አፍራስ ሐመዳውያን ፡ (ዘካ፮ ፡ ፫)።
ሐመድ ፡ በቁሙ፤ ዐመድ የእሳት ብላቶ ነጭ ትቢያ። የሣር የገለባ ሲኾን ስለ ጥቍረቱ ጠለስ ይባላል። አውዐያ ለሀገር ወኮነት ሐመደ። ጠፍኡ ከመ ሐመደ ሡዕ። መሬት ወሐመድ ፡ (ኢያ፰ ፡ ፳፰። ኢሳ፵፫ ፡ ፲፯። ዘፍ፲፰ ፡ ፳፯)።
፡ ደቃቅ ከሰል፤ ጥላት ጥቀርሻ። ሐመደ እቶን ፡ (ዘ፱ ፡ ፰)።
፡ ዐቧራ ትቢያ፤ ደቃቅ ዐፈር። ወደዩ ሐመደ ዲበ ርእሶሙ። ሐመደ ይቀምሑ ፡ (ኢዮ፪ ፡ ፲፪። መዝ ፡ ፸፩)። ማናቸውም ደቃቅ ነገር ኹሉ ሐመድ ይባላል፤ ዶቄት ማለት ነው። ሐመደ እብን፤ ኖራ በረቅ ጠመኔ።
ሐመድማድ ፡ ዐመዶ፤ ዐመድማዶ፤ ዐመድማ ቅጠል ዐመድ የነፋበት የሚመስል።
ሐመጸ ፡ (ትግ ሐምጸ። ዕብ ሐማጽ) ቦካ ሖመጠ ሖመጠጠ፤ ሸመጠረ፤ ሖምጣጣ ኾነ።
ሐሙኢዳ ፡ ቀጠሮ፤–ሀሙኢዳ።
ሐሚል ሎት ፡ (ሐመለ የሐምል ይሕምል። ዐረ ሐመለ፤ ጾረ። ዕብ ሐማል፤ ራራ) መፅነስ ማበብ፤ ማፍራት መሸከም። መማረር መልቀም፤ መዘንጠፍ መመልመል፤ የፍሬ የቅጠል። ወፈረ ገዳመ ይሕምል ሐምለ ምድር። ወበዕለተ ዐርብ የሐምል ሐምለ ገዳም ዘእንበለ ይኅሪ መሪረ ወጥዑመ ፡ (፬ነገ ፡ ፬ ፡ ፴፱። ገድ ፡ ተክ)።
ሐሚም ሞት ፡ (ሐመ፤ ሐመመ የሐምም ይሕምም። ዐረ ሐመ። ዕብ ወሱር ሐም) መሞቅ መተኰስ መፋጀት፤ በንዳድ በትኵሳት መያዝ። መታመም መከራ መቀበል፤ ማማጥ መጨነቅ ማዘን ማልቀስ መናደድ። ተሐምም ዐቢየ ፈፀንተ። ዘእንበለ ትሕምም ተፈወስ። በእንቲኣነ ሐመ። ተሐምም ለወሊድ። ሐመምኩ ላዕሌከ ፡ (ሉቃ፬ ፡ ፴፰። ሢራ፲፰ ፡ ፲፱።ኢሳ፶፫ ፡ ፬። ራእ፲፪ ፡ ፪። ፪ነገ ፡ ፩ ፡ ፳፮)።
፡ መመቅኘት፤ መንፈግ መቤስ መሠሠት። የሐምም አቅርቦ እዴሁ ውስተ አፉሁ ፡ (ምሳ፳፮ ፡ ፲፭)።
ሐሚው ዎት ፡ (ሐመወ የሐሙ ይሕሙ) ማመት ማመች፤ መታመት መታመች ዐማት ዐማች ማድረግ፤ ወይም መኾን። መምረር መጐፍነን፤ ሐሞት መኾን ወደ ሐሞት ጠባይ መለወጥ፤ የምግብ። ክፉ ጋብቻንም ያሳያል።
ሐሚዝ ዞት ፡ (ሐመዘ የሐምዝ ይሕምዝ። ዐረ ሐሚፀ። ሱር ሕማጽ። ዕብ ሐማጽ) መሖምጠጥ፤ መሰንፈጥ፤ መቡካት መበላሸት። መምረር መጐምዘዝ፤ መጐፍነን። መርዘኛ መርዛም መኾን በመርዝ መግደል። መጥላት መመረዝ፤ ቂም በቀል መያዝ። መቈጣት መወግሸት፤ እንደ መርዝ ኹኖ ሰው እስከ መግደል እስከ ማጥፋት። ሐመወና መፀ የዚህ ጎር ናቸው፤ ባንዳንድ ወገን ይመሳሰላሉ።
ሐሚድ ዶት ፡ (ሐመደ የሐምድ ይሕምድ። ዐረ ወትግ፤ ሐምደ፤ ገነየ) ማመድ መብላት፤ ማቃጠል ማመት፤ ሐመድ ሕመት ማድረግ፤ የእሳት የመብራት የኖራ የንጨት። መቍረጥ መጕመድ መጐማመድ፤ የስለት። ገመደን እይ፤ የዚህ ጎር ነው። ይውዒ ይትሐመድ በማለት ፈንታ የሐምድ ይላል ስሕተት ነው ፡ (ሕዝ፲፭ ፡ ፬)።
ሐሚግ ፡ (ሐመገ የሐምግ ይሕምግ። ሐመቀ) ማመግ፤ ማጥፋት ማበላሸት የምግብ። ማደፍረስ መበጥበጥ፤ የውሃ የመጠጥ። ማይ ዘሐመግሙ በእገሪክሙ። ፈለግ ዘሐመግሙ በደመ ቅቱላን። እንዘ የሐምጉ ማያተ ብዙኀ ፡ (ሕዝ፴፬ ፡ ፲፱። ጥበ፲፩ ፡ ፯። ዕን፫ ፡ ፲፭)። ማፍዘዝ ማደንገዝ፤ ማቦዝ ማብለዝ፤ ማድከም፤ የዐይን። ምስጢሩ ጽርየት ማሳጣት ነውና፤ ማደፍረስ ካለው ይገባል።
ሐማሊ ፡ (ሊት ልያን ያት፤ መልት። አው ሐማል፤ ላን ላት) የሚዝሸከም ተሸካሚ፤ ማራሪ ለቃሚ። ሐማል ወንድና ሴት ያስተባብራል።
ሐማሚ ፡ (ሚት ምያን ያት፤ መምት) የሚታመም ታማሚ፤ ሕማም የሚስማማው፤ ሐዘንተኛ መከረኛ። አንተ ሐማሚ ዘከመ ዕሪናከ ምስሌነ፤ ወአንተ ኢሐማሚ ዘከመ ዕሪናከ ምስለ አብ። ነአምን ከመ ቃለ እግዚ ኢሐማሚ። ሐሚምት አርኣያ ገብር ፡ (ሃይ ፡ አበ። ተረ ፡ ቄር)።
፡ የሚመቀኝ ምቀኛ፤ ሥሡ ንፉግ። ዐይንከኑ ሐማሚ ውእቱ። ዐይኑ እሐማሚ ይጠውዕ እክለ። ብእሲ ሐማሚ። ሐማምያን ፡ (ማቴ፳ ፡ ፲፭። ሢራ፲፬ ፡ ፲። ምሳ፳፰ ፡ ፳፪። ጥበ፮ ፡ ፭። ሮሜ፩ ፡ ፳፱)።
(ጥ) ሐማም ፡ (ዐረ) ፍል ውሃ፤ ማወት ቤተ ብለኔ።
ሐማስ ፡ (ትግሬ) ጠይም ዳለቻ ድፍርስ፤ የጠጠር ውሃ መሳይ።
ሐማት ፡ (ብ አሕማት) ሴት ዐማት። ረከባ ለሐማተ ጴጥሮስ ፡ (ማቴ፰ ፡ ፲፬)። መርዓት በማለት ፈንታ ሐማት ይላል፤ስሕተት ነው። ዘይገብር ከመ ዝ ወይሰክብ ምስለ ሐማቱ ያውዕይዎ በእሳት ፡ (ኩፋ ፡ ፵፩)።
ሐማዪ ፡ (ዪት ይያን ያት፤ መይት) የሚያማ ፡ (ዐሚ) ሐሜተኛ ሐሚና፤ ሰዳቢ ነቃፊ፤ ለፋፊ ለፍላፊ። ሰብእሰ ሐማዪ በላዔ ሥጋ ወሰታዬ ደም። ኢትኩን ሐማዬ። ኢይኩና ሐማይያተ። ወይከውኑ ሐመይት ወሐማይያን ብዙኀ ፡ (ድጓ። ሢራ፭ ፡ ፲፬።ፍ ፡ ነ ፡ ፲ ፡ ፰። ዕር ኢሳ ፡ ፳፮። ሮሜ፩ ፡ ፴)።
ሐሜለት ፡ (ጽር ሒሚሎቲ። ሱር ሚልታ) የላይ ልብስ፤ ካባ በርኖስ፤ መጐናጠፊያ ደበሎ ዐጥፍ። ሐ አርቲክል ነው፤ ሜለት ከሜላት ጋራ ይሰማማል፤ የሜላትን ፍች እይ፤ ባለብሉዮች ግን ኅባኔ ጥምጥም ይሉታል ፡ (፫ነገ ፡ ፲፱ ፡ ፲፫ ፲፱። ፬ነገ ፡ ፪ ፡ ፰ ፡ ፲፫ ፡ ፲፬)። በሠቅ ወበሐሜለት ፡ (ዕብ፲፩ ፡ ፴፯)።
ሐሜት ፡ (ሱር ሐኔት) በቁሙ፤ ዐሚታ ንቀፋ ስድብ፤ ክፉ ነገር ገመና ነውር፤ ስም የሚያጠፋ የሚሰብር፤ በውነት ወይም በሐሰት የሚነገር። ዝንጓጔ ወሐሜት ወዝክር ሕሡም። ዘአልቦ ሐሜት። ቀሲስ ንጹሐ ይኩን እምሐሜት ፡ (ዮሴፍ። ቲቶ፩ ፡ ፯። ቀኖ ፡ ኒቅ)። አንዳንድ መጣፍ በሐሜት ፈንታ እንደ ሱርስቱ ሐኔት ይላል፤ ፍችው አንድ ነው። ቃሕው ወሐኔት ፡ (ሢራ፵ ፡ ፭)። ባለብሉዮች ግን ንዝንዝ ዝብዝብ ይሉታል።
ሐም ሐማ ሐምው ፡ (ብ ሐማን፤ አሕማው) ወንድ ዐማት። ሐመ ሙሴ እስመ ሐሙሁ ለቀያፋ። አዝማዲሁ ወእምዝ ሐማን ፡ (ዘፀ፲፰ ፡ ፲፪። ዮሐ፻፲፰ ፡ ፲፫። ፍ ፡ ነ ፡ ፳፮)።
፡ ዐማች። እመሰ ጸባእክሙነ ትጸብኡ ውሉደክሙ ወአሕማወከሙ ፡ (ዮሴፍ)።
ሐምሐም ፡ ሐምሐም፤–ቅል፤–ሐመመ።
፡ (ዕብ ወሱር ቂቃዮን። ዐረ የቅጢነት) ቅልዕ፤ ቅል የቅል ዐይነት ኹሉ፤ በቈላ በእንቅልቅል በሙቀት አገር የሚበቅል፤ ሐረጋም ስፋሐ አቍጽል፤ ፍሬው ገንቦ ማድጋ የሚያካክል፤ የሚበላ የሚያገለግል። ወአዘዘ እግዚ ሐምሐመ ወበቈለ። ዘመደ ሐምሐም ፡ (ዮና፬ ፡ ፮–፲። ቈስጠ)።
ሐምለ ብሒእ ፡ መራራ ስንፋጣ፤ ሐዞ ስናፍጭ፤ አውጥ ዐሞጭ፤ የመሰለው ኹሉ ፡ (ዘፀ፲፪ ፡ ፰። ዘኍ፱ ፡ ፲፩)።
ሐምለ ሣዕር ፡ ፍሬ እክል፤ እሸት ምርት ፡ (ኩፋ ፡ ፮)።
ሐምለ ቅብዕ ፡ መሎኬ፤ ቅባታም ማላጋ ጠውላጋ፤ እንዳንጣሪያና እንደ ሳማ ያለ፤ የመሎኬን ፍች እይ፤ ከዚህ ጋራ አንድ ነው። ፡ (ኢሳ፶፩ ፡ ፳)። ዕብራይስጡ ግን ፥ ከወጥመድ የገባ ቦኸር አጋዘን ይላል እንጂ ሐምለ ቅብዕ አይልም።
ሐምሌ ፡ በቁሙ፤ የወር ስም የመስከረም ፲፲፤ ቅጠላም።
ሐምል ፡ (ብ አሕማል፤ ላት) ቅጠል ቅጠላቅጠል፤ ሣር ቋያ ቡቃያ ተክል፤ ሥንቆ ጐመን፤ ሰላጣ ቅመም፤ በየስሙና በያይነቱ፤ የሚበላ የማይበላ ማናቸውም ኹሉ። ዐጸደ ሐምል። ሐምለ ገዳም። ሐምለ ሁስጱ ዘይወፅእ ዲበ አረፍት ፡ (ዮሐ፲፰ ፡ ፩። ሱቱ ፡ ዕዝ፲፪ ፡ ፶፰። ፫ነገ ፡ ፬ ፡ ፴፫)።
ሐምስ ፡ (ትግሬ) ጠይም ዳለቻ ድፍርስ፤ የጠጠር ውሃ መሳይ።
(ጥ) ሐምሶ ሶት ፡ (ሐመሰ ይሔምስ የሐምስ። ዐረ) ማመስ ማገላበጥ፤ ለማሞቅ ለማድረቅ። መዋኘት፤ ባሕርን ማማሰል። መብላት መቀለብ፤ ለመሥባት ለመድለብ፤ የእንስሳ። ቦሙ ልማድ ለአባግዕ ይብልዑ ኅቡረ፤ ወሶበሂ ይወርዱ ይስተዩ ማየ፤ አው የሐምሱ ኢይትፈለጡ ዘዘ ዚኣሆሙ፤ አላ ኅቡራን በኵሉ ግዕዞሙ ፡ (ሥር ጳኵ)። ሐመሰ ብሎ ዋኘ ማለት የትግሬ ነው፤ ሙሴና ሐማሴን ከዚህ ወጥቷል። የባሕር ዳር ቅርብ አጠገብ፤ ጠረፍ ወደብ ማለት ነው።
ሐምይ ዮት ፡ (ሐመየ የሐሚ ይሕሚ። ሱር ሐነየ) ማማት መበዝበዝ፤ መንቀፍ መስደብ፤ ሰውን በኋላው በክፋ ማንሣት፤ በላዩ ክፉ ቃል መናገር። ሐመይዎ ለሙሴ። ሐመዩኒ በሐሰት። ዘየሐሚ ቢጾ በጽሚት። ዘየሐሚ አባሁ። ሐመይክሙ ዐቢያተ ወድሩካተ ቃላት ላዕለ ዕበዩ። ፡ (ዘኍ፲፪ ፡ ፩። ሆሴ፯ ፡ ፲፫። መዝ ፡ ፻። ምሳ፳ ፡ ፳። ሔኖ ፡ ፬)። ሐመወ ሐመዘ ሐመመ ሐመየ እሊህ ፬ቱ ዘመዳሞች ናቸው።
ሐሞት ፡ (ብ ሐማውት) በቁሙ፤ መራራ ፈሳሽ በፍጥረት ኹሉ ሆድ ከጕበት ጋራ እንደ ሽንት ውሃ በታናሽ ፊኛ ታቍሮ የሚገኝ፤ ዐይነቱ የዘይት፤ ምረቱ የሬት፤ ሲበዛ ደዌ የሚኾን፤ የሚያሰክር ራስ የሚያዞር። የምረርን ፍች እይ፤ ከዚህ ጋራ አንድ ነው። ተክዕወት ውስተ ምድር ሐሞትየ። ምንት ውእቱ ልቡ ወከብዱ ወሐሞቱ ለዝ ዓሣ። ወሀብዎ ይስተይ ወይነ ወሐሞተ ድሙረ ፡ (ኢዮ፲፮ ፡ ፲፫። ጦቢ፮ ፡ ፮። ማቴ፳፯ ፡ ፴፬)። ሬትና ከርቤ ሌላውም ኹሉ ከዚህ ስም ነሥቶ ሐሞት ይባላል፤ መራራ ማለት ነው። ወደዩ ሐሞተ ውስተ መብልዕየ ፡ (መራራ ቅጠል)። ምንት ይመርር እምሐሞት ፡ (ሬት፤ የሬት ወገን)። ፡ (መዝ ፡ ፷፮። ምሳ፭ ፡ ፬)።
፡ ዐሞት፤–ሐመወ፤
(ጥ) ሐሰ ሓስ ፡ (ዐረ ሓሸ። ሱር ሐስ። ዕብ ሓሊላ) ከሐሰወ ሥር የወጣ ነባር አንቀጽ፤ አሉታ። አይገባም፤ አይኾንም፤ አይዶለም፤ አይኹን አይደረግ፤ አይድረስ፤ ሕርም ውሸት። ሐሰ ኢትመውት ፡ (፩ነገ ፡ ፳ ፡ ፪። ሮሜ፫ ፡ ፬ ፡ ፴፩። ፲፩ ፡ ፩። ገላ፪ ፡ ፲፯)። ሲረባም ሐሰ ሊተ ለከ ሎቱ እያለ እንደ ወይና እንደ አሌ በለ ይዘምታል፤ ምስጢሩ እንደ አሌ በለ ይዘምታል፤ ምስጢሩ እንደ መሐላ ነው። ሐሰ ሊተ ከመ ኢይገብር ዘንተ። ሐሰ ለከ ኢታጥፋነ። ሐሰ ሎቱ ለእግዚእየ እምዝንቱ ርኩስ። ሐሰ ለነ እስከ ነኀድግ ፡ (፩ዜና ፡ ፲፩ ፡ ፲፱። ዮና፩ ፡ ፲፬። ፩ነገ ፡ ፳፭ ፡ ፴፩። ኢሳ፳፪ ፡ ፳፱)።
ሐሠር ፡ በቁሙ፤ ዐሠር ገለባ እብቅ ንፋሽ፤ ፍሬው የወጣለት። ሣር ድርቆሽ ቈሻሻ ጥራጊ ጕድፍ። ክምረ ሐሠር። ወሐሠሮሰ ያውዒ በእሳት። ሐሠር ለገቢረ ግንፋል። ከመ ሐሠር ዘቅድመ ገጸ ነፋስ ፡ (ሢራ፳፩ ፡ ፱። ማቴ፫ ፡ ፲፪። ዘፀ፭ ፡ ፯። ኢዮ፳፩ ፡ ፲፰)።
ሐሰት [1] ፡ በቁሙ፤ ዐሰት ውሸት፤ አሉታ ያወንታ ለውጥ። ኢትኩን ስምዐ በሐሰት። ውሉደ ሐሰት። ነቢያተ ሐሰት። ሐሰት ኢይወፅእ ርም አፉሁ። ወባሕቱ ትንሣኤ ሙታን ሐሰተ ይመስለኒ ፡ (ዘፀ፳ ፡ ፲፮። ኢሳ፴ ፡ ፱። ዕር ፡ ኢሳ፪ ፡ ፲፭። ዮዲ፭ ፡ ፭። ገድ ፡ ተክ)።
[2] ፡ ውሸት፤–ሐስዎ ሐሰወ።
ሐሠከ ፡ ዘነበ፤–ሐሲክ ሐሰከ።
ሐሰከ ፡ (ዐረ ሐሸከ) ዘነብ አካፋ፤ በረደ ቀዘቀዘ፤ ዕስክ ዕሽክ እትት አሰኘ፤ ዝናቡ ብርዱ ውሃው። ዕሽክ እትት አለ፤ ሰውዮው።
ሐሰክ ፡ (ካት፤ አሕሳክ። ትግሪኛ) ተምች የመቅሠፍት ትል በዝናብ የሚሠርጽ የሚወለድ የሣር የቅጠል የቡቃያ ያገዳና ያበባ እኽል ጠላት። ፡ (ተረት) የሰው ሕይወት ሽንብራ እሸት፤ በሽንብራውም ትል አለበት።
(ላ) ሐሠየ ፡ ዐሸ፤–ሐስይ ሐሰየ።
(ጥ) ሐሰየ ፡ ደስ አሰኘ፤–ሐሥዮ ሐሠየ።
ሐሠፈ ፡ ሻከረ፤–ኀሠፈ።
ሐሲል ሎት ፡ (ሐስለ፤ ሐሰለ የሐስል ይሕስል። ዕብ ሐሳም። ዐረ ሐዘመ፤ ለጐመ) መለበብ መሸበብ፤ በለኮ መሳብ። ነሣኣ ምስሌሁ ወአጽዐና ላዕለ ፈረስ፤ ወውእቱ የሐስል ላቲ ፡ (ስንክ ፡ ነሐ፭)።
፡ መሰብሰብ መክተት፤ መጫን መሸከም መውሰድ ማንሣት፤ ያዝመራ። ፡ (የገበሬ ቃል፤ ሮቢ ላይ ፶ ዳውላ ባር ማሽላ አምርቶ ማንሣት ስላቃተው) «ዐምሳ፤ ተው በምኒልክ ተነሣ»። ሰብስቦ መንዳት፤ ከበረት ማግባት፤ ምስጢሩ ከመክተት ይገባል። የሐስሎሙ ሕፃን ንኡስ ፡ (ኢሳ፲፩ ፡ ፮)።
ሐሢም ሞ ት ፡ (ሐሠመ የሐሥም ይሕሥም። ዐረ አሺመ። ዕብ ኣሼም፤ አበሰ) መክፋት መባስ፤ ማደፍ መርከስ፤ በግብር ዐሣማን መምሰል እንዳሣማ መኾን፤ ለመልክም ይኾናል። እስከ ሐሠመ ጺአቱ ሎቱ። ሐሠሞሙ ለሕያዋን ጼና አብድንት። ወሶበ ሰምዐ ሐሠሞ ዝንቱ ፡ (ዮሴፍ)። ቦ እለ የሐሥማ ውስተ ሕንጻ። መልከ ክፉ ኹነው የሚፈጠሩ ፡ (ሄርማ ፡ ገ፹)።
ሐሢር ሮት ፡ (ሐሠረ የሐሥር ይሕሥር። ቀሲስ) መሰብሰብ ማጓለብ ማጋበስ፤ የሣር የገለባ። መላጥ መምለጥ መቅረፍ መሸልቀቅ መፈልፈል መጠርጠር፤ የፍሬና የንቡጥ። ማሸት መጥመቅ፤ የቈሎ የሸት ፥ የወይን የዘይት ፥ የድፍድፍ።
ሐሲዕ ዖት ፡ (ሐስዐ የሐስዕ ይሕሳዕ። ዐረ ጀዘዐ) ቀለብ መቍረጥ፤ ምግብ መንሣት መከልከል፤ ጡት ማስጣል።
(ላ) ሐሲው ዎት ፡ (ሐሰወ የሐሱ ይሕሱ። ዕብ ኪሳህ። ሱር ክሳእ። ዐረ ከሳ) መክደን ማልበስ፤ መሰወር መደበቅ። ፀሓይ ብርሃኖ ሐሰወ ፡ (ስንክ ፡ ታኅ፲፬)።
፡ መክተት፤ ከኪስ ካቅማዳ ከከረጢት ማግባት፤ ማሰር መተብተብ መጠረፍ ማከት። ወሐሰወት ኵሎ ንዋያ ወአጾረታ ለወለታ ፡ (ዮዲ፲ ፡ ፭)።
ሐሳሊ ፡ (ሊት ልያን ያት፤ ሰልት) የሚለብብ፤ ሳቢ ሰብሳቢ ከታች።
ሐሣማ ፡ (ማት) ፤ በቁሙ ሕሪያ ፤ ሕሡመ መልክእ ወመብልዕ (ዐማርኛ)።
ሐሣሪ ፡ (ሪት ርያን ያት፤ ሠርት) ገለባ አውጭ ጪ፤ ጕድፍ ጠራጊ።
ሐሳቢ ፡ (ቢት ብያን ያት፤ ሰብት) የሚያስብ የሚቈጥር፤ ዐሳቢ ቈጣሪ። ሐሳብያነ ከዋክብት ፡ (አቡሻ ፡ ፫። ስንክ ፡ ጥር፮)።
ሐሳብ ፡ (ባት) በቁሙ፤ ዐሳብ ሥጋት። ፡ ( ፡ (የታቦት ዘፈን) ያለው ሊኾን ያለው ሊኾን፤ ዐሳብ አደቀቀው ጐኔን ዐሳብ አደቀቀው ጐኔን)። ሒሳብ ቍጥር፤ ግምት የሒሳብ ሥራ፤ ሰገል ጥንቈላ። ሐሳበ ሤጡ። በሐሳበ ሤጥ። ሰብአ ሐሳባት። እመ ኮነ ተአማኔ በሐሳበ ኮከብ። ዘየሐስብ ሐሳባተ ወልድ ምስለ እም ፡ (ግብ፲፱ ፡ ፲፱። ዮሴፍ። አቡሻ ፡ ፩። ፍ ፡ ነ ፡ ፭። ፈ ፡ መ ፡ ፲፭)።
፡ ልክ መጠን፤ ማዕርግ ሀብት። ዘሂ ይትኔበይ በሐሳበ ሃይማኖቱ። ዘብዙኅ ሐሳቡ ፡ (ሮሜ፲፪ ፡ ፮። ፩ጴጥ ፡ ፫ ፡ ፬)።
፡ ፈቃድ፤ ምላሽ ቍርጥ ነገር። ምስጢሩ ከሐሳብና ከቍጥር ይገባል። በሐሳብ ዘእምኀበ እግዚ። ያግብኡ ሐሳበ ለዘሀለወ ፡ (ቄር። ፩ጴጥ ፡ ፬ ፡ ፭)። በከመ ፈንታ ሐሳብ ይላል፤ ምስጢሩ ልክ ነው። በሐሳበ መልበስቱ። በሐሳበ ምሥዋዕክ።በሐሳበ ሤጡ ፡ (ዘፀ፳፰ ፡ ፲፭። ፳፱ ፡ ፵፩። ዘሌ፳፰ ፡ ፲፯)።
ሐሳዊ ፡ (ዊት ውያን ያት፤ ሰውት) በቁሙ፤ የሚዋሽ ዋሾ፤ ሐሰተኛ ከሓዲ። ሐሳዊ ውእቱ ዘይሔሱ ዘልፈ፤ ሰራቂ ይኔይስ እምሐሳዊ። ልሳን ሐሳዊት። ሐሳውያን ነቢያት። ሐሳውያነ መሲሕ ፡ (ፈ ፡ መ ፡ ፳፫። ምሳ፳፮ ፡ ፳፰። ማቴ፯ ፡ ፲፭። ፩ዮሐ ፡ ፪ ፡ ፲፰)።
ሐሳዪ ፡ (ዪት ይያን ያት፤ ሰይት) የሚያሽ ዐሽታ፤ ወጌሻ አልፊ።
ሐሴቦን ፡ ውስጥ ገጽ፤–ሀሴቦን።
ሐሤት ፡ ዕሠይታ፤ ፍጹም ደስታ፤ የልብ ተድላ የሚያዘልል የሚያስፈነጭ፤ እልል ዕሦ ዕሦ የሚያሰኝ፤ ዕሦ ቅሉ ዕሠይ ማለት ነው ፡ (መዝ ፡ ፲፭። ፳። ፶)።
ሐሴን [1] ፡ (ብ፤ ሐሳይን። ዐረ ሐሲን፤ ሐሱን) ውብ መልከ መልካም፤ ዝንጕርጕር ባለብዙ ሕብር፤ የዥግራ የሶራ የጣዎስ ዐይነት ወፍ ብራብሮ። ዐሸን ያንበጣ ወገን ከምድር የሚፈላ። ወይጠፍኡ ፍጡነ ከመ ሐሴን ዘወፅአ እምግቡ ወኢይትረከብ አሠሩ ወኢይገብው ውስተ ቤቱ ፡ (መቃ ፡ ገ፲)።
[2] ፡ ዐሸን፤–ሐስይ ሐሰየ።
ሐስል ፡ (ብ አሕስል፤ አሕሳል) መያዣ መክተቻ፤ አቅማዳ ስልቻ፤ ዳውላ ዐይበት ቅርጫት፤ ኪስ ከረጢት፤ ከክታን ከፀምር የሚሠራ፤ ወፍራም ጥቅጥቅ። ጥኑ ጠንካራ። ወአዘዘ ዮሴፍ ያምጽኡ አሕስሊሆሙ ወይደዩ ሎሙ እክለ ወወርቆሙኒ ውስተ አሕስሊሆሙ። ወፈትሐ ሐስሎ ወረከበ ወርቆ ውስተ አፈ ሐስሉ። ሰረቀት እለ ትፈትሑ አሕሳለ። ፡ (ዘፍ፵፪ ፡ ፳፭–፳፰።ፍ ፡ ነ ፡ ፵፱)።
ሐሥረ ፡ ጐሰቈለ፤–ኀሥረ።
ሐስቦ ቦት ፡ (ሐሰበ የሐስብ የሐስብ። ዕብ ሐሻብ። ሱር ሕሻብ። ዐረ ሐሰበ) ማሰብ፤ መመርመር። መቍጠር፤ መገምገም መገመት ይህን ያኽል ማለት። ምንት ይእቲ ትዕቢት፤ ይቤ ለእመ የሐስብ ሰብእ ነፍሶ ንጹሐ። የሐስብ ሎቱ ካህን ወርቆ። ሐሲበከ ሐስቦ ለሊከ። ኢየሐስብዎሙ በሐሳበ ዓለም ፡ (ፊልክ ፡ ፴፭። ዘሌ፳፯ ፡ ፲፰። ሱቱ ፡ ዕዝ፱ ፡ ፩። ሔኖ፹፪ ፡ ፭)።
ሐሥአ ፡ በረደ፤–ኀሢዕ ኀሥዐ።
ሐሥዐ ፡ በረደ፤–ኀሥዐ።
ሐስአ ፡ በረደ፤–ኀሥዐ።
ሐስዐ ፡ በረደ፤–ኀሢዕ ኀሥዐ።
(ጥ) ሐስዎ ዎት ፡ (ሐሰወ ይሔሱ የሐሱ። ሐሰ) መዋሸት፤ ሐስት መናገር፤ ዐሎ ማለት መሸፈጥ፤ የተናገሩትን መለወጥ፤ መክዳት መካድ ማፍረስ። ሐስዎ እውነትን በሐሰት መለወጥ፤ ሐቢል ግን ያልነበረውን ፈጥሮ መናገር ነው። ይኄይስ ሰሪቅ እምሐስዎ። አማነ እብል ወኢይሔሱ። ዘይምሕል ለቢጹ ወኢይሔሱ። ኢሐሰውኩ ቃለ አምላክ። ሐሰወ ኪዳኖ ፡ (ሢራ፳ ፡ ፳፭። ሮሜ፱ ፡ ፩። መዝ ፡ ፲፬። ኢዮ፮ ፡ ፲። ዮሴፍ)። በሐስወ ፈንታ አስተሐሰወ ይላል፤ አያሰኝም። ዮጊ ቃልሂ ከመ ኮነ ሥጋ ያስተሐስውዎ ፡ (ቄር ፡ ጰላ)።
(ጥ) ሐሥይ ዮት ፡ (ሐሠየ የሐሢ ይሕሢ) ማስደሰት፤ማሳሠይ፤ ዕሠይ ማሰኘት። መሠየት፤ መጐምዠት። ኢትሠሥዕ ለኵሉ መብልዕ ወኢተሐሢ ለኵሉ ዘርኢከ ፡ (ሢራ፴፯ ፡ ፳፱)።
(ላ) ሐስይ ዮት ፡ (ሐሰየ የሐሲ ይሕሲ) ማሸት ማሻሸት ማፍተልተል። መሐዉ ሠዊተ ወሐሰዩ በእደዊሆሙ ወበልዑ። ሐሰየ አዕይንቲሁ። እለ ይቀጠቀጡ ወየሐስዩ ነፍሰ ወሬዛ። ወለእመ አበየቶ ነፍሱ ለይሕስዮ በግማደ ልብሱ ፡ (ሉቃ፮ ፡ ፩። ጦቢ፲፩ ፡ ፲፩። ኢሳ፲፫ ፡ ፲፰። ፊልክ ፡ ፲)።
፡ መጣስ መጠምሰስ ማበራየት፤ መርገጥ መጠቅጠቅ፤ ማፍረጥረጥ መጥመቅ፤ የወይን የዘይት፤ ያዝመራ። ወቦኡ ወሐሰዩ እልክቱ ሠለስቱ ጸናዕት ማእከለ ትዕይንቶሙ ለኢሎፍሊ። አኮ በመንኰራኵረ ሠረገላ ዘየሐስይዎ ለከሙን ፡ (፩ዜና ፡ ፲፩ ፡ ፲፰። ኢሳ፳፰ ፡ ፳፯)።
ሐረመ ፡ ቀረጠ ነደፈ፤–ኀሪም ኀረመ።
ሐረሠ [1]:-ዐረሰ፤–ሐሪስ ሐረሰ።
[2]:-ወለደ፤–ኀሪስ ኀረሰ።
ሐረሰ ፡ ሐረሰ፤–ወለደ ቀለበ፤–ኀረሰ።
ሐረስ ሐረሳዊ ፡ ዝኒ ከማሁ፤ ሠራተኛ ሠሪ፤ ዐራሽ ቈፋሪ። ሐረሳዊ ብእሲ። ወዘኒ ይጻሙ ሐረሳዊ። ከመ ሐረሳዊ ዘይጸንሕ ፍሬሃ ፡ (ዘፍ፵፱ ፡ ፲፭። ፪ጢሞ ፡ ፪ ፡ ፮። ያዕ፭ ፡ ፯)።
፡ ጠንቋይ መሠሪ፤ ምትሀታም። ሐረሳውያን ፡ (ቀሌ)።
ሐረቁስ ፡ (ዐረ ረቅሽ። ዕብ ሐራቅ፤ ሐቀየ) ምግብ፤ ፍሬ ዕፅ፤ የሚጐረሥና የሚነከስ የሚጋጥና የሚገመጥ፤ የሚታኘክና የሚላመጥ ፡ (ገድ ፡ አዳ ፡ ገ፻፵፪)።
ሐረወ ፡ በሳ፤–ኀሪው ኀረወ።
ሐረየ ፡ መረጠ፤–ኀርይ ኀረየ።
ሐረግ ፡ (ብ አሕራግ) በቁሙ፤ ዐረግ፤ የወይን የዠንፎቅ ያብታ የቅጠል የጠንበለል፤ የመሰለው ኹሉ። ሐረገ ወይን ቅድሜየ፤ ወውስተ ውእቱ ሐረግ ሠለስቱ አዕጹቅ። ገመዱ ሐረገ ወይን። ወሐረጎሙኒ እምነ ገሞራ። አሕራግኪ። አሕራገ ወይን ፡ (ዘፍ፵ ፡ ፱ ፡ ፲። ዘኍ፲፫ ፡ ፳፫። ዘዳ፴፪ ፡ ፴፪። ኤር፴፩ ፡ ፴፪። መቃ ፡ ገ፭)። ትውልድ ዘር፤ ሽቅበና ቍልቍል የሚቈጠር ፡ (ሉቃ፫ ፡ ፳፫–፴፰። ማቴ፩ ፡ ፩–፲፮)።ዐረግኽን ምዘዝ እንዲል ፡ (መንዜ)።
ሐረፋ ፡ (ፋት) በቁሙ፤ ዐረፋ ከርጥብ ከፈሳሽ ከንዶድ ከሳሙና የሚወጣ። ጥማቂ እንጥፍጣፊ መረቅ፤ ከሚቀቀል ነገር የሚወጣ። ይትበላዕኑ ሐረፋ ሐምል ዘእንበለ ጼው ፡ (ኢዮ፮ ፡ ፮)።
ሐሩር ፡ በቁሙ፤ ሙቀት፤ ላበት። ነፋሰ ሐሩር። ጊዜ ሐሩር ፡ (ሆሴ፲፫ ፡ ፲፭። ፍ ፡ ነ ፡ ፲)።
ሐሪም ሞት ፡ (ሐረመ የሐርም ይሕርም። ዐረ ሐረመ፤ ከለከለ) መተው መጾም ሕርም ማለት፤ ሰውነትን ከሚገባ ነገር መከልከል ማራቅ፤ ወይም መራቅ ከልካይና ተከልካይ መኾን፤ በብፅዐት በፈቃድ። እለ የሐርሙ አውስቦ። በእንተ ዘሐረመ አውስቦ። በእንተ ዘየሐርም ንጹሐ ፡ (፩ጢሞ ፡ ፬ ፡ ፫።ሲኖዶ። አብጥ ፡ ፵፯)።
፡ ገንዘብን ወይም ራስን ለግዜር መለየት መቀደስ፤ ምስጢሩ ከብፅዐት ይገባል፤ ሪም ባለሪም ማለት ከዚህ የወጣ ነው። ተሐርሚዮሙ ለእግዚ። ኵሉ ዘየሐርሙ ፡ (ሚክ፬ ፡ ፲፫። ሕዝ፵፬ ፡ ፳፬)።
፡ ማገልገል ካህን መኾን፤ ምስጢሩ መቀደስ ካለው ይገባል። እለ የሐርምዋ ለደብተራ ፡ (ዕብ፲፫ ፡ ፲)።
፡ ማረም መንቀል፤ ማውገዝ መለየት፤ ምስጢሩ መከልከል ካለው ይገባል። አነ ሐረምኩ ወአውገዝኩ። ንሔርም እምቅድስት ቤተ ክርስቲያን እለ ይገብሩ ዐመፃ ፡ (ቀሌ)።
ሐሪሥ ፡ (ዐረ ሐሪሽ። ዕብ ሒሬስ፤ ብርቱ) ዝኒ፤ ከማሁ፤ ጐሽ፤ አውራሪሥ፤ ቁርበቱ ጋሻ የሚኾን። ግዙፈ ማእስ ማእስ፤ ይቡሰ ማእሰ፤ ጽኑዐ ማእስ ማለት ነው። ሐሪስ ተብሎ በሳት ሰ ሲጣፍ ግን ምስጢሩ ዕርሻና በሬነት ይኾናል። ይፈቅድኑ ይትቀነይ ለከ አርዌ ሐሪሥ ፡ (ኢዮ፴፱ ፡ ፱ ፡ ፲)።
ሐሪስ –አውራሪሥ ፤–ሐሪሥ።
ሐሪስ ሶት ፡ (ሐረሰ የሐርስ ይሕርስ። ዕብ ሐራሽ። ሱር ሕራት። ዐረ ሐረሰ ተ) ማረስ፤ ምድርን መሠንጠቅ መቅደድ፤ የረጋውን መሬት ማማሰል ማፍረስ ማብሰል ማለስለስ ለዘርና ለተክል ማዘጋጀት። ለርሻ ሥራ ፬ ስም አለው፤ ገመሳ ፥ ግልጋሎ ፥ ዕየማ ፥ ዘር። ገበረንና ተገበረን እይ፤ የዚህ መንቲያ ነው። ቦኑ ኵሎ አሚረ የሐርስ ዘየሐርስ። የሐርስ ለከ ትልመ ገራውሂከ። የሐርስዋ ለጽዮን ከመ ገራህት። ኢትሕርስ በአድግ ወበላሕም ኅቡረ ፡ (ኢሳ፳፰ ፡ ፳፬። ኢዮ፴፬ ፡ ፲። ሚክ፫ ፡ ፲፪። ዘዳ፳፪ ፡ ፩)።
፡ ሸክላ መሥራት፤ ምስል ማፍሰስ መጥረብ መቅረጥ። ክፉ ማሰብ መመኘት ማድረግ፤ መጠንቈል ማሟረት ምትሀት ማሳየት። ኢትሕርስ ሐሰተ ላዕለ ቢጽከ ፡ (ሢራ፯ ፡ ፲፪። ኢዮ፬ ፡ ፯)።
ሐሪር ፡ (ዐረብ) ሐር፤ ጥሩ ነጭ ፈትል፤ የሐር ትሎች ቱት የሚባል ቅጠል እየበሉ እንደ ሸረሪት፤ የሚፈትሉትና የሚያዘጉት። ከሐር ፈትል የተሠራ ጥሩ ልብስ። ዘይለብስ ሠቀ ምስለ ዘይለብስ ሐሪረ። መንጦላዕት ዘሐሪር ፡ (ፊልክ ፡ ፵፱። አዋል)።
ሐሪር ሮት ፡ (ሐረረ የሐርር ይሕርር ፤ ሐለለ። ዐረ ሐረ። ዕብ ሓራር) ፤ ማረር መትከን ፤ መክሰል መቃጠል ፤ መሞቅ መተኰስ። መናደድ መቈጣት። ይሕርር ሥጋሃ ፡ (ሕዝ፳፬ ፡ ፲)። ሐራ መውጣት ፤ ነጻ መኾን። ዐምሐራን ተመልከት።
ሐሪው ዎት ፡ (ሐረወ የሐሩ ይሕሩ። ዐረ ኀሪአ፤ ዐራ) መቈፈር መማስ፤ ለመንቀል ለማፍለስ። ማራት መኵሳት፤ ዐዛባ መዛቅ መጨማለቅ። ሕር ሕር ማለት፤ እንደ መጠጫ መንደቅደቅ መንበቅበቅ፤ የጕረሮ።
ሐሪድ ዶት ፡ (ሐረደ የሐርድ ይሕርድ። ዕብ ሐራድ፤ ፈጠነ ፈራ። ዐረ ሐረደ፤ ወጋ በሳ) ማረድ መጕረድ፤ በስለት መምታት መገዝገዝ፤ መቍረጥ መበጠስ፤ ያንገትና የራስ ፡ (ዘፍ፳፪ ፡ ፲። ፴፯ ፡ ፴፩። ዘፀ፲፪ ፡ ፮)። ወሐረደ ሎቱ አልሕምተ ወአባግዕ ብዙኀ። የሐረዶ ክሣዶ። ሕርድ ወብላዕ። ኢትብልዑ እንስሳ ዘእንበለ ይሕርድዎ ሕያዎ ፡ (፪ዜና ፡ ፲፰ ፡ ፪። ዘሌ፭ ፡ ፰። ግብ፲ ፡ ፲፫። ቄድር ፡ ገ፹፰)። መስረቅ መቅጠፍ ማታለል፤ መጥፎውን መልካም ማስመሰል። ጥምቀት ዐረደኝ እንዲሉ።
ሐሪግ ጎት ፡ (ሐረገ የሐርግ ይሕርግ። ዕብ ሐራግ፤ ዘለለ ፈነጨ። አራግ፤ ሳራግ፤ ታታ) መሳብ መምዘዝ፤ መጠምዘዝ መጠቅለል፤ የሐረግ። መፍተል ማክረር ማጠንጠን፤ የጥጥ የፀምር የክታን። ሐረጉን ፈትሉን መታታት መሥራት ማቈላለፍ፤ የጐታ የቅርጫት የሹራብ የወንፊት። ሐረግ መጣል፤ ማስመሰል፤ በጥልፍ በስፌት በሥዕል በጽፈት መጐንጐን መሸረብ። ጕንጕን ሐረግ እንዲሉ።
ሐሪጸ ሐሊብ ፡ (ዕብ ሐሪጼይ ሄሐላብ) ያይብ ልጥልጥ፤ ጅብና ከወተት ከርጎ የሚሠራ፤ ቍራሽ ታናናሽ ክፍል። ግብነትን እይ፤ ከዚህ ጋራ ፩ ነው ፡ (፩ነገ ፡ ፲፯ ፡ ፲፰)።
ሐሪጽ ጾት ፡ (ሐረጸ የሐርጽ ይሕርጽ ፀ። ጠሐነ፤ ደሐየ።ዕብ ሐሬጽ፤ ቈረጠ ከፈለ) መፍጨት፤ መከካት መገ(ከ) ርደ(ተ) ፍ ማድቀቅ፤ ማላም መሰለቅ፤ መቀጥቀጥ መደቈስ። ሐረጾ ወአድቀቆ። ተሐርጽ እምኔሁ ድቁቀ። አሐርጾሙ ከመ ጸበል። ክልኤቲ የሐርጻ በአሐቲ ማሕረጽ። ንሣእ ዐጽቀ በለስ ወሕርጽ ፡ (ዘፀ፴፪ ፡ ፳። ፴ ፡ ፴፮። መዝ ፡ ፲፯። ማቴ፳፬ ፡ ፵፩። ኢሳ፵፩ ፡ ፲፭)። ማረጥ፤ ዐራጣ መስጠት፤ የዶቄት። ደም መቍረጥ፤ ጽጌ ማጣት፤ የሴት።
ሐሪጽ ፡ ዶቄት፤ ዐመድ ትቢያ፤ ከሚፈጭና ከሚደቈስ ነገር የሚወጣ ውጤት። ነሥአት ሐሪጸ ወሎሰት። ሐሪጸ ሰገም። እምሐሪጽ ልዉስ። ወደይክዎ ለውእቱ ሐሪጽ ውስተ ነቅዕ ዘይወርድ ፡ (፩ነገ ፡ ፳፰ ፡ ፳፬። ዘኍ፭ ፡ ፲፭። ሆሴ፯ ፡ ፬። ዘዳ፱ ፡ ፳፩)።
ሐሪፍ ፡ ጸደይ፤–ኀሪፍ።
ሐሪፍ ፎት ፡ (ሐረፈ የሐርፍ ይሕርፍ። ዕብ ዓራፍ፤ ራዐፍ። ዐረ ረዒፈ) መንጠብ፤ መውረድ መንጠፍጠፍ፤ መመንጨት መፍሰስ መጕረፍ። መፍላት መገንፈል፤ መኵረፍረፍ፤ ዐረፋ ማውጣት። ማልገግ መቈበር፤ ቈበርን ዐረፋን መድፈቅ፤ ከድካም ከደዌ የተነሣ እንደ በቅሎና እንደ በሬ እንደ ጋኔናም። ሠወነን እይ።
ሐራ [1] ፡ ጭፍራ፤–ሐሪር ሐረረ።
[2] ፡ ሐርነት፤ ነጻ። ጨዋ፤ ነጻነት ያለው። ጭፍራ፤ ሰራዊት። ሊቀ ሐራ። ሐራ ሰማይ።
ሐራሚ ፡ (ሚት ምያን ያት፤ ረምት) የሚተው የሚያርም ሕርም ባይ፤ ከልካይ ተከልካይ። ቀዳሽ አገልጋይ። ዐራሚ ነቃይ፤ የሚያወግዝ የሚለይ። መጽሐፍ ግን በሐረመና በሐራሚ ፈንቃ ተሐረመ ተሐራሚ ይላል፤ አያሰኝም ፡ (ሮሜ፲፬ ፡ ፭ ፡ ፮)። ኢትበል በእንተ እግዚ ተሐረምኩ። ኢይትሔረሙ በእንተ እግዚ። መባልዕት ዘይትሔረሙ አይሁድ እምኔሁ።ዘይትሔረም አውስቦ። መነኮሳት ተሐራምያን ፡ (ሢራ፲፭ ፡ ፲፩።ፊልክ ፡ ፺፩። መቃ ፡ ገ፲፭። ቀኖ ፡ ግንግ። ገድ ፡ ተክ)።
ሐራሲ ፡ (ሲት ስያን ያት፤ ረስት) የሚያርስ ዐራሽ ገበሬ፤ ጃን ገበር። ሐራሲ በዕርፈ መስቀል። ተኀፍሩ ሐረስት። ዲበ ወፍረ ሐረስት። እስመ መፍቀሬ ሐረስት ውእቱ ፡ (ድጓ። ዮኤ፩ ፡ ፲፩። መክ፭ ፡ ፰። ፪ዜና ፡ ፳፮ ፡ ፲)።
፡ ሸክላ ሠሪ፤ ጠቢብ ብልኀተኛ፤ መሠሪ አስማታም፤ ሟርተኛ። ወገብሩ ከማሁ ሐራስያነ ግብጽ በሥራያቲሆሙ ፡ (ዘፀ፯ ፡ ፲፩። ፰ ፡ ፯ ፡ ፲፰። ዘሌ፳ ፡ ፳፯)።
ሐራዊ ፡ የጨዋ ወገን፤ የጭፍራ ወገን። ሐራዊ ዘክርስቶስ ፡ (ፊልክ። ዮሐ ፡ ፲፱ ፡ ፳፫)።
ሐራውያ ሐርዌ ፡ (ብ አሕርው) ሕሪያ ከርከሮ፤ ሥር እየማሰ እያፈለሰ የሚበላ ጥርሳም ጥቍር የበረሓ ዐሣማ፤ ከቤት ዐሣማ የተለየ፤ ትግሮች መፍለስ ይሉታል። ለቤት ዐሣማም ይነገራል፤ ሐሣማንና ሐንዘርን እይ። ስምንቱም እንደ ዶርሆ ነው፤ ሴትና ወንድ ያስተባብራል። ሐራውያ ሐቅል ለዋው። ወአርኩሳ ሐራውያ ሐቅል። እመ ይዌልጥ ሐራውያ ጸጕሮ ከመ ፀምር። ወሐራውያኒ ተኀፂባ ገብአት ዲበ ጸብር። መራዕየ አሕርው። ዘይሴሰዩ አሕርው ፡ (፪ነገ ፡ ፲፯ ፡ ፰። መዝ ፡ ፸፱። ኩፋ ፡ ፴፯። ፪ጴጥ ፡ ፪ ፡ ፳፪። ማር፭ ፡ ፲፩። ሉቃ፲፭ ፡ ፲፮)።
ሐራዲ ፡ (ዲት ድያን ያት) የሚያርድ ዐራጅ፤ በጋማች። ፋደት ፋሮ የማር ሌባ፤ ቀፎ እየደፋ ማር የሚበላ የውሻና የድመት ዐይነት፤ ግም ክርፋታም።
ሐራጥቃ ፡ (ጽር ኤሬቲኪ) መናፈቅ ጠዋየ ሃይማኖት ባህሉና ትርጓሜው ከመጽሐፍ ከንባብ የማይገጥም፤ መጻሕፍት እወ ያሉትን አልቦ፤ አልቦ ያሉትን እወ የሚል፤ የርሱን ሐሳብ ብቻ የሚከተል፤ የጨዋ የወታደር ዐይነት፤ ነገሩ ከጨዋ የሚስማማ ከሊቃውንት የማይስማማ፤ እንዳርዮስ እንደ ንስጥሮስ እንዳውጣኪ ያለ። ባለመጣፎች ግን ለይተው ተለወጠ የሚል ይሉታል፤ አንድ ባሕርይ የሚሉን ያሳያል። በእንተ ሐራጥቃ ዘተግህደ ዕልወቱ። ዘተወክፉ ጥምቀተ እምሐራጥቃ አው ቀረቡ ቍርባኖሙ ፡ (ፍ ፡ ነ ፡ ፫። ፭። ፈ ፡ መ ፡ ፳፯ ፡ ፯)።
ሐራጺ ፡ (ጺት ጽያን ያት፤ ረጽት) የሚፈጭ ፈጭታ፤ ባለወፍጮ፤ ዶቄት ሸያጭ።
ሐራጻ ፡ የዶቄት ወለድ ፍድፋጅ፤ የውጤቱ ትርፍ፤ ይልቁንም የጤፍ። ለብር ወለድም ይኾናል፤ ርዴ ብሎ ዐራጣ ማለት ዐማርኛው ከዚህ ወጥቷል።
ሐርማዝ ሐርመዝ ፡ (ዐረ ሂርሚስ። ትግ ሐርመስ፤ ዝኆን) አውራሪሥ፤ ባላንድ ጕጭማ ቀንድ፤ ቀንዱ ባፍነጫው የሚበቅል ራሰ ጐዳ አፍንጫ ቀንዳ። ጐሽ የበረሓ በሬ። ማኅደረ ሐርማዝ ወደስከን። አዘዘ ከመ ይግበሩ ሎሙ ሠለስተ ሣጹነ እምአዕፅምተ ሐርመዝ፤ ወይግንዝዎሙ። ወገብረ ሰሎሞን መናብርተ ብዙኃተ እምአቅርንተ ሐርመዝ ፡ (አዋል። ስንክ ፡ ግን፲። ጊ ፡ ወ ፡ ሐ ፡ ገ፸፱)።
ሐርማዝ ፡ ዝኆናዊ አሞራ። ዖፍ ዘይሰመይ ዖፈ ሐርማዝ፤ወበውስተ ዝንቱ ብሔር ሐርመዛት ዐቢይት ፡ (ጊ ፡ ወ ፡ ሐ ፡ ገ፲፭)።
ሐርስ ፡ ሟርት ጥንቈላ፤ አስማት ምትሀት፤ አፍዝ አደንግዝ። ዘሥራይ ወዘሐርስ። ሰብአ ሐርስ ፡ (ዘዳ፲፰ ፡ ፲፩። ዘሌ፳ ፡ ፮)። በሐርሰ ፈንታ ሐረስ ሐሪስ ሐራስ ይላል፤ ኹሉም ስሕተት ነው፤ አያሰኝም።
ሐርብ ፡ (ዐረ። ዕብ ሔሬብ፤ ሰይፍ) ጦርነት ውጊያ፤ ሰልፍ። ዐ(ሐ) ርበኛ ማለት ዐማርኛው ከዚህ ወጥቷል።
ሐርተመ ፡ (የረተመ ዲቃላ፤ ወይም የሐረመ ስሯጽ) ጠፋ ተበላሸ ጐሰቈለ፤ ከሳ ጠቈረ ፊቱ ተሰበረ፤ ወራዳ ምናምንቴ ኾነ። ሐርተመ ተዓይን። ኀሰርነ ወሐርተምነ። የሐረትም ዕጓለ መሕያው። ተሐረትም ምክዕቢተ። ለአብ ኃጥእ የሐረትሙ ውሉዱ ፡ (ኤር፬ ፡ ፳። ሚክ፪ ፡ ፬። ኢሳ፭ ፡ ፲፭። ሢራ፳፪ ፡ ፭። ፵፩ ፡ ፯)።
ሐርገፅ ፡ (ፃት። ረገፀ) ዐዞ የባሕር አውሬ ያሣ ዐይነት መጋዝ ጥርስ፤ ሰው እየነጠቀ የሚጐርሥ እንቅልፋም እንጕልቻም፤ እንቅልፍ የሚረግጠው የሚደብተው ማለት ነው። ተሐርገፀ እንዲል ሐባብ፤ አንቀላፋአንጐላቸ ሲል። ዐዞ ማለትም ዕዙዝ ዐዚዝ ማለት ነው፤ ረገፀንና ዐዘዘን እይ። ፡ (ሙሾ፤ ዐዞ ስለ ነጠቀው ልጅ እኅቱ እናቱና አባቱ) ላንድ ቀን ትእዛዝ ሰዉ ይመረራል፤ የኔ ወንድም ታዞ አባይ ላይ ይኖራል። ግባተ መሬቱን አትድገሙ እናንተ፤ ታዞ ኺዷል እንጂ፤ ልጄ መቼ ሞተ። ልጄን አትጥሉብኝ ቢያዛችኹ ተሹሞ፤ አ(ዐ) ዞ አያውቅምና ከዚህ አስቀድሞ። መሠጦ ሐርገፅ። አክይስት ወዐናብርት ወሐርገፃት። ወረዱ ኀበ ፈለግ፤ ወሀለዉ ውስቴቱ ሐርገፃት፤ ወቆመ አሐዱ እምኔሆሙ ማእከሎሙ ፡ (አቡሻ ፡ ፶። መቃ ፡ ገ፲፪። ፊልክ ፡ ፺፱)። በሐርገፅ ፈንታ ሐገፅ ይላል፤የጣፊ ግድፈት ነው ፡ (ዘሌ፲፩ ፡ ፳፱)።
ሐርጌ ፡ (ብ አሕሩግ፤ ሐራጊት) የቀንድ ከብት፤ ወጠጦ ኰርቤላ ቍርንቢ፤ የበግ የፍየል አውራ ሙክት። ሐረገ ቀርን፤ ዘቀርኑ ይመስል ሐረገ፤ ቀንደ ጠማማ ቈልማማ ማለት ነው። ሐርጌ እምውስተ አባግዕ። ሐርጌ እምውስተ አጣሊ። ዘበደመ በግዕ ሐርጌ ወላሕም ፡ (ዘሌ፭ ፡ ፲፭። ፬ ፡ ፳፫። ቅዳ ፡ ሕር)። መጋዝእት ወአሕሩግ ዐቢያን፤ አሕሩገ በግዕ። ሐራጊት ሠናያን። ሐራጊት ሥቡሓን። ሐራጊተ ጠሊ ፡ (ገድ ፡ ተክ። ኤር፴፪ ፡ ፳። ሚክ፭ ፡ ፯። ፪ዜና ፡ ፳፱ ፡ ፳፩)። እንደ ዕብራይስጡ ሲፈታ ግን፤ የሚዘል የሚፈነጭ፤ ሯጭ ፈርጣጭ ያሰኛል። ፪ኛም በሆይ ፡ (ሀራግ) ሀረገ ብሎ ዐረደ ገደለ ይላልና፤ ሀርጌ ተብሎ በሄ ሲጣፍ ፍሪዳ መሥዋዕት ያሰኛል።
ሐቈነ ፡ አረጋ፤–ዐቍን ዐቈነ ዕቋን።
ሐቂር ሮት ፡ (ሐቀረ የሐቅር ይሕቅር። ዕብ ሐቃር። ዐረ ሐቀረ፤ ማሰ) መቈፈር መመርመር፤ ምድርን ነገርን የሰውን ጠባይ። ግብሩን ምስጢሩን ካወቁ በኋላ ማስተሐቀር ቅር ማሰኘት፤ መናቅ ማቃለል መንቀፍ ማጸየፍ። መጽሐፍ ግን በሐቀረ ፈንታ እንዳማርኛው አስተሐቀረ ይላል፤ አስተ ተርጓሚና ጣፊ ፍችውን አቃለለን ሲያዩ ያገቡት ነው፤ ሐየጸንና ዐገሠን ፈሥሐን እይ። ግእዝ መሀረ ያለውን ዐማርኛ አስተማረ እያለ ልማድ ይጨምራል፤ የግእዝና ያማርኛ ልማድ ካንዳንድ ጊዜ በቀር ወትሮ አይስማማም። ኢይምሰልከ ዘአስተሐቀርኩከ። እለ ያስተሐቅሩ ሕጎሙ። ኢትትመካሕ በአስተሐቅሮ አቡከ። አስተሐቅሮታ ለእሙ። በኀበ ጠቢብ ዕጹብ አስተሐቅሮ ፡ (ዘፍ፴፩ ፡ ፴፭። ሶፎ፩ ፡ ፲፪። ሢራ፫ ፡ ፲፩። ፳፩ ፡ ፳፬)።
ሐቂቅ ቆት ፡ (ሐቀ፤ ሐቀቀ የሐቅቅ ይሕቅቅ። ሐገገ) ማብዛት ማሳነስ ጥቂቱን ብዙ ብዙውን ጥቂት ማድረግ፤ መቍረጥ መወሰን። ሐገገን፤ እይ፤ የዚህ መንቲያ ነው። ማፋቅ፤ ሕቅ ሕቅ ማለት ፡ (ዐማርኛ)።
ሐቂፍ ፎት ፡ (ሐቀፈ የሐቅፍ ይሕቅፍ። ዐረ ሐቀፈ፤ ደነነ። ዕብ ሀቄፍ) ማቀፍ፤ የሰውን ገላ በ፪ እጅ ጠምጥሞ መያዝ መቀበል፤ ራስን ግንባርን መደገፍ፤ እጅን ማጣመር ማስተላለፍ ከሕፅን ማግባት፤ መክበብ ማጠር ከማኽል ማግባት። ሐቀፎ ወሰዐሞ። የማኑ ተሐቅፈኒ ወፀጋሙ ታሕተ ርእስየ። አብድ ሐቀፈ እዴሁ ወበልዐ ሥጋሁ። ዕግትዋ ለጽዮን ወሕቀፍዋ ፡ (ዘፍ፳፱ ፡ ፲፫። ማሕ፪ ፡ ፮። መክ፬ ፡ ፭። መዝ ፡ ፵፯)። እጅና ክንፍ ተመሳሳዮች ስለ ኾኑ ለአዕዋፍም ይነገራል። ከመ ዖፍ እንተ ተሐቅፍ አንቆቅሖ። ወከመ ንስር የሐቅፍ ዕጐሊሁ በገበዋቲሁ ፡ (ዲድ ፡ ፮። ዘዳ፴፪ ፡ ፵፩)።
ሐቃል ፡ (ላን ላት። ሐቃሊ፤ ፡ (ሊት ልያን ያት) ) ዐራሽ ዘላን፤ ባላገር። ለሐቃል ወለግዩር ፡ (ዘፀ፲፪ ፡ ፵፱)።
፡ ገልቱ አረመኔ፤ ፊደል የሌለው ቋንቋው ያልጠራ በርበር። ሐቃል ወሀገሪት ፡ (ሮሜ፩ ፡ ፲፬። ቆላ፫ ፡ ፲፩)።
፡ በረኸኛ ቦለድ፤ ዐዳኝ ወንበዴ። ዔሳው ውእቱ ብእሲ ድሩክ ወሐቃላዊ ወጸጓር። እስመ ብእሴ ሐቃላዊ ውእቱ ወነዓዊ።ዕደው ሐቃልያን ወመደንግፃን ፡ (ኩፋ ፡ ፲፱። መሳ፱ ፡ ፬)።
ሐቃዪ ፡ (ዪት ይያን ያት፤ ቀይት) የሚያፋጭ የሚያጋጭ፤ የሚያንቀጫቅጭ፤ ቈርጣሚ ጐርዳሚ፤ የቈሎ ያጥንት።
ሐቃፊ ፡ (ፊት ፍያን ያት፤ ቀፍት) የሚያቅፍ ዐቃፊ፤ ተቀባይ።
ሐቄ ሐቌ ፡ (ብ ሐቍያት። ዐረ ሐቅው) ወገብ፤ የሕፅን አጠገብ፤ የትጥቅ ሙያ ከጭን በላይ ከሕፅን በታች መካከሉ ዙሪያው ግራና ቀኙ። ሕልጽን እይ፤ ምስጢሩ መፋጫ መጋጫ መወሳወሻ ማለት ነው። ቅንት ሐቌከ ከመ ብእሲ። ኦ ዘታወፅኦ ለሕፃን እምሐቌ ብእሲ ወትፌንዎ ውስተ ከርሠ ብእሲት። እለ ወፅኡ እምሐቌሁ ለአብርሃም ፡ (ኢዮ፴፰ ፡ ፫። ቅዳ ፡ አት። ዕብ፯ ፡ ፭)። በሕፅን ፈንታ ሐቌ ይላል፤ አያሰኝም። ለምንት ተሐቅፍ ሐቌ ዘማዊት ፡ (ምሳ፭ ፡ ፳)።
ሐቅ ፡ (ዐረ ወትግ። ዕብ ሖቅ) ሕግ፤ እውነት ርግጥ አማን።
ሐቅል ፡ (ብ አሕቁ(ቃ) ል፤ ላት። ዕብ ወሱር ሐቅላእ። ዐረ ሐቅል) ገራህት፤ ዕርሻ ቅብቅብ፤ ዱር በረሓ ምድረ በዳ፤ ዐልፎ ዐልፎ ዕርሻ ያለበት። ሐቅለ ድማኅ፤ ገራህተ ደም ብሂል። ሐቅል ውእቱ ብሔር። ወመጽአ ዔሳው እምሐቅል ርኂቦ። ወሖረ ይንበር ውስተ ሐቅለ ሞአብ። ወተመይጣ እምሐቅለ ሞአብ፤ ምድር ፡ (ግብ፩ ፡ ፲፱። ማር፮ ፡ ፴፭። ኩፋ ፡ ፳፬። ሩት፩ ፡ ፩ ፡ ፪ ፡ ፮)።
፡ ሰፊ ሜዳ ዘብጥ ረባዳ፤ ግራ ቀኙ ተራራ የኾነ፤ የወንዝ ዳር የተራራ እግር። ምስጢሩ ምድረ በዳ ካለው ይገባል። «ሐቅለ ሲና፤ ሐቅለ ቃዴስ፤ ሐቅለ ዱራ፤ ሐቅለ ሰናዖር» አሕቃሊሃኒ። ወርእየ አሕቃላቲሁ። አሕቃላተ ቢድው። አሕቁል። ኮከበ አሕቁላት ወገዳማት ፡ (ኢሳ፶፩ ፡ ፫። ዘፍ፲፫ ፡ ፫። ዮኤ፪ ፡ ፳፪። ዕር ፡ ኢሳ፮ ፡ ፫። ግንዘ)።
ሐቅሎ ሎት ፡ (ሐቀለ ይሔቅል የሐቅል) መሰምረት ከዱር ከበረሓ መግባት፤ ለማረስ ለማደን ለመቀማት።
ሐቅር ፡ (ራት) ቅርታ ነቀፌታ፤ ንቀት።
ሐቅይ ዮት ፡ (ሐቀየ የሐቂ ይሕቂ። ዐረ ሐረቀ። ሱር ሐሪቅ። ዕብ ሐራቅ) ማፋጨት ማጋጨት ሢጠጥ ሢጠጥ ማድረግ፤የጥርስ። ከቍጣ ከንደት ከመጐምዠት ከሥቃይ ብዛት የተነሣ። ሐቀዩ ስነኒሆሙ ላዕሌየ። ከመ ዘየሐቅዩ አስተዳለዉ ይብልዑ። ኀበ ሀሎ ብካይ ፡ (መዝ ፡ ፴፬። ሢራ፶፩ ፡ ፫። ማቄ፳፭ ፡ ፴)።
፡ መቈርጠም መጐርደም፤ መስበር ማድቀቅ ማንቀጫቀጭ። አዕፅምተ ሰብእ ተሐቂ። የሐቅየኒ አዕፅምትየ ፡ (ምሳ፳፬ ፡ ፳፫። ኢዮ፲፬ ፡ ፳)።
ሐቌ ፡ ወገብ፤–ሐቀየ።
ሐበሰ ፡ (ዐረብ) ዐበሰ አጋዘ፤ አሰረ ከወህኒ አገባ።
ሐብረ ፡ ዐበረ፤–ኀቢር ፡ ኀብረ።
ሐበበ [1]:-ሰደበ፤–ሀቢብ ሀበ ሀበበ።
[2]:-ጠመቀ ረገጠ፤–ኀቢብ ኀበበ።
ሐበወ ፡ ወጨፈ፤–ሀቢው ሀበወ።
ሐበዘ ፡ ጋገረ፤–ኀቢዝ ኀበዘ።
ሐቢ ፡ (ቢት ብያን ያት፤ በይት) ዋስ መድን ተያዥ። ጠባቂ ሹም አለቃ ወኪል ምስለኔ እንደ ራሴ። ሐቤ ምእት። እሉ እሙንቱ ሐበይቶሙ ለክልኤቱ ምእት መላእክት። ይኩኑክሙ ሐበይተ ወመሳፍንተ ፡ (ማቴ፰ ፡ ፭። ሔኖ፮ ፡ ፰። ዘዳ፩ ፡ ፲፭)።
ሐቢል ሎት ፡ (ሐብለ፤ ሐበለ የሐብል ይሕ(ብ) በል። ዕብ ሐባል። ዐረ ሐበለ) ማበል መዋሸት፤ ፈጥሮ መናገር፤ ማታለል መሸንገል፤ ማሳት መጕዳት። መግመድ መፍተል፤ በገመድ ማሰር፤ መሳብ መጐተት። ቀላድ መጣል በገመድ መስፈር መለካት መክፈል፤ የምድር። ሐንበለን እይ፤ የዚህ ስሯጽ ነው። አኮ ሠናይ ለመኳንንተ ጽድቅ ሐቢል። የሐብሉ አዕርክቲሆሙ። ብእሲ እኩይ የሐብል አዕርክተ ፡ (ምሳ፲፯ ፡ ፳፯። ፳፮ ፡ ፲፱። ፲፮ ፡ ፳፱)።
ሐቢብ [1] ፡ (ዐረ እልሐቢብ) ወዳጅ ፍቁር።
[2] ፡ ቦት፤ (ሐበ፤ ሐበበ የሐብብ ይሕብብ። ዐረ ሐበ) መውደድ ማፍቀር፤ በፍቅር መቃጠል። መጽሐፍ ግን በሐበበ ፈንታ ተሐበ ተሐበበ ይላል፤ እያሰኝም። እለ ይትሐበቡ በተባዕት ፡ (ቀሌ። ፩ቆሮ ፡ ፮ ፡ ፱)። ማፍራት፤ ፍሬ መያዝ። ሐንበበን እይ።
ሐቢጥ ጦት ፡ (ሐብጠ፤ ሐበጠ የሐብጥ ይሕብጥ። ዐረ ሐቢጠ) ማበጥ፤ መነፋት፤ ፡ (ጥቀ) መቀብጠጥ፤ መቍሰል ከበትር ከደዌ የተነሣ። እስከ የሐብጥ ሥጋሁ። ተፀምደ በቀዊም እስከ ሐብጠ እገሪሁ። ለእመ ሐበጠ አአሉ፤ ለዘሐበጠ እስኪቱ ፡ (ቄድር። ስንክ ፡ ታኅ፲፪። ፳፭። መ ፡ ፈ)። በሐበጠ ፈንታ ተሐበጠ ይላል፤ አያሰኝም። ቦ ለ ይትሔበጡ በትዕቢት ፡ (ተረ ፡ ቄር ፡ ፲፱)።
ሐባሊ ፡ (ሊት ልያን ያት) የሚያብል፤ ዐባይ ዋሾ። ሐባሊ ሶበ ተአምኖ ይትጓሐለወከ። ሐባሊ ለይትነፃኅ ፡ (ፈላስ ፡ ገ፴፮። ቅዳ)። ገማጅ አሳሪ፤ ሰፋሪ።
ሓባሪ ፡ (ሪት ርያን ያት) የሚያቀልም፤ የሚያልል፤ ቀለም አግቢ።
ሐባዪ ፡ (ዪት ይያን ያት፤ በይት) ጠባቂ ከልካይ፤ ሿሚ ወካይ፤ አዋሽ ዋስ መድን ሰጭ።
ሐባጢ ሕቡጥ ፡ ያበጠ የተነፋ፤ ቅብጥጥ ያለ። በሕቡጥ ፈንታ ቅቡጥ ይላል፤ የጣፊ ስሕተት ነው። ዘይከውን ጽንፈ ዐይኑ ቀይሐ ወቅቡጠ ፡ (መ ፡ ፈ)።
ሐብለ ፡ ደፈረ፤–ኀብሎ ኀበለ።
ሐብለት ፡ (ታት) እንጥልጥል፤ የዦሮ ያንገት ጌጥ ሽልማት፤ጕትቻ ድሪ፤ የወርቅ የብር ሰንሰለት። ሕልቀታተ ወሐብለታተ ፡ (ዘፀ፴፭ ፡ ፳፪)። በሐብለት ፈንታ ሐብላት ይላል፤ የሐብል ብዢ ነው ፡ (መሳ፰ ፡ ፳፮። ፩ጢሞ ፡ ፪ ፡ ፱)።
ሐብለየ ፡ (ተቀ ግ) ከዳ፤ ተተነኰለ። ክፋ ዐሰበ። ተናገሩ ምስሌሆሙ በእኩይ ወሐብለይዎሙ። ሐብለይዎ ወገብሩ ላዕሌሁ ምክረ። ከመ የሐብልይዎሙ ለአግብርቲሁ ፡ (ኩፋ ፡ ፴ ፡ ፴፬። መዝ ፡ ፻፬)።
፡ በዘበዘ፤ ዘረፈ ገፈፈ፤ ቀማ ወሰደ፤ በተንኰል በኀይል፤ በግድ በገመድ። የሐብልዮ ነኪር ኵሎ ተግባሮ። ይበርብርዎሙ ወየሐብልይዎሙ። ወሐብለይዎሙ ለግብጽ ፡ (መዝ ፡ ፻፰። ኢሳ፩ ፡ ፮። ዘፀ፫ ፡ ፳፪። ፲፪ ፡ ፴፪)። በሐብለየ ፈንታ ተሐብለየ ይላል፤ ስሕተት ነው። እነሥት ጸቈኖ ወይትሐበለይዎ። ወእለሰ ይነብሩ ቤጤሌዋ ወረዱ ውስተ ትዕይንቶሙ ለአሶር ወተሐብለይዎሙ ወብዕሉ ፈድፋደ ፡ (ኢሳ፭ ፡ ፭። ዮዲ፲፭ ፡ ፮)።
ሐብል ፡ (ብ አሕባል፤ ላት። ዕብ ሔቤል። ሱር ሐብላ። ዐረ ሐብል) በቁሙ፤ ገመድ ቀላድ፤ ከቃጫ ከናጫ ፥ ከጓሳ ከገርሣ ፥ ከጭራ ከጭረት ፥ ከቈርበት ከዥማት ፥ ከእንሰት ከልጥ፤ ከክታን ከጥጥ ፥ ከፀምር ከሐር፤ ከሌላውም ኹሉ ተፈትሎ ተከሮ የሚሠራ፤ ጠፍር፤ ሰንሰለት፤ ወጥመድ። ሐብል ነዋኅ። ሐብለ ዐጌ። ሐብለ አነዳ። አሕባለ ሥርው ደቃቃት። አሕባለ ቢሶንስ። አሕባለ ጠፈር። ኅቡእ ዲበ ምድር ሐብሉ ፡ (ኢሳ፭ ፡ ፲፰። ሕዝ፵ ፡ ፫። ስንክ ፡ ጥቅ፲፯። መቃ ፡ ገ፳። አስቴ፩ ፡ ፮። ገድ ፡ ላሊ። ኢዮ፲፰ ፡ ፲)።
፡ ርስት ቀላድ፤ ቦታ ወዠድ፤ የርስት የመሬት ክፍል፤ ወገን። ወድቀ ሐብሎን። ትኩንክሙ ሐብለ ርስትክሙ። ወእስራኤልኒ ሐብለ ርስቱ። ፡ (ኢያ፲፯ ፡ ፭። መዝ ፡ ፻፬። ዘዳ፴፪ ፡ ፱)።
ሐብስ ፡ በቁሙ የግዞት ቤት ወህኒ። ሐብስ ዘይቤ ቤተ ጽልመት ፡ (ጥሬ ፡ ሰዋ)።
ሐብረተ ፡ (ተቀ ግ) ወለወለ ሰነገለ፤ ዐደሰ ኰላ፤ የማዕደናት። ወርቅ እመ ኢሐብረትዎ ኢይበርህ። ጽህርት እንተ ኢሐብረትዋ ዛሕላ። ለመኑ ዛቲ ሰይፍ ዘየሐበርትዋ ፡ (መል ፡ ኤር፳፫። ሕዝ፳፬ ፡ ፮። ፈላስ)።
ሐብራቲ ፡ (ቲት ትያን ያት) የሚወለውል፤ ወልዋይ ሰንጋይ።
ሓብሮ ሮት ፡ (ሓበረ የሓብር የሓብር) ማቅለም፤ ቀለም ማግባት መንከር፤ በብዙ ዐይነት ቀለም መሸለም ማስጌጥ ማንቈጥቈጥ፤ መልክ ማውጣት፤ ሥዕል መሣል ሐረግ መጣል። ባለቅኔዎች ግን ቤቱ የባረከ ሲኾን ኆበረ ብለው በኖለወ ቤት በኀርም ይገሱታል። ከጥሬውና ከቅጽሉ በቀር አንቀጹ አይገኝም።
ሐብቀቀ ሐብቈቈ ፡ (አብከከ፤ በኪክ በከ) አሳደፈ አረከሰ፤ አበላሸ ከንቱ አደረገ፤ በጠበጠ አደፈረሰ፤ ቀላቀለ ደባለቀ፤ አወከ አሸበረ።
ሐብአ ፡ ዐባ ሰወረ፤–ኀቢእ ኀብአ።
ሐብይ ዮት ፡ (ሐበየ የሐቢ ይሕቢ። ዐረ ሐባ) መጠበቅ፤ መከልከል። መሾም መወከል። ማዋስ፤ ዋስ መድን ቀለብ የሚበቃ ምግብ መስጠት፤ ዕልፍ ትርፍ የሌለው የሚገባ ነገር ስላምታ ግብር ማቅረብ። መጽሐፍ ግን በሐበየ ፈንታ አሕበየ ተሐበየ ይላል፤ አያሰኝም። ወአሕበዩ ሎቱ በተአዝዞ። ክርስቶስ ዘዲበ ኪሩቤል ይነብር ወኵሎ ዓለመ ዘይትሐበይ ፡ (ዮሴፍ። መዋሥ)።
ሐተታ ፡ በቁሙ፤ ምርምር አመራመር፤ ምርመራ ጥየቃ፤ፍተሻ። አመ ዕለተ ሐተታ። ጽኑዐ ሐተታ የሐትትዎሙ። አመ ገብረ እግዚ ሐተታየ። ሐቲቶሙ ሐተታ ጽኑዐ ፡ (ጥበ፫ ፡ ፲፰። ፮ ፡ ፯። ኢዮ፲፬ ፡ ፫። ፈ ፡ መ ፡ ፳፫ ፡ ፮)።
- ሐቲት ቶት ፡ (ሐተ፤ ሐተተ የሐትት ይሕትት፤ ኀሠሠ። ዕብ ሐታት፤ ተሰበረ፤ ፈራ ደነገጠ።ሱር ሐቴት ፤ አስተካከለ) ፤ መመርመር መፈተን ፤ መላልሶ መጠየቅ ፤ ማስመስከር ማናገር ፤ ከዚያ በኋላ መፍረድ ፤ የዳኛ። ሕትቶሙ ለአበው። ኢትሕትት ዘኢይትከሀለከ። ኢትሒስ ዘእንበለ ትሕትት። ኢትሕትቱኒ ዘእገብር። የሐትት ኅሊና እንዘ ኢይሴአል። ሐቲተ ሕትዎ። ሕቱ ርእሰክሙ። ይሕትቱ ትዕይንት ማእከለ ቀታሎ ወማእከለ አበ ደም (ኢዮ፰ ፡ ፰። ሢራ፫ ፡ ፳፩። ፲፩ ፡ ፯። ዮዲ፰ ፡ ፴፬። ቅዳ ፡ ኤጲ። ፪ነገ ፡ ፳ ፡ ፲፰። ኪዳ። ዘኍ፴፭ ፡ ፳፬)። በሐተተ ፈንታ አስተሐተተ ይላል ፤ ስሕተት ነው። ያስተሐይጽ ወያስተሐትት መኑ እሙንቱ (ኪዳ)።
ሐታቲ ፡ (ቲት ትያን ያት) የሚመረምር፤ መርማሪ ጠያቂ፤ ዳኛ ባላጋራ። ለእመ ሐተተ ሐታቲ ወይቤ። ኢይበጽሕዎ ኅሊናተ ሐታትያን ፡ (አፈ ፡ ድ፳፮። ያዕ ፡ ዘእል)።
ሐነቀ ፡ ዐነቀ፤–ኀኒቅ ኀነቀ።
ሐነወ ፡ (ዕብ ሐናሕ። ዐረ ሐና) ሰፈረ፤ ስፍራ ያዘ፤ ጐዦ ሠራ ድንኳን ተከለ።
- ሐነጠ ፡ (ዐረብ። ዕብ ሐናጥ። ሱር ሕናጥ) ሽቱ ቀባ ለቀለቀ፤ በሽቱ ለወሰ ዐጀለ፤ የሬሳ አቀባብ፤ እንዳይፈርስ እንዳይበሰብስ በሚያደርግ በታወቀ ሽቱ። ጸዐጠን እይ፤ ከዚህ ጋራ አንድ ነው። ወሐነጠ ኖኅ ሥጋሁ በከርቤ ወበሰሊኆት ወአስቀጢን (አቡሻ ፡ ፵፰)።
ሐኑክ ፡ (ትግ) ምግብ፤ የሚጐረሥ የሚታኘክ።
ሐኒክ ኮት ፡ (ሐነከ የሐንክ ይሕንክ። ዐረ ሐነከ። ዕብ ሐናኽ) ጠልቆ ማወቅ፤ ማስተዋል። ማፈር፤ መሰቅጠጥ። ዘየአምር ሐኒከ። የሐንክዎ ወይፈርህዎ። ሰላም ለከ ገብረ ዮሐንስ ቡሩክ፤ በምሃባርከ ሐኒክ ፡ (ምሳ፫ ፡ ፲፫። ሉቃ፱ ፡ ፵፭። ስንክ ፡ ኅዳ፳፯)።
፡ መባረክ መቀደስ፤ የቤት የንዋየ ቅድሳት። ማኘክ ማላመጥ፤ መበጠስ መቍረጥ፤ የጥርስ የመኪና። ዕንካ ማለት፤ እጅ በጅ መስጠት። መጣፍ ግን በሐነከ ፈንታ አንከየ፤ ይላል፤ የተሳሳተ ነው፤ ነከየን እይ።
ሐኒጽ ጾት ፡ (ሐነጸ የሐንጽ ይሕንጽ። ነደቀ) ማነጥ መቅረጥ፤ መጥረብ፤ የዋሻ የንጨት። መሥራት መመሥረት መንደቅ፤ የቅጥር የቤት። ሐኒጸ ሀገር። ንሕንጽ በእብን። ሕንጹ አብያተ ፡ (ኩፋ ፡ ፲። ኢሳ፱ ፡ ፲። ፴፮ ፡ ፭)። መፍጠር ማደስ፤ ማጽናት ማበርታት፤ እንዳይፈርስ ማድረግ። ከመ ይሕንጽ ለከ ዘርዐ እምኔሃ። ከመ ይሕንጹ መዝበራ ለጽዮን። ለዓለም አሐንጽ ምሕረተ። ሐነጸ ሥርዐተ ማኅበር ፡ (ኩፋ ፡ ፲፬። ዕዝ፱ ፡ ፱። መዝ ፡ ፹፰። ስንክ ፡ መስ፳፬)።
ሐናጺ ፡ (ጺት ጽያን ያት፤ ነጽት) የሚያንጥ የሚቀርጥ ጠሪቢ፤ ዐናጢ ገንቢ። ሐናጽያንኪ ፈጸሙ ሥነኪ። አብጽሐ እልፈ ሐናጽያነ ፡ (ሕዝ፳፯ ፡ ፬። ዮሴፍ)።
ሐኔት [1] ፡ ሐሜት፤–ሐመየ፤ ሐነየ።
[2] ፡ ሐሜት፤–ሐመ(ነ) የ።
ሐንሓን ፡ (ትግ) ሰርን ኰሸኰሽ፤ ያፍንጫ ዐጥንት፤ ማእከለ አዕይንት።
ሐንቅቆ ቆት ፡ (ሐንቀቀ የሐነቅቅ የሐንቅቅ) መኵራት መንጠራራት፤ ያልተሰጠውን መሻት፤ አምጡ ውለዱ ማለት፤ መደላደል መቀማጠል፤ መብሰክሰክ መንቀባረር፤ የወይዛዝርና የመኳንንት የባለጠጎች የሕፃናት፤ ለበሽተኞችም ይኾናል። ምስጢሩ ዶሮ ዕለቡ ፀሓይ በንቅብ አግቡ እንደ ማለት ነው። በሐንቀቀ ፈንታ ተሐንቀቀ ይላል ስሕተት ነው። እምከመ አጽገብካ ለነፍስከ ኢትትሐንቀቅ። እፍስ እንተ ተሐንቀቀት ታስተጋብእ ኀቤሃ ሕማመ ኀጢአት ፡ (ማር ፡ ይሥ፩ ፡ ፱። ፳፰ ፡ ፫)።
ሐንበለ ፡ (ስሯ ግ። ሐበለ) ኮረ፤ ጫነ አመቻቸ፤ ደበደበ ደለደለ።
ሐንበበ ፡ (ስሯ ግ። ሐበበ) አፈራ፤ ፍሬ ያዘ ተሸከመ። ሐንበበት ፍሬ ፡ (አርጋ ፡ ፪)።
ሐንከሰ ፡ (ዲቃ ግ። ሐነከ፤ ነከሰ) ዐነከሰ፤ ዐጭር ኾነ፤ ዐፈረ ተሰቀጠጠ፤ ተሰብሮ ተቈርጦ ተሸምቅቆ ወይም ሰሎ ደርቆ፤ የእግር። ተጠራጠረ፤ አወላወለ አመነታ፤ የልቡና። ሐንከሱ በፍኖቶሙ። እስከ ማእዜኑ ተሐነክሱ በክልኤ ልብክሙ። ስመ ሀካይ የሐነክስ በፍኖት ፡ (መዝ ፡ ፲፯። ፫ነገ ፡ ፲፰ ፡ ፳፩። አፈ ፡ ድ፴)።
ሐንካስ ፡ (ሳን ሳት) ዐንካሳ ሽምድምድ፤ እግሩ ተካክሎ የማይቆም የማይኼድ። ዕዉር ወኢሐንካስ። ዕዉራን ይሬእዩ ወሐንካሳን የሐውሩ። ሐንካሳን ወይቡሳን ፡ (ዘሌ፳፩ ፡ ፲፰። ማቴ፲፩ ፡ ፭። ዮሐ፭ ፡ ፫)። ተጠራጣሪ ወላዋይ።
ሐንክሶ [1] ፡ ማንከስ፤ መጠራጠር፤ ዐንካሳ መኾን።
[2] ፡ (ዐረ ሐንክስ) ሽቱ፤ የሽቱ ዕንጨት ቅጠል፤ መዐዛው ከሩቅ የሚሸት። ማርያም ድንግል ምዕዝት ዘእምሐንክሶ ፡ (ደራሲ)።
ሐንዋት ፡ (ዐረ ሐዋኒት። ዕብ ሐኑዮት) መደብሮች። አንዳንድ መጽሐፍ በሐንዋት ፈንታ እንዳረቡ ሐ(ከ) ዋኒት ይላል ፡ (ግብ፳፰ ፡ ፲፭)።
ሐንዘር ፤ (ዐረ ኂንዚር። ዕብ ሐዚር። ሱር ሕዚራ) ፤ ሐሣማ ሕሪያ ፤ ርኵስ የቤት እንስሳ ፤ እስራኤል የሚጸየፉት አሕዛብ የሚነፈንፉት። በለብሉዮች ግን አነር ይሉታል ፤ ሐሠመንና ሐረወን እይ (ሔኖ፹፰ ፡ ፲)።
ሐንገዝ ፡ (ሐገዘ፤ ሐገዝ። ዐረ ሐጂብ) ሽፋል፤ ቅንድብ፤ ጠጕሩ የማያድግ የማይረዝም፤ ሐገዝን እይ። ይትላጸይ ሥዕርተ ርእሱ ወጽሕሞ ወሐንገዞ ፡ (ዘሌ፲፬ ፡ ፱)። ብብት ብልት ኀፍረት፤ ያገጭ ሥር ሸለቆው። ጸጕር ሠርጸ ድማሕ ወሐንገዝ። ሕንጋዙ ፡ (ጕርዔሁ) ፡ (መጽ ፡ ምስ። ገድ ፡ ላሊ)።
ሐንጶን ፡ (ዐረ ሐንፋእ) ገበሎ ጕበና የዕሥሥትና የንሽላሊት ዐይነት ፬ እግር ያለው ዥራታም፤ በግሩና በልቡ የሚኼድ። ባለብሉዮች ግን አርጃኖ እንዝዝ ይሉታል። ላጽቂት ወሐንጶን ፡ (ዘሌ፲፩ ፡ ፴)።
ሐንጸጸ ፡ ጠረጠረ፤–ኀንጽጾ ኀንጸጸ።
ሐንፈጠ [1] ፡ (ዲቃ ግ። ነፈጠ) ጫረ ጐፈጨረ፤ ላጠ መለጠ፤ፊቱን ነጨ። እመ ቦ ዘሞተ ኢተሐንፍጡ ገጸክሙ። በአምሳለ አንስርት ወቋዓት እንዘ የሐነፍጡ ገጾሙ በአጽፋሪሆሙ ፡ (ፍ ፡ ነ ፡ ፵፭። ስንክ ፡ መስ፲፰)። ነፈጠን እይ።
[2]:-ቀረጠ፤–ኀፈጠ ኀንፈጠ።
ሐንፈጸ ፡ (ዲቃ ግ። ነፍጸ) አነፈሰ አንዘረዘረ፤ አዘራ አበጠረ፤ አጐለበ አንጓለለ። ሰአለ የሐንፍጽክሙ ከመ ዐለስ። ዘየሐነፍጸከ ሰይጣን ፡ (ሉቃ፳፪ ፡ ፴፩። አፈ ፡ ተ፴፩። ፊልክ ፡ ፻፹፱። አርጋ ፡ ፭)። ነፍጸንና ኀንጸጸን እይ።
ሐንፈጽ ፡ (ትግሪኛ) ቅይጥ፤ ቅልቅል ገብስና ስንዴ ዐብሮ የሚዘራ። ሐለስትን እይ፤ ከዚህ ጋራ አንድ ነው።
ሐኖት [1] ፡ (ዕብ ወዐረ ሐኑት። ሱር ሓኑታ) መደብር፤ የንግድ የገበያ ቤት፤ መብል መጠጥ ጨዎታ መሸታ ያለበት፤ ዓለማዊ እንግዳ የሚያርፍበት። ሥጋ ሐኖት። ኢይበልዑ ውስተ ቤተ ሐኖት፤ እመ ቦ ካህን ዘበልዐ ውስተ ሐኖት። ወኢትባእ ሐኖተ ለግሙራ ፡ (ምሳ፳፫ ፡ ፳። ፊ ፡ መ ፡ ፴፪ ፡ ፩። ሃይ ፡ አበ)።
[2] ፡ የመሸታ ቤት፤–ሐነወ።
ሐከክ ፡ ክርክር፤–ሀኪክ ሀከከ።
ሐከየ ፡ ሰነፈ፤–ሀክይ ሀከየ።
ሐኪም ፡ (ማን ማት ሐካም) ብልኅ ዐዋቂ ፈላስፋ፤ ኬንያ ጥልቅ ረቂቅ ዕውቀት ያለው። ወስመ መምህሩ ዘመሀሮ ጥበበ አርስጣጣሊስ ሐኪም። ወሰመየት ስሞ እብነ ሐኪም ፡ (ዮሴፍ። ከብ ፡ ነገ)። በቁሙ፤ ፈዋሽ የሰውን ደዌ ከነስሙ ከነመድኀኒቱ በየስልቱ የሚያውቅ፤ በሽተኞች እንደ ቄስ የሚሹት።
ሐኪም ሞት ፡ (ሐከመ የሐክም ይሕክም። ዐረብ። ዕብ ወሱር ሐካም) ብልኅ መኾን መፈልስፍ፤ በውቀት ማደግ፤ ጥበብን ዕውቀትን ገንዘብ ማድረግ። ዝም ዕክም ጸጥ ማለት፤ አለመቀባጠር። መጽሐፍ ግን በሐከመ ፈንታ ተሐክመ ይላል፤ስሕተት ነው። በአርምሞ ወበተሐክሞ ይመስል ጠቢበ ፡ (ምሳ፲፯ ፡ ፳፰)። በቁሙ፤ ማከም መፈወስ፤ ድውይን መዳሰስ መዳበስ፤ ማገም መብጣት መድኀኒት መስጠት። ኬነን እይ፤ የዚህ መንቲያ ነው። ግስነቱ ዐጕልና ገቢር እንደ ኾነ ባፈታቱ አስተውል።
ሐኪክ ኮት ፡ (ሐከ፤ ሐከከ የሐክክ ይሕክክ። ዐረ ሐከ። ዕብ ሐካኽ) ማከክ መፎከት ማቍሰል፤ መላጥ መቅረፍ፤ መፋቅ መላግ፤ መሞረድ መፈግፈግ፤ የገላ የቈርበት የንጨት የብረት። ነሥአ ገልዐ ወአኀዘ ይሕክክ ቍስሎ። ኀለቁ እንዘ አሐክክ ጸውበ። ፡ (ኢዮ፪ ፡ ፰። ፯ ፡ ፭)። ዕከካም መኾን፤ ዕከክ መልበስ፤ በዕከክ ደዌ መያዝ። ዘሐከከ አባሉ ፡ (መ ፡ ፈ)።
ሐካኪ ፡ (ኪት ክያን ያት፤ ከክት) የሚያክ የሚያቈስል፤ ጥፍራም፤ ዕከካም። ራስን ባንበሳና በነምር መስሎ ዐካኪ ዘራፍ ማለት ከዚህ የወጣ ነው ይባላል።
ሐዊ ፡ መጽሐፍ፤ የመጽሐፍ ስም፤ ሐዊ የሚባል ሰው የጣፈው የሰበሰበው፤ የአበውን ዜና የቅዱሳንን ገድል ሕግና ሥርዐት የሚናገር፤ መጠኑ ከመንፈቅ ስንክሳር የሚበልጥ። ፍችው እሳታዊ ሰማያዊ፤ መንፈሳዊ እንደ ማለት ፡ (ግብ፪ ፡ ፫)።
ሐዋሊ ፤ (ሊት ልያን ያት ፤ ወልት) ፤ የሚዞር የሚከብ ፤ቀላቃይ።
ሐዊል ሎት ፡ (ሖለ፤ ሐወለ የሐውል፤ ይሑል። ዐረ ሐውለ፤ ዞረ) መዞር መክበብ። መቀላቀል መደባለቅ፤ አንድ ማድረግ። ሐበለን እይ፤ የዚህ ጎር ነው።
ሐዊሳ ፡ ፍጥነት ችኰላ፤ ንቅነቃ ቅስቀሳ። የደስታና የአንክሮ የስላምታ ቃል፤ ሐዲስ ድንቅ ነገር ደስ የሚያሰኝ ምስጢር ከማየት ከመስማት የተነሣ ራስን ዐንገትን በመነቅነቅ፤ ወሰው ወሰው፤ መልካም መልካም፤ ይበል ይበል፤ ዕሠይ ዕሠይ ማለት። ሐዊሳ ሐዊሳ ለዝንቱ ሐዋሪያ። ሐዊሳ ለምጽአትከ ወለምጽአትከ ወለመዊኦትከ ፡ (አፈ ፡ ተ፲፪። ዮሴፍ)። የሰላምታ ቃል ሲኾን ፍችው እንደ በሓ ነው። ኢይፈርህ ብሂሎተከ ሐዊሳ ሐዊሳ፤ እስመ ባሕረ ልብየ መልአ ሰላምከ ዓሣ ፡ (ደራሲ)።
ሐዊስ ሶት ፡ (ሖሰ የሐውስ ይሑስ፤ ኮሰ። ዕብ ሓሽ። ዐረ ሐሰ፤ ሀዘ) መፍጠን መቀልጠፍ፤ መቸኰል። ማዘን መታወክ፤ መዋለል። መነቅነቅ መናጥ ማናወጥ ማንቀሳቀስ፤ ራስን ሕዋስን። ኮሰን እይ፤ የዚህ መንቲያ ነው። መጽሐፍ ግን በሖስ ፈንታ አሖሰ ይላል፤ አያሰኝም። አሖሰ ርእሶ ዲቤኪ። አሖሱ ከናፍሪሆሙ ላዕሌየ። በአሑሶ ክነፊሁ ፡ (ኢሳ፴፯ ፡ ፳፪። ሰቈ፫ ፡ ፷፩። ጥበ፭ ፡ ፲፩)።
ሐዊር ሮት ፡ (ሖረ የሐውር ይሑር) መኼድ መራመድ ከቦታ ወደ ቦታ መፍለስ፤ እግርን በፈረቃ ማንሣት መጣል፤ መንቀል መትከል ማሽቀዳደም። በደረት በልብ መሳብ መጐተት ለመም ማለት። ሄደንና ኬደን እይ፤ የዚህ ጎሮች ናቸው። ሑሩ ውስተ ኵሉ ዓለም። ከመ ይሑር በእገሪሁ። ሑሪ በእንግድዓኪ ፡ (ማር፲፮ ፡ ፲፭። ግብ፫ ፡ ፲፪። ዘፍ፫ ፡ ፲፫)።
፡ 1 መኖር፤ መቀመጥ የቦታ የግብር። ለምንት የሐውር ወልደ ብእሲት ምስለ ብሉየ መዋዕል። ዘየሐውር በጽድቅ። ዘከመ ሖርኩ ቅድሜከ። ኢሖሩ በትእዛዝከ። ዘኢሖረ በምክረ ረሲዓን ፡ (ሔኖ። ኢሳ፴፫ ፡ ፲፭። ፴፰ ፡ ፫። ኤር፴፱ ፡ ፳፫። መዝ ፡ ፩)።
፡ መሥራት ማድረግ፤ መቅረብ መራከብ። ሖሮን እግዚእ ለኀምስ ግብራት። ሐዊረ ብእሲተ ብእሲ። ኢትሑር ኀበ እንስሳ። ኵሉ ዘየሐውር እንስሳ ኵነኔሁ መዊት። እለ የሐውሩ ወእለ የሐውርዎሙ ፡ (ትር ፡ ወን። ማር፯ ፡ ፳፩። ዘሌ፲፰ ፡ ፳፫። ዘፀ፳፪ ፡ ፲፰። ፩ቆሮ ፡ ፮ ፡ ፱)።
ሐዊጽ ፡ ሐውጾ መንጻት መጥራት፤ ንጹሕ ጽሩይ ብሩህ መኾን። ወከመ ርእየተ ጽንዐ ሰማይ ሶበ ሐወጸት። መኑ ይእቲ ዛቲ እንተ ትሔውጽ ከመ ጎሕ። ሐውጽ እምሰማይ ብርሃነከ ከመ ንርአይ ፡ (ዘፀ፳፬ ፡ ፲። ማሕ፮ ፡ ፱። ድጓ)።
ሐዊጽ ጾት ፡ (ሖጸ የሐውጽ ይሑጽ፤ አው ሐውጾ፤ ሐወጸ ይሔውጽ የሐውጽ። ሐየጸ። ዋሐየ) ማወጥ መጐብኘት መሰለል፤ መፍቀድ መጠየቅ አሻግሮ ማየት፤ ዐይንን ልብን ጥሎ ሥራዬ ብሎ ማየት መመልከት። አመ ሐውጾ ሐወጸክሙ እግዚእ። ኢትትሀከይ ሐውጾ ድዉይ። የሐውጽዎሙ ለነዳያን። ወይሔውጽ እንተ መሳክው። እንተ ትሔውጽ እምርሑቅ። ወዘሰ ሐወጸ ውስተ ሕግ ፍጹም ፡ (ዘፍ ፡ ፶ ፡ ፳፭። ሢራ፯ ፡ ፴፭። ኪዳ። ማሕ፪ ፡ ፱። ፯ ፡ ፮። ያዕ፩ ፡ ፳፭)። ግስነቱ ገቢርና ዐጕል ነውና፤ ያለፈው ገቢር የሚመጣው ዐጕል እንደ ኾነ ፍችውን አስተውል።
ሐዋላ ፡ (ዐረብ) በፖስታና በባንክ የሚላክ ገንዘብ።
ሐዋሪ ፡ (ሪት ርያን ያት) የሚኼድ ኸ(ሀ) ያጅ፤ ተራማጅ ሯጭ ገሥጋሽ ፡ (ዘማዊ)። ጻማዊ በገድሉ ወሐዋሪ በፍኖተ አበው ቅዱሳን። ፈላሲ ወሐዋሪ እምኔነ፤ ሐዋሪ ዘኢይሴፎ ተመይጦቶ ፡ (ገድ ተዝ። ግንዘ)። ደላዊ ሐያቢ ቀዳሒ በማለት ፈንታ ሐዋሪ ይላል፤ የመላሽ ስሕተት ነው። ሐዋሬ ማይክሙ። ወረሰዮሙ ሐዋርያነ ማይ ለኵሉ ተዓይን። ይወፅኣ ሐዋርያተ ማይ ፡ (ዘዳ፳፱ ፡ ፩። ኢያ፱ ፡ ፳፭። ዘፍ፳፬ ፡ ፲፩። ፩ነገ ፡ ፱ ፡ ፲፩)።
ሐዋርያ ፡ (ያት። ዐረ ሐዋሪይ) መንገደኛ መልክተኛ ቀላጤ። ከመ እኩይ ሐዋርያ። ሐዋርያ ጠቢብ ያድኅን ርእሶ። ፈነወ ሐዋርያተ ፡ (ምሳ፮ ፡ ፲፩። ፲፫ ፡ ፲፯። ሕዝ፲፯ ፡ ፲፭)።
፡ በቁሙ፤ መንፈሳዊ ሹም መምህር፤ ዙሮ የሚሰብክ የሚያስተምር፤ ባለምሥራች ዐዋጅ ነጋሪ። ሐዋርያ ዘተጸውዐ ወተፈልጠ ለትምህርተ ወንጌል። ርእይዎ ለዝንቱ ሐዋርያክሙ። ዘሎቱ ተሠየምኩ አነ ሐዋርያ ወዐዋዴ። ጉባኤ እንተ ሐዋርያት ሐዋርያተ በግዑ ፡ (ሮሜ፩ ፡ ፩። ዕብ፫ ፡ ፩። ፪ጢሞ ፡ ፩ ፡ ፲፩። ጸሎ ሃይ። ራእ፳፩ ፡ ፲፬)።
ሐዋርያዊ ፡ የሐዋርያ። ቀኖና ሐዋርያዊ። መንበር ሐዋርያዊት ፡ (ፈ ፡ መ ፡ ፲፯። አቡሻ)።
ሐዋዝ ፡ ሐዋዝ፤ ያማረ የጣፈጠ የተሰማማ፤ ደስ የሚያሰኝ። መልካም። ቅጽልነቱ ዐጕል ስለ ኾነ ፥ ወንድና ሴት ያስተባብራል። ሐዋዝ ማሕሌት ወመሰንቆ በቤተ ስታይ። ሐዋዝ ውእቱ ሕገ እግዚ። ምድር ሐዋዝ ወሥብሕት። ሐዋዘ ትነውም። ንግበር ሐዋዘ ውስተ ፍጥረትነ ፡ (ሢራ፳፭ ፡ ፮። ሮሜ፯ ፡ ፳፪። ሔኖ፹፱ ፡ ፵። ምሳ፫ ፡ ፳፬። ጥበ፪ ፡ ፮)። ዐዋዜ ጥሩ ድልኽ ፡ (ዐማርኛ)።
ሐዋጺ ፡ (ጺት ጽያን ያት) የሚጐበኝ፤ ተመልካች፤ ጠያቂ ፈቃጅ፤ መርማሪ ሰላይ። እግዚእ ሐዋጼ ነፍሰ ትሑታን። ድዉያን እለ አልቦሙ ሐዋጺ። ሐዋጺ ህልው ይሔውጽ ልቦ ፡ (ኪዳ። ፍ ፡ ነ ፡ ፯ ፡ ፫። ጥበ፩ ፡ ፮)።
ሐው [1] ፡ እሳት፤–ሐውይ ሐወየ።
[2] ፡ እሳት የሚፋጅ የሚያቃጥል፤ ሕብሩ ቀይ የምሼት ሰማይ የሚመስል። በብዝኀ ትንታጉ ለሐው ይበዝኅ ፍሕሙ።ሐወ ዘአቈርከ። ጤገን ዘአፍልሕዎ በሐው። አንዲዶሙ ሐወ ፡ (ሢራ፲፩ ፡ ፴፪። ድጓ። ስንክ ፡ ኅዳ፯። ሠኔ፳፩)።
ሐውለየ ፡ ለየ ነቀፈ፤–ሀውለየ።
ሐውል ፡ (ላት። ዕብ ሖል፤ አሸዋ) ያሸዋ ጭቃ፤ ዐፈር ኵረት የተቀላቀለው። ሻፎ አለት ጥርሳም ስለታም ሸካራ ደንጊያ።ወምስካቡ ሐውላት ዐበይት ፡ (ኢዮ፵፩ ፡ ፳፩)።
ሐውልት ፡ (ታት) በቁሙ፤ ትክል ደንጊያ እንደ ዐምድ እንደ ምሰሶ የቆመ፤ ክብነት ምእዙንነት ያለው፤ ለመታሰቢያ የሚተከል የሚነደቅ፤ ወይም ከኖራ ካሸዋ ከሽሜነት ከደንጊያ ዶቄት ቀላቅለው ደባልቀው እያፈሰሱ የሚሠሩት ፍስ ደንጊያ። አቀሙ ሐውልተ እብን ዐቢይ። ኢታቅሙ ለክሙ ሐውልተ እብን። ሐውልተ ጼው። ሐውልተ ስመዕ ፡ (፪ነገ ፡ ፲፰ ፡ ፲፯። ዘሌ፳፮ ፡ ፩። ዘፍ፲፱ ፡ ፳፯። ቅዳ)።
፡ ያጕል ግስ ስም፤ ኖመ ቆመ፤ ጥዕየ ሐመ፤ ጸንዐ ደክመ፤ ይህን የመስለ ግስ ሐውልት ይባላል፤ ቅልቅል ማለት ነው።
ሐውት ሐይት ፡ (ዕብ ሔት) የፊደል ስም፤ ፰ኛ ፊደል ሐ፤ በግእዝ አልፍ ቤት በአበገደ። ሕይወት ማለት ነው፤ ሐይወን እይ። ምስጢሩ በ፰ኛው ሺሕ የሚኾን ሐዲስ ሕይወትን ትንሣኤ ሙታንን ካስነሺው ጋራ ባንድነት ያሳያል ፡ (ዮሐ፲፩ ፡ ፳፭። ማቴዘ፳፪ ፡ ፴፪)። ጸሐፍት ግን ሐመር ሐ ይሉታል።
ሐውዝ ፡ (ዛት) ተድላ ደስታ፤ ጣዕም ፍትወት፤ ውበት ስምምነት። ጐየ እምሐውዘ ዓለም። ሐውዘ መሰንቆ ወማሕሌት። ሐውዘ መንበርት። ሐውዘ መባልዕት። ሐውዘ አየራት ወፍሬያተ ምድር። ፡ (ድጓ። ሢራ፵፬ ፡ ፭። ሉቃ፰ ፡ ፲፬። ዲድ ፡ ፲፬። ግንዘ)።
ሐውይ ዮት ፡ (ሐወየ የሐዊ ይሕወይ። ዐረ ሐዊየ) መጋም መቃጠል፤ እሳት መኾን መምሰል፤ መጥቈር መክሰል፤ የብረት የንጨት። መምሸት መጨለም፤ ድግዝ ማለት። ፀሓይ ስትገባ የሰማይን መቅላትና መጥቈር ያሳያል።
ሐዘን ፡ ሐዘን፤ ፡ (ናት) በቁሙ፤ ዐዘን፤ ደረቅ ሸካራ ጥኑ ጠንካራ ነገር፤ የሚያነድ የሚያጤስ፤ የሚያስለቅስ ሐሳብ። ሐዘን ኢይባእከ፤ እስመ ብዙኃን እለ ሞቱ እንበይነ ሐዘን። እስመ ሐዘኑ ለልብ ይሰብሮ ለኀይል። ወንሬስየክሙ ዘእንበለ ሐዘን። እንተ ኢፈጸመት ዕድሜ ሐዘነ ምታ ዘሞተ። ሐዘናት ብዙኃት ፡ (ሢራ፴፰ ፡ ፲፰። ማቴ፳፰ ፡ ፲፬። ፍ ፡ ነ ፡ ፳፬ ፡ ፪። ፊልክ ፡ ፸፱)።
ሐዘንዚን ፡ የልቅሶ ቃል፤ ወርድ ንባብ፤ የሐዘን ዜማ። ካህናት ይትቀነዩ ዘንተ መዝሙረ በዜማ ሐዘንዚን ፡ (ግንዘ)።
ሐዙራን ፤ (ሱር ወዐረ ሐዚራን) ፤ የወር ስም ፤ የሶርያ ወር ሠኔ (ገድ ፡ ላሊ። መጽ ፡ ምስ)።
ሐዙር ፡ (ዐረ እልሐዝር) ግምት መላ፤ ጥንቈላ። ክታብ ሥራሥር፤ መንድግ፤ መስተፋቅር። እለ ይገብሩ እልሐዙረ በኵርናዕ ወይፈቅዱ ቦቱ ይርብሑ ረባሐ ፡ (ፍ ፡ ነ ፡ ፶ ፡ ፭)።
ሐዚል ሎት ፡ (ሐዘ(ዝ) ለ የሐዝል ይሕዝል) ማዘል መሸከም፤ በዠርባ በሕፅን። ዘባንኪ እምዘባነ ኪሩብ ዘዐብየ፤ ሐዚሎ እሳተ። ሐፃኒት እንተ ተሐዝል ደቂቃ። ወሐዘሎሙ በክነፊሁ ፡ (ደራሲ። ፩ተሰ ፡ ፪ ፡ ፯። ዘዳ፴፪ ፡ ፲፩)።
ሐዚን ኖት ፡ (ሐዘ(ዝ) ነ የሐዝን ይሕዝን። ዐረ ሐዚነ) ማዘን መቈርቈር፤ መቈጣት መናደድ፤ መከፋት። በመጥፎ ቦታ ላይ ተኝቶ ተቀምጦ ምቾት ከማጣት የተነሣ፤ ሐዝሐዝን እይ። ሐዘነ መንፈሳ ለርብቃ። ለምንት ተሐዝን። ወሰሚዖሙ ዐሠርቱ ሐዘኑ በእንተ ክልኤቱ አኀው ፡ (ኩፋ ፡ ፳፯። ዘፍ፬ ፡ ፮። ማቴ፳ ፡ ፳፬)።
ሐዚእ ኦት ፡ (ሐዝአ የሐዝእ ይሕዛእ። ዐረ ሐዘአ) መንዳት፤ ማባረር ማሳደድ፤ ሰብስቦ አስቀድሞ፤ መከተል፤ የረኛ ያርበኛ። ነድአን እይ።
ሐዚዝ ዞት ፡ (ሐዘ፤ ሐዘዝ የሐዝዝ ይሕዝዝ) ማነቅ መሰርነቅ ማስጨነቅ፤ ማስፋቅ ሕቅ ስርቅ ማሰኘት፤ ማንዘዝ ትን ማለት ባፍንጫ መውጣት፤ መምረር መከርከር፤መሖምጠጥ መጐፍነን፤ የመጠጥ የፈሳሽ ነገር። መጽሐፍ ግን በሐዘዘ ፈንታ አሕዘዘ ይላል፤ አያሰኝም። ያስትይዎ ብሒአ ዘምስለ ሐሞት ለአሕዝዞቱ። በእንተ ጕርዔከ ስቴ ሐሞት ዘአሕዘዞ። ዐቀቦ ለዮናስ በከርሠ ዐንበሪ ከመ ኢያሕዝዞ ሞገደ ባሕር ፡ (ኦርጋ። አዋል። መጽ ፡ ምስ)። ዳግመኛም ዐገተ ከበበ በማለት ፈንታ፤ አሕዘዘኒ ማይ እስከ ነፍስየ ይላል ፡ (ዮና፪ ፡ ፮)።
፡ መጐንጨት መማግ፤ ገጭ ጕርጕጭ ማድረግ፤ መዋጥ ማሥረግ፤ ኹሉም የጕረሮና ያፍ ያፍነጫ ሥራ ነው። መጥቈር መዝጐን መብለዝ፤ እንዝዝ መምሰል፤ ማሳከክ መሻከር መቀንቀን፤ የሥጋ የገላ ከደዌ ከበትር የተነሣ። የሐዝዘኒ በሕቁ ማእስየ ፡ (ኢዮ፴ ፡ ፴)። ዛሕዝሐን እይ።
ሐዛሊ ፡ (ሊት ልያን ያት፤ ዘልት) የሚያዝል ዐዛይ፤ ተሸካሚ። ዕደው ሐዘልት ፡ (፪ዜና ፡ ፪ ፡ ፪)።
ሐዛቢ ፡ (ቢት ብያን ያት፤ ዘብት) የሚያዝብ፤ የሚሰበስብ፤ ዐሳቢ ጠርጣሪ።
ሐዛኒ ፡ (ኒት ያን ያት) የሚያዝን ዐዘኝ፤ ተቈርቋሪ። ብእሲ ሐዛኒ ያየብስ አዕፅምቲሁ ፡ (ምሳ፲፯ ፡ ፳፪)።
ሐዛኢ ፡ (ኢት እያን ያት) የሚነዳ ነጅ፤ አባራሪ አሳዳጅ።
ሐዝሐዝ ፡ ኵረት። ጠጠር፤ ጭንጫ አሸዋ። ማጥ ረግረግ ውሃማ ቦታ ፊላ ቄጠማ ሸንበቆ መቃ የሚበቅልበት። ማእከለ ጾላዕት ይበይት ወውስተ ሐዝሐዝ የሐዩ። ያሰጥሞ ሐዝሐዘ ፈለግ ፡ (ኢዮ፰ ፡ ፲፯። ፳፩ ፡ ፴፫)። ሐዘነን እይ፤ የዚህ ዘር ነው።
ሐዝቦ ቦት ፡ (ሐዘበ ይሔዝብ የሐዝብ። ሐሰበ) ማዘብ ማሰር፤ የጫማ የመጫሚያ። መሰብሰብ፤ መወገን። ማሰብ፤ መጠርጠር፤ መፍራት ምን አልባት ማለት። አነ አሐዝብ ከመ መልአክ ውእቱ። ወኢሐዘብኩ እስማዕ ካልአ ነገረ። ኢሐዘብኩከ ትንብብ ከመ ዝ። ሐዘብከኑ እኩን ከማከ። አሐዝብ ሕያዋኒነ እምውኅጡነ። አሐዝብ ንመጽእ አነ ወእምከ ወአኀዊከ ወንሰግድ እከ ዲበ ምድር ፡ (ፊልክ ፡ ፶፫። ፩ቆሮ ፡ ፪ ፡ ፪። ኢዮ፳ ፡ ፪። መዝ ፡ ፵፱። ፻፳፫። ዘፍ፴፯ ፡ ፲)። ዳግመኛም በሐዘበ ፈንታ ተሐዘበ ይላል፤ ስሕተት ነው። ተሐዘባ ከመ ዘማዊት። ብእሲ ዘይትሔዘብዎ በዝሙት። በከመ ይትሔዘቡ እለ አልቦሙ አእምሮ። ምንተኑመ ትትሔዘቡኒ። ትትሔዘብኑ ታስተአብዶ ለእግዚ። አትሔዘብ ናስጣርዮስ ዝንቱ ፡ (ኩፋ ፡ ፵፩። ቈስጠ ፡ ፲፫። ፊልክ ፡ ፪፻፲፬። ድጓ። ሮሜ፪ ፡ ፬። ቄር ፡ ጰላ)።
ሐዝዐ ፡ ነዳ አባረረ፤–ሐዚእ ሐዝአ።
ሐየሰ ፡ ተሻለ፤–ኀዪስ ኄሰ ኀየሰ።
ሐየየ ፡ ቸል አለ፤–ሀይይ ሀየ፤ ሀየየ።
ሐዪስ ሶት ፡ (ሔሰ፤ ሐየሰ የሐይስ ይሒስ) መንቀፍ ማጸየፍ፤ ማነወር መክሰስ፤ መስደብ መቈጣት። ኢትሒስ ዘእንበለ ትሕትት። ሶቤሃ የሐይስ ርእሶ። ኢትሒሰኒ፤ እስመ ኀሠሥኩ ኣእምር። ይሒስከ እግዚ ፡ (ሢራ፲፩ ፡ ፯። ኢዮ፴፭ ፡ ፳፯። ጦቢ፭ ፡ ፲፬። ይሁ ፡ ፱)።
ሐዪቅ ቆት ፡ (ሔቀ፤ ሐየቀ የሐይቅ ይሒቅ) ማቀፍ መክበብ፤ ዳር ደንበር ቅርብ አጠገብ መኾን፤ የደሴትና የባሕር የየብስ፤ ለሕንጻም ይኾናል።
ሐዪብ ቦት ፡ (ሔበ የሐይብ ይሒብ። ደለወ። ዕብ ሻአብ) ማየብ፤ መቅዳት መጥለቅ መደንበቅ፤ መሳብ መጐተት፤ ከጕድጓድ ካዘቅት ጨልፎ ማውጣት ፡ (ዘፀ፪ ፡ ፲፮ ፡ ፲፱)። ደለወን ተመልከት።
ሐዪክ ኮት ፡ (ሔከ የሐይክ ይሒክ። ሐነከ) ማላመጥ ማኘክ፤ በጥርስ መፍጨት መለንቀጥ፤ ለመዋጥና ለመሰልቀጥ፤ የምግብ። አይ አስናን ዘየሐይክ ዘንተ ኅብስተ። ወይሒኮ በለኈሳስ። እንዘ የሐይክ ፡ (ቅዳ። ሥር ፡ ጳኵ)።
ሐዪው ዎት ፡ (ሔወ ሐይወ የሐዩ ይሕዩ፤ የው። ዕብ ሐያህ፤ ሐይ። ሱር ሕያእ። ዐረ ሐየ) መዳን መፈወስ ወደ ጥንተ ሕይወት መመለስ፤ መታደስ ዳግመኛ መሠራት፤ ሙቶ መነሣት በሕይወት በጤና መኖር፤ አለመታመም አለመሞት። እመ ደወየ ኢይሴፎ ሐዪወ። ትፈቅድኑ ትሕየው። አመ የሐይዉ ምዉታን። ወሐይወ አዳም እምድኅረ ወለዶ ለሴት ሰብዐተ ምዕተ ዓመተ። ሕየው ለዓለም ፡ (ኢዮ፳፬ ፡ ፳፫። ዮሐ፭ ፡ ፮። ማር፲፪ ፡ ፳፫። ዘፍ፭ ፡ ፬። ዳን፫ ፡ ፱)።
፡ ደስ ፈቅ ማለት፤ ደስታ መመላት፤ ምስጢሩ መታደስ ካለው ይገባል። ሐይወ ልቡ ወነፍሱ ለያዕቆብ። ተሐደሰት ወሐይወት መንፈሱ ፡ (ዘፍ፵፭ ፡ ፳፮። ኩፋ ፡ ፴፫)። ሐዮኩ ከ ኪ ሐዮነ ክሙ ክን እያለ እንደ ሀለወ በቅርብ በቅርቦች ይጐርዳል። ሐውትንና ሔትን እይ፤ የዚህ ዘር ናቸው።
ሐዪጽ ጾት ፡ (ሔጸ፤ ሐየጸ የሐይጽ ይሒጽ። ሐወጸ) ማስተዋል መመልከት ውስጡን ምስጢሩን ማሰብ መመርመር መሻት፤ መላልሶ ቀምሎ ትክ ብሎ ማየት፤ የክፉ የበጎ። ሐወጸን እይ፤ የዚህ መንቲያ ነው። መጽሐፍ ግን በሐየጸ ፈንታ አስተሐየጸ ይላል፤ አስተ አለቦታው ገብቷል፤ ሐቀረን እይ፤ ይህም እንደዚያ ነው። እምርሑቅ ያስተሐይጽ ዐይኑ። መጻእክሙ ታስተሐይጹ አሠረ ምድር። አስተሐይጽ በልብከ ወአእምር መኑ አንተ። ወበአይኒ ግብር ያስተሐይጽዎ ዘልፈ። ዘያስትሐይጻ ለድንግል ፡ (ኢዮ፴፱ ፡ ፳፱። ኩፋ ፡ ፵፪። አፈ ፡ ተ፲፩። ዳን፮ ፡ ፲፩። ቀሌ)።
ሐያሲ ፡ (ሲት ስያን ያት፤ የስት) የሚነቅፍ ነቃፊ፤ ከሳሽ ወቃሽ።
ሐያጺ መሐይጽ መስተሐይጽ ፡ የሚያስተውል ተመልካች አስተዋይ፤ ልባም ዐይናማ። ዲያቆን ይኩን መስተሐይጸ ከመ ይርአይ ፡ (ኪዳ)።
ሐይል ፡ በቁሙ፤–ኀይሎ ኀየለ።
ሐይመት ፡ ድንኳን፤–ኀይመት።
ሐይመነ ፡ አመነ፤–ሀይመነ፤ ሃይማኖት።
ሐይቅ ፡ (ቃት) ዙሪራ ዳርቻ ወደብ ጽንፍ፤ የባሕር ጠረፍ። ታናሽ መጠነኛ ባሕር ዙሪያው ዳርቻው የሚታይ፤ በተራራ በየብስ የተከበበ፤ እንደ ዟይ እንደ ሐይቅ እንደ ጣና ያለ። ሐይቀ ባሕር። ኀበ ሐይቀ ባሕር። መንገለ ሐይቀ ጌንሴሬጥ። ድንጋግ ዘሐይቅ ፡ (መሳ፭ ፡ ፲፯። ማቴ፲፭ ፡ ፳፱። ሉቃ፭ ፡ ፩። አርጋ ፡ ፪)።
ሐይብ ፡ በቁሙ፤ ዐይብ የላም ልጅ የርጎ ተወራጅ። ፡ (ተረት) ዐይቡ ዳኛ፤ ቅቤው መልከኛ ፡ (መ ፡ ፈ)።
ሐይድ ፡ ቅሚያ፤–ሀይድ ሄደ።
ሐደመ ፡ አንቀላፋ፤–ሀዲም ሀደመ።
ሐደሠ ፡ በቁሙ፤–ሐድሶ ሐደሰ።
ሐደረ ፡ ዐደረ –ኀዲር ኀደረ።
ሐደፈ ፡ ቀዘፈ፤–ኀድፎ ኀደፈ።
ሐዲስ ፡ (ሳን ሳት፤ ዳስ ሳት) በቁሙ፤ ዐዲስ እንግዳ ቀድሞ ያልነበረ ኋላ የተገኘ የተፈጠረ፤ ወይም የታደሰ የተለወጠ፤ ብልየት የጠፋለት። ዐርክ ሐዲስ ወይን ሐዲስ። በእንተ ሐዲሳን ሕዝብ እለ ይፈቅዱ ይጠመቁ። ብሉያት ወሐዲሳት። ሐዳስ ሥርዐት። ሐዳሳተ ሰማያተ ወሐዳሰ ምድረ ንሴፎ ፡ (ሲኖዶ። አርጋ። ዕብ፱ ፡ ፲፭። ፪ጴጥ ፡ ፫ ፡ ፲፫)። ሐዲላት ሐዳሳት በማለት ፈንታ ሐደስት ይላል፤ የተሳሳተ ነው ፡ (መሳ፲፭ ፡ ፲፫ ፡ ፲፬። ዘፀ፳፫ ፡ ፲፭)።
ሐዲድ ፡ (ዐረብ) ብረት ዛንጅር። እምክሣድየ ሐዲደ ፡ (ስንክ ፡ ሚያ፳፩)።
ሐዳሚ ፡ (ሚት ምያን ያት፤ ደምት) የሚተርት ተራች፤ ምሳሌ ዐዋቂ፤ ተጫዋች።
ሐዳሲ ፡ (ሲት ስያን ያት፤ ደስት) የሚያድስ የሚጠግን፤ ወጌሻ ገንቢ ዐናጢ። ኮነ ሐዳሲሃ ለጽድቅ ፡ (ገድ ፡ ኪሮ)።
ሐዳፍ ፡ (ብ አሕዳፍ። ዕብ ዖሬፍ) ማዥራት ጫንቃ፤ ያንገት ኋላ አጽንዑ ሐዳፎሙ። እግዚ ሰበረ አሕዳፊሆሙ ፡ (ኤር፲፱ ፡ ፲፭። መዝ ፡ ፻፳፰።
ሐድሞ ሞት ፡ (ሐደመ ይሔድም የሐድም። ዕብ ሐድ) መተረት መመሰል፤ በተረትና በምሳሌ መንገር ማስተማር። ሐድም ሐድሞተ ወመስል ምሳሌ ፡ (ሕዝ፲፯ ፡ ፪)።
(ጥ) ሐድሶ ሶት ፡ (ሐደሰ ይሔድስ የሐድስ። ዕብ ሐዴሽ። ሱር ሐዴት። ዐረ ሐደሰ) ማደስ፤ መለወጥ ሐዲስ ማድረግ፤ ማጥናት ማበርታት፤ መሥራት መጠገን፤ ያሮጌ የሰባራ። የሐድስዋ ለንስሓሆሙ። ኵሎ ትሔድስ። ይሔድሱ አህጉረ እለ መዝበራ ፡ (ዕብ፮ ፡ ፮። ጥበ፯ ፡ ፳፯። ኢሳ፷፩ ፡ ፬)።
፡ ዐዲስ ነገር ማውጣት መፍጠር። ይሔድስ እግዚእ ሐዲሳተ ፡ (ሔኖ ፡ ፻፮ ፡ ፲፫)።
፡ መባረክ መቀደስ መመረቅ፤ ያዲስ ቤት። ደቅሐንና ሐነከን ተመልከት። ወሐደሰ ቤተ እግዚ። ሐድሶ ሕንጸታ ፡ (፪ዜና ፡ ፯ ፡ ፭ ፡ ፱። ዮሐ፲ ፡ ፳፪)። በሐረስ ፈንታ ሐደሰ ይላል፤ የተሳሳተ ነው። ሐድሱ ሐዳሳተ ፡ (ኤር፬ ፡ ፫)።
ሐድዐ ፡ ጸጥ አለ፤–ሀዲእ ሀድአ።
ሐገመ ፡ (ሐከመ) ዐገመ ዋገምት ተከለ። ዘሩ ሐከመ ነው፤ ከ በገ ተለውጧል።
ሐገን ፡ ንፍጥ ያፍንጫ እድፍ ፡ (ትግሬ)።
ሐገዝ ፡ ብብት፤ ኀፍረት ጕያ። ሐንገዝን እይ፤ የዚህ ስሯጽ ነው።
ሐገፈ ፡ (ዐረ ሐጀበ) መከተ፤ አነገበ፤ ለበሰ ያዘ፤ የጋሻ።
ሐገፋ ፡ (ፋት) ጋሻ የሰልፍ ልብስ፤ ላዩ ብረት ውስጡ ቈርበት፤ ከሰይፍና ከጦር የሚያድን። ወልታን እይ። ሠለስቱ ምእት ሐገፋ ዘወርቅ። ወነሥአ ሐገፋተ ወርቅ። ሐገፋ ወረምሕ። ኪንኒ እግዝእትየ ቅድመ ፀርየ ሐገፋ ፡ (፪ዜና ፡ ፱ ፡ ፲፮። ፲፪ ፡ ፱። ፲፬ ፡ ፰። ደራሲ)።
ሐጕለ ፡ ዐጣ፤–ሀጕል ሀጕለ።
ሐጊል ሎት ፡ (ሐገለ፤ ሐግለ የሐግል ይሕግል። ዐረ ሐጀለ) ማሰር መሸንከፍ፤ መቀየድ መሰንከል። ከዚህ የተነሣ መር መር ፥ ኵብ ኵብ ፥ ዱብ ዱብ እያሉ መኼድ፤ የቍራ ያንካሳ የእስር አካኼድ አረጋገጥ። ከጥሬው በቀር አንቀጹ አይገኝም።
ሐጊዝ ዞት ፡ (ሐገዘ የሐግዝ ይሕግዝ። ዐረ ሐጀዘ) መግታት ማቆም፤ ማስጠጋት ማስደገፍ፤ እንዳይኼድ እንዳይወድቅ መከልከል መጠበቅ፤ የመርከብ የፈረስ። መሰወር መደበቅ፤ ከብብት ከጕያ ማግባት መሸጐጥ። በቁሙ፤ ማገዝ መርዳት።
ሐጋያዊ ፡ የበጋ፤ ለበጋ የሚኾን፤ የበጋ ወራት ሐሩር ድርቅ የሚጠናበት ፡ (አቡሻ ፡ ፴፯)።
ሐጋይ ፡ በጋ ድርቅ፤ የድርቅ ወራት ካራቱ ክፍላተ ዘመን አንዱ እጅ ፫ ወር ወይም ፺፩ ቀን ተሩብ፤ ከታኅሣሥ ፳፮ እስከ መጋቢት ፳፮። ሀለዉ አርባዕቱ ዘመናት፤ ቀዳሚሆሙ ዘመነ መፀው። ወፈለጠ እምውስቴቶሙ ክረምተ ወማእረረ ወሐጋየ በበ ኍልቆሙ ወበበ ጊዜሆሙ ፡ (አዋል። ሢራ፴፮ ፡ ፱)። የሐጋይ ፍች በጋ ስለ ኾነ መፀውም ጸደይም በርሱ ስም ሐጋይ ይባላሉ። ዘጠኝ ወር በጋ ሦስት ወር ክረምት እንዲሉ። ክረምተ ወሐጋየ ዘአንተ ፈጠርከ። ወከማሁ ይከውን በክረምት ወበሐጋይ ፡ (መዝ ፡ ፸፫። ዘካ፲፬ ፡ ፰። ዘፍ፰ ፡ ፳፪)።
ሐጋጊ ፡ (ጊት ግያን ያት) በቁሙ፤ የሚያግግ፤ ሕግ ሠሪ ወሳኝ አቋሚ፤ በቃል በመጽሐፍ። እስመ ሐጋጌ ብሉይ ወሐዲስ አሐዱ ወቱ። እንዘ ሐጋጌ ሕግ በመለኮቱ ናሁ ኮነ መትሕተ ሕግ። ሐጋጌ አጽዋም እምስቴ። ፡ (አፈ ፡ ድ፴፪። ሃይ ፡ አበ። ጥቅ፲፪)።
ሐጌ ፡ (ዕብ ሐጋይ) የሰው ስም፤ ነቢይ ካሥራ ኹለቱ ደቂቀ ነቢያት አንዱ። በዓላዊ ዘተወልደ በዕለተ በዓል ማለት ነው። በእደ ሐጌ ነቢይ ፡ (ሐጌ፩ ፡ ፩)።
ሐግ ፡ (ዕብራ) በዓል፤ የበዓል ቀን። ምንተ ይገብሩ በዕለተ ሐጎሙ ፡ (ሆሴ፱ ፡ ፭)።
ሐግል ፡ (ላት። ዐረ ሐጅል፤ ሒጂል) ማሰሪያ፤ የግር ብረት። የግር ጌጥ፤ ግርጃ ድኰት ጥምዝ። መንቈር፤ ቀንበር ከነማነቆው። ግበር ለከ ጋገ ወሐግለ ወደዮ ውስተ ክሳድከ ፡ (ኤር፳፯ ፡ ፪)።
ሐግይ ዮት ፡ (ሐገየ የሐጊ ይሕጊ) ማጋየት ማቃጠል፤ በጋ ድርቅ መኾን፤ የእሳት የወራት። መባጀት፤ በጋው እስኪያልፍ መቈየት። መጋረድ መሸፈን ፡ (ትግሬ)። ጋይ ጋያ ማለት ከዚህ ወጥቷል።
ሐግጎ ጎት ፡ (ሐገገ ይሔግግ የሐግግ። ዕብ ሐቃቅ። ዐረ ሐቀ) ማገግ መደንገግ፤ መወሰን መቍረጥ፤ መጣፍ ማወጅ። የሥርዐት የትእዛዝ የፍርድ ያገዛዝ፤ የዘመን የጊዜ፤ ለዋጋም ይኾናል። ሐገና ዐ(አ) ገና ማለት ከዚህ የወጣ ነው። ሕግ ዘሐገገ ለክሙ እግዚ። አሕዛብኒ የሐግጉ ሎሙ ሕገ። ሙሴ ሐገገ ሎሙ ሕገ ፡ (ዘፀ፳፬ ፡ ፰። ሮሜ፪ ፡ ፲፬። ሃይ ፡ አበ ፡ ፪)።
ኀጡእ ፤ (ኣን ኣት ጥእት) ፤ ያጣ ፤ የተቸገረ የሌለው ድኻ። ኂጡእኬ አንተ አሐተ ነገረ። ኅጡአ ልቡና። ኅጡአ ንዋይ። ዲያቆን የሐውጽ ድዉየ ወኅጡኣነ (ፊልክ ፡ ፫። ፍ ፡ ነ ፡ ፵፩ ፡ ፪። አፈ ፡ ተ፳። ፈ ፡ መ ፡ ፴፩ ፡ ፪)።
፡ የታጣ የሸሸ ፤ የኰበለለ። ወየአምሩ ከመ ኅጡእ ውእቱ። እንዘ ኅጡእ እምገጸ ሳኦል (፩ነገ ፡ ፳፪ ፡ ፲፯። ፩ዜና ፡ ፲፪ ፡ ፩)።
ሐጢብ ቦት ፡ (ሐጠበ የሐጥብ ይሕጥብ። ዕብ ሐጣብ። ዐረ ሐጠበ) መቍረጥ መፍለጥ መክትከት፤ መስበር መሰባበር፤ መልቀም መሰብሰብ፤ የንጨት የማገዶ። ሤምናክሙ ትሕጥቡ ዕፀ ወትቅድሑ ማየ። ዘየሐጥብ ዕፀ። ይሕጥብ ዕፀ። ተሐጥብ ዕፀወ። ሶበ የሐጥብ ዕፀወ ይሤጽር በበ አርብዓ ጾረ ብእሲ እስከ ያነጢ ዘይጸውር ሎቱ ፡ (ኢያ፱ ፡ ፲፱ ፡ ፳፩። ዘዳ፱ ፡ ፭። ፫ነገ ፡ ፲፯ ፡ ፲። ገድ ፡ ተክ)።
ሐጣቢ ብ ፡ (ቢት ብያን ያት፤ ጠብት) የሚቈርጥ የሚፈልጥ፤ ሰባሪ ለቃሚ፤ ቀራፊ ቋሚ። እምሐጣበ ዕፅ አስከ ሐዋሬ ማይ። ሐጣብያነ ዕፅ ወቀዳሕያነ ማይ ፡ (ዘዳ፳፱ ፡ ፲። መቃ ፡ ገ፯)።
ሐጥብ ፡ ሐጥብ፤ ፡ (ዐረ ሐጠብ) የሙጋድ የማገዶ ዕንጨት፤ ፍልጥ ጭራሮ ጕቶ ጕልጥምት። ሥልሰ ኤልያስ ውስተ ዕፀ ሐጥብ ወውስተ አባለ ላሕም ማየ ሰዊጦ እሳተ እምሰማይ አውረደ ላዕሌሆሙ ፡ (ተረ ፡ ቄር ፡ ሳዊ)።
ሐፀረ ፡ ዐጠረ፤–ሐጺር ሐጸረ።
ሐጸበ ፡ ዐጠበ፤–ኀፂብ ኀፀበ።
ሐጸወ ፡ ሰለበ፤–ኀጺው ኀጸወ።
ሐጸየ ፡ ዐጨ፤–ሐፅይ ሐፀየ።
ሐጹር ፡ (ራት። ዕብ፤ ሐጼር) ዐጥር ቅጥር ከለላ፤ ወልወል ከቤት ውጭ ከቅጥር ግቢ በቤት ግራና ቀኝ ፊት ለፊት ያለ ደጅ ዐጥረ ገጥ። ሐጹር የዐውዳ። ማይ ሐጹራ። ደስያተ ሙሴ ወአሮን ሕዝበ እስራኤል፤ ዘሐጹረ ገጾሙ ኮነ ፍቅረ አምልኮ ዕፅ አስራብ ፡ (ድጓ። ናሖ፫ ፡ ፭። ቅኔ)።
፡ የሾኽ ዘለላ፤ በረት ዳስ። ወገብረ ህየ ሐጹረ ሎቱሂ ወለእንስሳሁ ፡ (ዘፍ፴፫ ፡ ፲፯)።
፡ ዕርድ ምሽግ፤ መታኰሻ ግንብ። ትነድቅ ሐጹረ ላዕለ ይእቲ ሀገር እንተ ትገብር ጸብአ ምስሌከ። ሕጽሩ ሐጹረ ውስተ ሀገር ፡ (ዘዳ፳ ፡ ፳። ፫ነገ ፡ ፳ ፡ ፲፪)።
ሐጺር ሮት ፡ (ሐጸረ የሐጽር ይሕጽር። ዕብ ሐጻር። ዐረ ሐጸረ) ማጠር መቅጠር፤ መክበብ ዙሪያውን መዝጋት መወስን፤ መጠበቅ መሰወር። ሐጸሩ አርእስተ አድባር። ሐጸሩኒ በሐሰት። አሐጽር ፍኖተ በሦክ። ሐጸሮ ለማይ በትእዛዙ። ሐጸርዋ ለባሕር በአናቅጽ። ይሕጽርክሙ በሐጹረ መስቀሱ ፡ (ዮዲ፭ ፡ ፩። ሆሴ፲፩ ፡ ፲፪። ፪ ፡ ፰። ኢዮ፳፮ ፡ ፲። ፴፰ ፡ ፰። ግንዘ)።
ሐጺን ፡ ብረት፤–ኀጺን።
ሐፂን ኖት ፡ (ሐፀነ የሐፅን ይሕፅን) ማቀፍ፤ ማጥባት ማሳደግ፤ የልጅ። እንተ ተሐፅኖ ወታጠብዎ። ተሐፅን ሳራ ሕፃነ። እለ የሐፅና። ወለት እንተ ሐፀና። መፍትው ሕዝበ ክርስቲያን እለ አልቦሙ ውሉድ ይሕፅንዎሙ ለዕጓለ ማውታ ፡ (ኩፋ ፡ ፵፯። ዘፍ፳፩ ፡ ፯። ማቴ፳፬ ፡ ፲፬። አስቴ፪ ፡ ፯። ዲድ ፡ ፲፰)። ለንጨትና ለሣር ለጠጕርም ይነገራል። ማይ ሐፀኖ ፡ -ሐፂኖቱ ወፀፊሮቱ ፡ (ሕዝ፴፩ ፡ ፬። ፍ ፡ ነ ፡ ፶፩)። በሴሰየ ፈንታ ሐፀነ ይላል፤ ምስጢሩ ከማጥባት ይገባል። የሐፅኖ ለሢበትኪ፤ ያረጀ ሰውነትሽን ፡ (ሩት፬ ፡ ፲፭)።
ሐጺጽ ጾት ፡ (ሐጸ፤ ሐጸጸ የሐጽጽ ይሕጽጽ። ዕብ ሐጻጽ፤ ከፈለ) መጕደል ማነስ፤ መከፈል መቀነስ፤ እኩሌታ እስከ መኾን ድረስ። ኀጠጠን እይ፤ የዚህ ጎር ነው። ሐጸ ማይ። የሐጽጽ የሐጽጽ ልቡ ከመ ወርኅ። እለ የሐጾሙ አእምሮ። ኢየሐጽጽ መዐተ ንጉሥ እመዐተ አንበሳ። ኢይሕጽጽ እክልከ። ፡ (ዘፍ፰ ፡ ፫። ሢራ፳፯ ፡ ፲፩። ምሳ፱ ፡ ፬። ፳ ፡ ፪። ኩፋ ፡ ፴፩)።
ሐጻረ ዔኖን ፡ ስመ ሀገር፤ የደማስቆ ክፍል፤ የምድረ እስራኤል ዳርቻ ፡ (ሕዝ፵፰ ፡ ፩)።
ሐጻሪ ፡ (ሪት ርያን ያት፤ ጸርት) የሚያጥር የሚከብ፤ ዐጣሪ ከባቢ።
ሐፃኒ ፡ (ኒት ንያን ያት፤ ፀንት) የሚያቅፍ የሚያጠባ፤ አሳዳጊ ሞግዚት። ሐፃንያትኪ። ወልደ ሐፃኒቱ። መምህር ወሐፃኒ። ሐፀንተ ደቂቁ ፡ (ኢሳ፵፬ ፡ ፳፫። ግብ፲፫ ፡ ፩። አፈ ፡ ድ፴፬። ፬ነገ ፡ ፲ ፡ ፩)።
ሐፃዪ ፡ (ዪት ይያን ያት፤ ፀይት)። የሚያጭ፤ ማጫ የሚሰጥ፤ ዐጭታ።
ሐፄ ፡ (ሐፃዪ) ዐጤ፤ የመንግሥት ዕጮኛ፤ በዓለ መንግሥት ሕዝብና ካህናት ዘውዱን ዙፋኑን እንደ ሙሽራ ባርከው መርቀው የሚሰጡት፤ ተቀጸል ጽጌ የሚሉት። አኮ በቃለ ሐፄ ወአኮ በመኰንን ፡ (ታሪ ፡ አኵ)። የንግሥና የተክሊል ሥርዐት አንድ ስለ ኾነ ሙሽሮችም በጫጕላቸው ወራት ሐፄና እተጌ ወይም ንጉሥና ንግሥት ይባላሉ። ወይወስዱ ለንጉሥ ደናግለ ድኅሬሃ ወያበውእዎን ውስተ ጽርሐ ንጉሥ፤ ጫጕላ ፡ (መዝ ፡ ፵፬)። ሐፄና ዐጤ ስለ ማለት በዐረብና ባማርኛ ብዙ ተረትና አፈ ታሪክ አለ።
ሐፄጌ [1] ፡ ሐፃዬ ምድር፤ ፈኃሪሃ ለምድር፤ ንጉሠ ምድር እግዚአ ምድር። ባለርስትን ባለጌ እንዲሉት፤ የጌን አፈታት እይ። ተቀጸል ጽጌ ሐፄጌ ፡ (የድጓ ፡ ግስ)።
[2] ፡ (ማእከላይ ስም) ዘይቤው ዕጨ ዕጨጌ፤ ሱታፌ ንጉሥ፤ ባለሢሶ መንግሥት። ምስጢሩ ሊቀ ሀገር ሊቀ ካህናት፤ ርእሰ አድባራት ወገዳማት። ኢትዮጵያ እንደ ኒቅያ ሕግ ትምርቱንና ንጽሕናውን ጠባዩንና አናዎሩን አስተዳደጉን አይታ መርምራ፤ ይደልዎ ብላ መርጣ መስክራ ባልሾመችው ሌሎች ከወገናቸው መርጠው በሚሾሙት፤ ቋንቋውን በማታውቀውና ቋንቋዋን በማያውቅላት በባዕድ በንግዳ በውጭ አገር ጳጳስ ታዞ ተናዞ መኖርን ስለ ወደደች፤ ፪ኛም ክብሯንና መንበረ ክብሯን አካታ ፈጽማ ይቅርብኝ ብላ ለባዕድ መስጠትን ስለ ጠላች፤ አፍኣዊ ስሙን መለካዊ ወይም ባስልዮስ እንደ ማለት ሐፄጌ ብላዋለች እንጂ ውሳጣዊ ስሙ ጳጳስ ሊቀ ጳጳስ ነው። ጳጳስ ሲታጣም በግልጥ የጳጳስ ሥራ እየሠራ አቡንና ዕጨጌ ይባላል፤ ጳጳስም ቢኖር ላገሩ እንግዳ ለሕዝቡ ባዳ ስለ ኾነ፤ አፈ ድዳ ቀንደ ጐዳ መስሎ ያቀረቡለትን ቅስና ዲቁና ከመሾም በቀር ሊፈርድና ሊተች ሊሰብክ ሊያስተምር አይችልምና፤ በሕዝብና በካህናት ላይ ሥልጣኑ መብቱ ፍትሐ ነገሥቱ ወትሮ የጨጌ ነው። ወፈታሒሰ ውእቱ ሊቀ ካህናት፤ ወውእቱ ሊቀ ጳጳሰት፤አው ኤጲስቆጶስ፤ አው ዘአትለውዎ እሙንቱ ወረሰይዎ ህየንቴሆሙ በእንተ ፍትሕ። ይኩን ድኁነ ልሳን ወዘየአምር ነገረ ልሳን እንተ ኢትትከሀል፤ ልሳነ ሰብአ ሢመቱ በዘይትናገሩ በበይናቲሆሙ ፡ (ፍ ፡ ነ ፡ ፵፫)። በፅግዕና በፅጋዕ ዘይቤም ሲፈቱት፤ወምስማካሰ ለመንግሥትክሙ ውእቱ ክርስቶስ እንዳለው ኹሉ ፡ (ቄር) መጨጊያ መከዳ ያሰኛልና፤ ይህ ስም ዕጨግናን ከጵጵስና አዛምዶ አዋሕዶ አጣምሮ አስተባብሮ ያሳያል። ይኸውም እንደ ግራና ቀኝ መከዳ ንጉሡን አማኽለው አቡኑ በቀኝ ዕጨጌው በግራ በመቀመጣቸው ይታወቃል፤ አቡን ሲታጣ ግን ቀኙ የጨጌ ነው። ዕጨግነትም የተዠመረ ባ፲፪፻፷፫(፶፫) ዓመት ይኩኖ አምላክን ቀብተው ባነገሡ በዳግማይ ተክለ ሃይማኖት ነው፤ ርሳቸውም በናታቸው የነገሥታት ወገን የይኩኖ አምላክ ያክሥት ልጅ ወይም የናት ወንድም አጎት፤ ወዲህም የደብረ ሊባኖስ አበ ምኔት ነበሩ ይባላል። ፊት በሕግ ቀሰው በኋላ መንኵሰው አቡን ስለ ኾኑ ያልተማሩ ሰዎች የማይገባ መስሏቸው፤ አቦ ብልኀት ዕጨግነት ከሚስት ብለዋቸዋል። ዳግማይ ማለትም በ፯ኛው ፡ (ሴክል) መቶ ይህን ሐዲስ ስም ተክለ ሃይማኖት መባልን እንደ ያዕቆብ በጌታ ቃል ለተሰየሙት፤ ለጻድቁና ለቅዱሱ ለታላቁ ሐዋርያ እንጂ፤ ባ፲ኛው ፡ (ሴክል) መቶ መንግሥትን ከድልነዓድ ወስዶ መዠመሪያ ከዛጔ ወገን ለነገሠው መራ ተክለ ሃይማኖት ለተባለው ለላስታው ንጉሥ እይዶለም። በጻድቁና በጨጌው መካከል ያለው ዘመን ካ፭፻፶ ቢበልጥ እንጂ አያንስም ፡ (ታሪክና ገድል)። ጳጳስን እይ።
ሐጽ [1] ፡ ፍላጻ፤–ሐጺጽ ሐጸ።
[2] ፡ (ብ አሕጻጽ፤ አሕጻ ጻት። ዕብ ሔጽ) ፍላጻ፤ ስለቱ የሚፈልጥ የሚቆርጥ፤ የሚከፍል፤ የሚሠጥቅ፤ በቀስት የሚነደፍ፤ የሚወረወር። ፪ኛም ዐጭር ቀጭን ታናሽ ቀላል፤ ከዘገር ካበታ ጦር የሚያንስ ሕጹጽ ማለት ነው። ይበውእዋ በሐጽ ወበቀስት። ፈነወ አሕጻሁ ወዘረዎሙ። አስተዳለዉ አሕጻቲሆሙ። ይደራበዩ በአሕጻት ፡ (ኢሳ፯ ፡ ፳፬። መዝ ፡ ፲፯። ፲ ፡ ፪። ፊልክ ፡ ፻)።
ሐጽረ ፡ ዐጭር ኾነ፤–ኀጺር ኀጽረ።
ሐፅረ ፡ ዐጭር ኾነ፤–ኀጺር ኀጽረ።
ሐፅይ ዮት ፡ (456) ፡ (ሐፀየ የሐፂ ይሕፂ። ፈኀረ) ማጨት፤ ማጫ ማሥመሪያ ዐረቦን መስጠት፤ የልጃገረድ። ለአከ ንጉሥ ይሕፅያ ሎቱ። የሐፂ ሕፄሃ ለአቡሃ። ብእሲትየ እንተ ሐፀይክዋ በምእት ቍልፈት ፡ (ዮሴፍ። ዘፀ፳፪ ፡ ፲፮። ፪ነገ ፡ ፫ ፡ ፲፬)።
ሐፈሠ ፡ (ሐፈነ) ዐፈሠ ተረፈሰ፤ አብዝቶ ዘገነ ዛቀ። አነሣ ወሰደ፤ ጠረገ አሶገደ። ወሐፈሥዎ በድኖ ለሳኦል። ዐውሎ ዘየሐፍሦ። ይነሥኦሙ ዐውሎ ወየሐፍሦሙ ነፋስ ፡ (፩ዜና ፡ ፲ ፡ ፲፪። ኢሳ፲፯ ፡ ፲፫። ፶፯ ፡ ፲፫)።
ሐፈጠ ፡ መታ ደሰቀ፤–ኀፊጥ ኀፈጠ።
ሐፊን ኖት ፡ (ሐፈነ የሐፍን ይሕፍን። ዐረብ። ዕብ ሐፋን) ማፈን መሸፈን፤ መዝጋት መድፈን፤ ማፈሥ መዝገን፤ መጨበጥ መጀቦን፤ ባንድ ወይም በ፪ እጅ መታፈን።
ሐፍሥ ፡ (ሕፍን) ዝግኝ ጥርኝ ጭብጥ። ጥቂት ታናሽ ገንዘብ በረከት እጅ መንሻ ግብር፤ ለጣዖት ለጠንቋይ የሚሰጥ። ይሁቡ ሐፍሠ በእንቲኣሁ። እምዘትነሥእ ሐፍሥ ፡ (ኢሳ፰ ፡ ፳። ግብ፲፮ ፡ ፲፮)። ኵባያ ጽዋ። ሐፍሠ ወይነ ዘቢብ ፡ (ሆሴ፫ ፡ ፩)።
ሐፍሦት ፡ (ዕብ ሖፍሺት) ነጻነት ሐራነት፤ ብችነት ከሰው መለየት። ቤተ ሐፍሦት። የድውያን ቤት፤ ለምጻሞችና ኮብሻሞች ደዌያቸው ከሰው እንዳይናኝ ለብቻቸው የሚኖሩበት ፡ (፪ዜና ፡ ፳፭ ፡ ፳፩)።
ሑል [1] ፡ (ዕብ ሖል) ተርታ መናኛ መካከለኛ፤ ፍጹም ርኩስ ያይዶለ፤ መሥዋዕትና ቍርባን የማይኾን፤ ለሕዝብ የሚገባ ሕዝብ የሚበሉት። ይምሀሩ ለሕዝብ ማእከለ ፡ (ንጹሕ) ቅዱስ ወሑል ፡ (ሕዝ፵፬ ፡ ፳፫)።
[2] ፡ መካከለኛ፤–ሐዊል ሐወለ።
ሑሰት ፡ (ታት) ፡ መፍጠን፤ መታወክ መናወጥ፤ መንቀሳቀስ፤ ንቅነቃ። ሑሰታ ለጥበብ ይፈጥን እምኵሉ ሑሰት። በሑሰተ ልብነ። ሑሰተ ባሕር። ረሰይከነ ሑሰተ ርእስ ለሕዝብ። ውልዋሌ ወሑሰተ ነፍስ ፡ (ጥበ፯ ፡ ፳፬። ፪ ፡ ፪። ሔኖ፻፩ ፡ ፮። መዝ ፡ ፵፫። ፊልክ ፡ ፶፬)።
ሑረት ፡ (ታት) መኼድ፤ አካኼድ፤ ኦናዎር፤ ኑሮ። ሑረት ወግብአት። ሑረተ ብእሲተ ብእሲ። ሑረተከ በሰላም ያሠኒ። መምህር ይኩን ንጹሐ በሑረታቲሑ ወጽሩየ በፍናዋቲሁ። በእንተ ሠናይ ሑረታቲሁ ለሕዝብ ፡ (ዘካ፯ ፡ ፲፬። ቀሌ። ፈ ፡ መ ፡ ፩ ፡ ፭። ዮሴፍ)።
ሑቃፌ ፡ ዝኒ ከማሁ፤ ዐቀፋ ዕቅፊያ ቅበላ ፡ (አርጋ ፡ ፩)።
ሑቡር ፡ (ራን ራት ብርት) ቀለም የገባ የታለለ፤ የተሸለመ የተጌጠ፤ ቀይ ጥቍር ዝንጕርጕር። በአልባሰ ወርቅ ዑጽፍት ወሑብርት። አልባሰ ቅዳሴ ይኩና ፀዓድወ ወአኮ ሑቡራተ። ዑጽፍታ ታንሶሱ ወታስተሪ ሑብርታ ፡ (መዝ ፡ ፵፬። ፍ ፡ ነ ፡ ፲፪)።
ሑብርታት ፡ (የሑብርት ብዢ) ሽልምልሞች፤ ዝንጕርጕሮች፤ ባለብዙ ሕብሮች። ሀሎ ዲቤሁ ልብስ ጥቁብ፤ ወቦ ውስቴቱ ሑብርታት ፡ (ፊልክ ፡ ፻፴፮)።
ሑት [1] ፡ (ዐረ እልሑት) ከመ ኮከብ፤ ካ፲፪ቱ መናዝል አንዱ። በየካቲት ከፀሓይ ጋራ ፴፩ ዕለት ፲ ኬክሮስ ይመግባል። ፍችው ዓሣ ማለት ነው። ፡ (አቡሻ ፡ ፬)።
[2] ፡ ኮከብ፤–ሐወተ።
ሑዥራ ፡ ሠግር፤–ሁጅ(ግ) ራ።
ሑያጼ ፡ (ሕዋጼ) ማስተዋል መመልከት፤ አስተያየት። ግምት መላ ጥንቈላ፤ ሕልም ቅዠት በቀን ያዩትን ወይም ያሰቡትን ሊት ማለም። ወይከውኑ እለ ያስተሐይጹ በሑያጼ ወርኅ ፡ (ኩፋ ፡ ፮)።
ሑጻጼ ፡ ዝኒ ከማሁ፤ መጕደል ማነስ፤ ጕድለት፤ ነውር። ዘአልቦ ሑጻጼ። ፍድፋዴ ወሑጻጼ። እምኢኮነክሙ ሑጻጼ ወዘለፋ ፡ (አዋል። ፍ ፡ ነ ፡ ፴፩። ዮሴፍ)።
ሐሚቅ ቆት ፡ (ሐመቀ። ዐረ ሐሚቀ) ማበድ መክነፍ፤ ክፉ መጥፎ መኾን።
ሒሰት ፡ መንቀፍ፤ መነቀፍ አነቃቀፍ፤ ነቀፋ ነቀፌታ ስድብ።
ሒስ ፡ ነውር ገመና፤ ኀጢአት በደል የሚያስነቅፍ ነገር፤ ነቀፋ። ንጹሕ አንተ እምዝ ሒስ ዘኅቡኣት። እንተ እንበለ ሒስ። ዘአልቦ ነውር ወሒስ። ሒስ ንስቲት ፡ (ሔኖ፷፭ ፡ ፲፩። አስቴ፰ ፡ ፲፫። ጥበ፲ ፡ ፲፭። ፲፫ ፡ ፮)።
ሒከት ፤ ማላመጥ ፤ አስተኛኘክ አበላል።
ሒክ ፡ (ዕብ ፡ ሔኽ) ላንቃ ትናጋ፤ ያፍ ውስጥ ላይኛው ክፍል ዋሻው። የላይና የታች የግራ የቀኝ መንጋጋ መፍጫው ማላመጫው። ሐነከን እይ።
ሔለይ ፡ በቁሙ፤ ዔሊ ደንጊያ ልብሱ። ልዝብ ልሙጽ፤ ወይም ጯኺ ድምጠ ቀጭን።
ሔልዩ ፡ (ጽር ሒሊዉ) ፀሓይ፤ ሥዕለ ፀሓይ። ሀገረ ሔልዩ ፡ (ዘፍ፵፩ ፡ ፵፭። ሕዝ፴ ፡ ፲፯)።
ሔሴፎት ፡ የጕድፍ መጣያ፤–ሀሴፎት።
ሔረቅ ፡ (ትግ ሐባብ ሔረቅረቅ) ቃታ፤ የሳንባ በሽታ፤ ስንባብ።
ሔረግ ፡ ዔረግ የሐረግ ቅርጫት። ሐና ዐ ተወራራሾች ስለ ኾኑ ሔ በዔ ተለውጦ ወደ ዐ ተራ ኺዷልና፤ ዔረግን እይ።
ሔሬቢ ፡ ሰይፋዊ፤ ሰይፋም ሰይፈኛ፤ ተዋጊ ሐርበኛ። ባለቅኔዎች ግን ፋቂ ዐራቢ፤ ባለነት ባለቈርበት ይሉታል፤መጥረቢያውንም መኵረቢ ይሉታል።
ሔር ፡ ቸር፤–ኀዪር ኄረ ኄር።
ሔቅ [1] ፡ (ዕብራ) ሕፅን ብብት፤ ድልድል መሠረት በሕንጻው ዙሪያ በመብቀያው እንደ ዕርከንና እንደ መደብ እንደ ዝናር ኹኖ የሚሠራ፤ ዙሮ ተጠምጥሞ የሚገጥም። ወሔቅ እመት፤ ወእመት ርሕቡ እምሔቀ ምድር ፡ (ሕዝ፵፫ ፡ ፲፫ ፡ ፲፬)።
[2] ፡ ሕፅን፤–ሐየቀ።
ሔት [1] ፡ ስመ ፊደል፤–ሐዪው ሐይወ፤ ሐየተ።
[2] ፡ (ዕብራ) ስመ ፊደል ሳምን፤ ሐውቶ ሐ፤ ዘሩ ሐዪው፤ ፍችው ሕይወት። ሐውትና ሔት አንድ ስም ናቸው። ሔት፤ ክፍልየ እግዚ ፡ (መዝ ፡ ፻፲፰ ፡ ፶፯–፷፬። ሰቈ፩ ፡ ፰። ፪ ፡ ፰። ፫ ፡ ፳፪። ፬ ፡ ፰)።
ሔትዮት ፡ (ዕብ ውሂትዊታ ታው) ምልክት፤ ስመ ፊደል ተ መስቀላዊ። ወጸሐፍ ሔትዮተ ውስተ ፍጽሞሙ ፡ (ሕዝ፱ ፡ ፬)። ውሂትዊታና ወጸሐፍ ፩ ናቸውና፤ ታወ ፥ ትእምርተ በማለት ፈንታ ሔትዮት ይላል፤ የተሳሳተ ነው፤ አንቀጹን ጥሬ አድርጎታል።
ሔኖክ ፡ (ዕብ ሐኖኽ) የሰው ስም፤ ሐዲስ ቅዱስ ማለት ነው ፡ (ዘፍ፬ ፡ ፲፯። ፭ ፡ ፲፰። ፳፭ ፡ ፬)።
ሔዋ ሔዋን ፡ (ዕብ ሐዋ) በቁሙ፤ መዠመሪያ ሴት የአዳም ሚስት፤ ሕያውት እመ ሕያዋን። ወሰመየ አዳም ስመ ብሲቱ ሔዋ፤ እስመ ይእቲ እመ ኵሉ ሕያው ፡ (ዘፍ፫ ፡ ፳)።
ሔው ፡ (ዕብ ሐይ) መዠመሪያ ወንድ አዳም የሔዋን ባል፤ ሕያው አበ ሕያዋን። ወነፍኀ በአንፉ መንፈሰ ሕይወት፤ ወኮነ ሕያወ በመንፈስ ፡ (ዘፍ፪ ፡ ፯)።
ሔው ሔዋ ፡ ስም፤–ሐይው ሐይወ።
ሕለት ፡ ዘንግ፤–ኀሊል ኀለለ።
ሕሉብ ፡ (ባን ባት ልብት) የታለበ ዕልብ ወተት፤ ወይም ጥገት፤ ጡት።
ሕላል ፡ ሠርቀ ወርኅ፤–ሀላል።
ሕላቅ ፡ (ቃት) ምዕማድ፤ የዐምድ እግር፤ ዐምድ የሚቆምበት ስክተት መሠረት፤ የዐምዱን ሥር ለመንከስ ለመጕረሥ አፉ እንደ ቀለበት ክብ የኾነ። ዲበ ምንት ስቁል ሕላቃቲሃ ፡ (ኢዮ፴፰ ፡ ፮። ቅዳ ፡ ኤጴ)።
ሕልመልሜሌክ ፡ ስመ ኮክብ ዐቢይ፤ መጋቤ ሐጋይ፤ ካራቱ ዐበይት ከዋክብት አንዱ። ዘይቤው ሕልመ ንጉሥ ማለት ይመስላል፤ ምስጢሩ ግን ታላቅነት ነው። ፪ኛ ስሙ ፀሓይ ይባላል፤ ምግብናውም ፺፩ ቀን ነው ፡ (ሔኖ ፡ ፷፬)።
ሕልም ፤ (ማት። ብ ሕለም አሕላም ፤ ማት) ፤ በቁሙ ፤ በንቅልፍ ውስጥ የሚታይ ነገር ፤ እንደ ትንቢት ያለ። ሕልም ፪ ወገን ነው ፥ የነፍስ የሥጋ ፤ የነፍስ ሕልም ፍሬ ያለው ነው ፤ ትንቢት ራእይ ይባላል (ዘፍ፴፯ ፡ ፮። ፵፩ ፡ ፩። ዳን፪ ፡ ፩)። የሥጋ ሕልም ግን እንደ ምትሀት ኹኖ ቅዠት ይባላል ፤ ከንቱ ማለት ነው ፤ ለኹሉም ከፉና በጎ አለው ፤ ሳሕስሐን እይ። ወሕልምኒ ከንቱ ያደነግፆ ለአብድ። እስመ ለብዙኃን አስሐቶሙ ሕልም። ሕልም ዘዝሙት። አሕላም እኵያት።አሕላማት ሕሡማት (ሢራ፴፩ ፡ ፩ ፡ ፯። ፈ ፡ መ ፡ ፲፬ ፡ ፰። አፈ ፡ ድ፳፬። ፊልክ ፡ ፻፷)።
ሕልቀት ፡ (ታት) ቀለበት፤ የጣት ጌጥ፤ ሌጣ ሰንኬቶ ወይም ፈርጥና ማኅተም ያለው። ሕልቀትየ ዘአጽባዕትየ። ሕልቀተ ወርቅ ውስተ አጻብዒሃ። አውፅአ ንጉሥ ሕልቀቶ። ሕልቀተ ማዕተብ(ኩፋ ፡ ፵፩። ገድ ፡ ተክ። አስቴ፫ ፡ ፪። ሢራ፵፱ ፡ ፲፩)። ያፍጫ ስናግ የብረት ቀለበት፤ እንደ ሰዓት ፍንጅ የሚከፈትና የሚዘጋ። ሕልበትን እይ።
ሕልቅ [1] ፡ (ብ አሕላቅ) ጕንጭ፤ መንጋጋ ከነመላሱ ወይም ከነራሱ፤ ከናናቱ ከነጭንቅላቱ። ዘይሁብዎ ለካህን መዝራዕተ ወሕልቀ ፡ (ዘዳ፲፰ ፡ ፫)። ጕረሮ፤ ክበብ ክርክር ያለው ውስጠ ክፍት፤ መዋጫውና መሰልቀጫው።
[2] ፡ (ጽር ዖልኪ። ዕብ ቤቃዕ)። ድሪም፤ የዲድርክም አላድ ወይም የሰቅል እኩሌታ። ዲናርን ድርሀምን ድርከሜን እይ፤ ከዚህ ጋራ አንድ ነው፤ ባለብሉዮች ግን ወቄት ይሉታል። ነሥአ አዕኑገ ዘወርቅ ዘዘ ሕልቅ ድልወቱ፤ ወአውቃፈ ዘዘ ዐሥሩ ሕልቅ ድልወቱ ፡ (ዘፍ፳፬ ፡ ፳፪)።
ሕልበት ፡ ማለብ፤ መታለብ አስተላለብ። አፍንጫ፤ ያፍንጫ ጕንጭ ግራና ቀኙ፤ ወይም መካከሉ ሹሉ የሚሰነገው። ተአስርኑ ሎቱ ሕልቀተ ውስተ ሕልበቱ ፡ (ኢዮ፵ ፡ ፳፩)። በቁሙ፤ ዕልበት አብሽ፤ ካብሽ የሚሠራ የጦም ወጥ ፡ (ዐማርኛ)።
ሕልያን ፡ (ዐረ ሑልዋን፤ በርጢል። ዕብ ሾሐድ። ሱር ሾሓዳ) መማለጃ ጕቦ፤ ክፉ ስጦታ፤ ለመጥፎ ዳኛና ላባይ ምስክር የሚሰጥ። ያፈቅሩ ሕልያነ። ይነሥኡ ሕልያነ። አምኃ ወሕልያን ያዐውሮሙ ለጠቢባን ፡ (ኢሳ፩ ፡ ፳፫። ፭ ፡ ፳፫።ሢራ፳ ፡ ፳፪)።
ሕልጽ ፡ ወገብ፤ የትጥቅ ሙያ፤ ከጭን ማውድና ከባላው በላይ ከጐድንና ከሕንብርት በታች መካክሉ። ሐቌን እይ፤ ከዚህ ጋራ አንድ ነው፤ ባለቅኔዎች ግን ለይተው ኅምስ ኃምሳይ ሕዋስ ኀፍረተ ብእሲት ይሉታል። እመኒ ተኀብአ ማእከለ አቍያጽ፤ እምተረግዞ ኢያምሠጠ ሕልጽ ፡ (ቅኔ)።
ሕመሜ ፡ ሕመሜ፤ መመቅኘት፤ ምቀኝነት፤ ተንኰል ሽንገላ የሚያናድድ ነገር። እምሕመሜ እኩይ። ወሕመሜ ይትናገር አፉሆሙ ፡ (ቅዳ። ምሳ፳፬ ፡ ፪)።
ሕመቅ ፡ እብደት፤ እብድነት፤ ክፋት ቅለት።
(ጥ) ሕመት [1] ፡ (ሳቢና ጥሬ ዘር) መሞቅ፤ አሟሟቅ። ሙቀት ትኵሳት። ጥቀርሻ ጥላት፤ ክሰል የሕሳት ትራፊ መልሶ እሳት የሚበላው፤ ከንጨት ከደንጊያ የሚወጣ ፍጹም ጥቍር። ጸሊም እምነ ሕመት ራእዮሙ። ጸሊም ከመ ሕመት። ማየ ሕመት ፡ (ሰቈ፬ ፡ ፰። ሄርማ ፡ ገ፸፬። ፪ቆሮ ፡ ፫ ፡ ፫)።
[2] ፡ ክሰል፤–ሐመመ።
ሕመግ ፡ እድፍ፤ ጭቅቅት ኀጢአት፤ የአእምሮ ዝገት፤ ድንቍርና። ንጹሕ ውእቱ ወአልቦ ውስቴቱ ሕመግ ፡ (አፈ ፡ ድ፴፬)።
ሕሙም ፡ (ማን ማት ምምት) የሞቀ ሙቅ፤ የታመመ ድዉይ፤ ሕዙን። ማይ ሕሙም፤ ፡ (ሙቅ ግም ድፍርስ)። ብእሲሁ ቅሡፍ ወሕሙም። ሕሙማን ይፈቅድዎ ለዐቃቤ ሥራይ። ኵሉ ዓለም ሕሙም ወትኩዝ። ተንሣእኩ ሕሙምየ ፡ (ዐዝኜ)። ሕምምት ነፍስየ ፡ (ስንክ ፡ ጥቅ፳። ኢሳ፶፫ ፡ ፫። ማቴ፱ ፡ ፲፪። ሮሜ ፡ ፳፫። ዕዝ፬ ፡ ፭። ሱቱ ፡ ዕዝ፱ ፡ ፵፩)።
ሕሙስ ፡ (ዐረብ) ሽንብራ፤ የቀይ ዳማ። የታመሰ ዕምስ።
ሕሙቅ ፡ (ቃን ቃት ምቅት) ያበደ እብድ፤ መጥፎ ምኑን ከንቱ ብልሹ። እፎ ትትመየጡ ዳግመ ውስተ ኀሳር ወሕሙቅ ነገር ፡ (ቄር ፡ ስም። ገላ፬ ፡ ፱)።
ሕሙይ ፡ (ያን ያት ሚት) የታማ የተነቀፈ፤ ስዱብ ንቁፍ። ግብረ ሕሙይ፤ ፍትወት ሕሙይ።
ሕሙድ ፡ (ዳን ዳት ምድ) የታመደ፤ የተበላ የተቃጠለ፤ ሐመድ የኾነ ፡ (መጽ ፡ ምስ)።
፡ ዐሟዳ አፍንጫ ጐራዳ፤ ዝንጀሮ ፊት፤ ኵርፋድ።
ሕሙግ ፡ (ጋን ጋት ምግት) የታመገ ዕምግ፤ ክፉ ጥፉ ብልሹ፤ ድፍርስ። ማይ ሕሙግ። ወይን ሕሙግ፤ መብልዕ ሕሙግ የሐምጎ ለልብ ፡ (ኤር፪ ፡ ፲፰። ፈላስ ፡ ገ፲፫)።
ሕማም ፡ (ማት) ትኵሳት ንዳድ፤ በቁሙ በሽታ፤ ሐዘን ጭንቅ መከራ፤ ወይሌ ዋይታ ወዮታ። ክቡድ ሕማም። ኀበ አልቦ ደዌ ወአልቦ ሕማም። ከመ ይፈጽም በሕማማት። ሕማሙ ለዝ ዓለም። አሐቲ ሕማም፤ ካልእት ሕማም ፡ (ሢራ፴፬ ፡ ፪። ቀሌ። ዕብ፪ ፡ ፲። ሮሜ፰ ፡ ፲፰። ራእ፱ ፡ ፲፪። ፲፩ ፡ ፲፬)።
ሕሜት ሕምየት ፡ (448) ማማት መንቀፍ፤ መታማት መነቀፍ።
ሕማምት ፡ (ትግሬ) ያውሬ ስም ግስላ፤ ቍጡ ብስጩ ተናዳጅ።
ሕምል ፡ (ላት። ዐረ ሒምል) ሸክም፤ ጭነት። ዕሥራ እልፍ ሕምለ ሥርናይ ፡ (ዮሴፍ)።
ሕምር ፡ ሕምር፤–ቀይ ዐይነት፤–ኅምር።
ሕምዝ ፡ መርዝ፤ የተቀመመ መድኀኒት የሚገድል የሚያድን። ከእንስሳትና ከአራዊት ከተሐዋስያን፤ ከዕፀው ከአሥራው ከሣር ከቅጠል፤ ከቋያና ከቡቃያ ወገን ከማግስኞ ፍጥረት የሚገኝ፤ መራራ ሖምጣጣ ጐምዛዛ። ዘከመ እንስሳት እለ ቦሙ ሕምዝ፤ ወዘከመ አራዊት መሣጥያን እለ ይሴሰዩ ሕምዛተ። ወበቍላትኒ ቀታልያን እለ ያማስንዎ ለልብ ወለኵሉ ዘሥጋ በበሊዖቱ። ወላዕለ ዝንቱ ፍትሕ፤ እመ ተረክበ እምነ ዝንቱ ክፍል አሐዱ ጾታ ዘያማስን ጥዑየ ወዘይፌውስ ድዉየ፤ ይትገሐሥ ጥዑይ እምበሊዖቱ፤ ወለድዉይሰ ብዉሕ ከመ ይብላዕ እመንገለ ጾታ መድኀኒት ፡ (ፍ ፡ ነ ፡ ፳፫)።
፡ ቍጣ መዐት፤ ክሕደት ኀጢአት። ዐቢይ ሕምዙ። መሠረታተ ሕምዝ ፡ (ራእ፲፪ ፡ ፲፪። ቅዳ ፡ ዲዮ)።
፡ መራራ ሸካራ ክፉ ነገር፤ ሰው የሚጐዳ ቃል። ሕምዘ አርዌ ምድር ታሕተ ከናፍሪሆሙ ፡ (መዝ ፡ ፻፴፱)። መሪር፤ ሐሞት፤ ዕጕሥታር በማለት ፈንታ። ሕምዝ ይላል፤ መራራ ክፋ ማለት ነው። እግዚ አስተየኒ ማየ ሕምዝ። አጽገበኒ ሕምዘ። ምረተ ሕምዝየ ፡ (ኤር፰ ፡ ፲፬። ሰቈ፫ ፡ ፲፭ ፡ ፳። ዘዳ፳፱ ፡ ፲፯)። ባወራረድና ባንጻር አፈታት ባለብሉዮች ሰራዊት ባለቅዳሴዎች ምድር ይሉታል።
ሕምገት ፡ ማመግ መታመግ፤ መደፍረስ አደፈራረስ፤ ድፍረሳ ድፍስነት ፡ (ሄርማ ፡ ገ፶፩)።
ሕሠም ፡ (ማት) ክፋት፤ ክፉነት መጥፎነት፤ የመልክ። ኢታስተአክዮ ለሰብእ እንበይነ ሕሠሚሁ። ኢይክሉ ይክድኑ ሕሠሚሆሙ በተሰርግዎ። ሕሠመ ራእየ ብእሲቱ ፡ (ሢራ፲፩ ፡ ፪። አፈ ፡ ተ፲፭። ፍ ፡ ነ ፡ ፳፬ ፡ ፩)። ለጠባይና ለግብርም ይኾናል። በእንተ ሕሠመ ግዕዙ። አህ እምዛቲ ሕሠም። ገቢረ ሕሠማት ፡ (ፍ ፡ ነ ፡ ፳፬። አፈ ፡ ተ፲፭። ፈላስ)።
፡ ጥፋት፤ ጕዳት። ዘኢይረክቦ ሕሠም፤ ኵሉ ዘይረክባ እምሕሠማት። ኵሉ ግብረ ሕሠም ፡ (አርጋ። ፍ ፡ ነ ፡ ፳፰። ዮሴፍ)።
ሕሱል ፡ (ላን ላት ስልት) የተለበበ ልብብ፤ ስሑብ።
ሕሡም ፡ (ማን ማት ሥምት) የከፋ ክፋ፤ ጥሩ መጥፎ ቢስ። ሕሡም ራእዮሙ። እለ ይትሐወሱ ሕሡማን። ምግባራት ሕሠማት። ኢታውሥእ ሕሡመ በአፉከ። ተአመን ከመ ሕሡም አልቦ ዘይረክበከ። ኢይረክባ ምንትኒ ሕሡም ፡ (ዘፍ፵፩ ፡ ፲፱። ጥበ፲፮ ፡ ፩። ዮሴፍ። ኢሳ፶፰ ፡ ፲፫። ሢራ፲፱ ፡ ፲ / ፍ ፡ ነ ፡ ፳፬ ፡ ፮)።
ሕሱብ ፡ (ባን ባት ስብት) የታሰበ፤ የተቈጠረ። መስተቃትላን እለ ሕሱባን ውስተ ሰርዌ ፡ (፩ዜና ፡ ፳፰ ፡ ፩)።
ሕሱይ ፡ (ያን ያት ሲት) የታሸ የለፋ ልፍ፤ ለስላሳ ልዝብ። ማእሰ በግዕ ሕሱይ ፡ (ዘፀ፳፭ ፡ ፭። ፳፮ ፡ ፲፬። ክብ ፡ ነገ፲፯)።
ሕሱፍ ፡ ሸካራ፤–ኀሢፍ ኀሠፈ።
ሕሳል ፡ (ላት) ልባብ ፉሎ፤ ፡ (ጥባ) ሽባ፤ ለኮ፤ የፈረስ የበቅሎ ማሰሪያ መሳቢያ ገመድ። ጠፍር። እለ በሕሳል ወበልኋም ይመይጥዎሙ መላትሒሆሙ ፡ (መዝ ፡ ፴፩)።
ሕሳዌ ፡ (ያት ውያት) መዋሸት፤ ዋሾ መኾን። ውሸት፤ ሐስት። በኢሕሳዌ ፡ (አፈ ፡ ተ፬። ፍ ፡ ነ ፡ ፭)።
ሕሥመት ፡ መክፋት ማስከፋት፤ ክፉነት መጥፎነት።
»ሕስት ፡ (ታት) ውሰት ትውስት፤ የተውሶ ዕቃ ከብት። በእንተ ሕስት፤ ሕስትሰ ነሢአ በቍዔት ውእቱ ዘእንበለ ቤዛ በገጽ እሙር። ዘከመ ዲናራት ወጠፋልሐ ብሩር ወዘይሰፈር ወዘይትሜዘን ልቃሕ ውእቱ ወአኮ ሕስት። በከመ ልብሰ ሕስት ከማሁ ብዕሎሙ ለኃጥኣን በቅድመ እግዚ። ኀላፊ ንብረት ከመ ጽላሎት ወከመ ልብሰ ሕስት ፡ (ፍ ፡ ነ ፡ ፳፰። መቃ ፡ ገ፲። ድጓ)።
ሕስው ፡ (ውት ሱት፤ ዋን ዋት) የተዋሸ፤ የታበለ ውሸት የኾነ። ሕስወ ተናገርከ። ይትኔበዩ ሕስወ። ሀብት ሕስው። ምትሀት ሕስው ፡ (ኤር፶ ፡ ፪። ጥበ፲፬ ፡ ፳፰። ምሳ፳፭ ፡ ፲፬። ስንክ ፡ መስ፲፭)።
ሕስየት ፡ ማሸት መታሸት፤ አስተሻሸት፤ ዕሽታት።
ሕሩም ፡ (ማን ማት ርምት) የተወ፤ ያረመ ሕርም ያለ፤ በገዛ እጁ የተከለከለ። ሕሩመ ሥጋ ወወይን። ከርሠ ድንግል ማርያም ሕርምተ ሩካቤ ወዘርዕ። ኄራን ወሕሩማን መስተጋድላን ፡ (ስንዝ ፡ መስ፪። ጥበ ፡ ጠቢ፹፩። ቄድር ፡ ገ፹፯)።
፡ የታረመ የተተወ፤ ሕርም የተባለ፤ የተከለከለ ክልክል፤ ተደራጊ። ሰስሎ እምነ ሕሩም። ገባሬ ሕሩማት። ዘተክልአ እምተዋስቦ ኀልዮ ከመ ሕርምት ይእቲ። ወዝንቱ ሕሩም ላዕለ ምእመናን ፡ (ዮሴፍ። ፈ ፡ መ ፡ ፱። ፊልክ ፡ ፪፻፲፬)።
፡ የተለየ የተቀደሰ። ልዩ ሕርም፤ ለግዜር የተስጠ። ሕሩመ ይኩንክሙ ለእግዚ። ንዋዩ ኮነት ሕርምተ ለእግዚ። ሕሩም ዘሐረሙ። ሀገር ሕርምት ፡ (ዘፀ፴ ፡ ፴፯። ፍ ፡ ነ ፡ ፲። ዘሌ፳፯ ፡ ፳፰ ፡ ፳፱። ኢሳ፲፱ ፡ ፲፰)።
፡ የተወገዘ ውጉዝ፤ ልዩ ርጉም። ይኩን ቅዉመ ወሕሩመ እምቤተ ክርስቲያን ፡ (ቀሌ)።
፡ ሹልዳ ጭን፤ የጭን ሥጋ እስራኤል የሚያርሙት። ሥርወ ሕሩም ፡ (ዘፍ፴፪ ፡ ፳፮ ፡ ፴፫)። ሐባቦች ሕርቱም ይሉታል።
ሕሩስ ፡ (ሳን ሳት ርስት) የታረሰ፤ የተገመሰ የተገለገለ የታየመ፤ የተዘራ።
ሕሩድ ፡ (ዳን ዳት ርድ) የታረደ የተራረደ፤ ዕርድ መሥዋዕት፤ ምሽግ።
ሕሩጽ ፡ (ጻን ጻት ርጽት) የተፈጨ የተደቈሰ፤ የደቀቀ የተሰለቀ። ልሕኵት ሕሩጽ። በእንተ ዐፅምከ በማሕረጽ ሕሩጽ ፡ (ሄርማ ፡ ገ፹፭። ስንክ ፡ ታኅ፲፩)።
(ጥ) ሕራር ፡ (ራት) ዕራሪ ከሰል፤ ጥቍር ዐመድ። ንሣእ ለከ ሕራረ ዕጣን። በሕራረ ዐፅሙ ወሥጋሁ ፈወሰ ፡ (ጦቢ፮ ፡ ፲፯። ፰ ፡ ፪። ስንክ ፡ ሐም፳፩)።
ሕርመት ፡ (ታት) በቁሙ፤ መተው መልክል ማረም፤ ሕርም ማለት። ሕርመተ ተዋስቦ ሕርመተ ሐራውያ። በእንተ ሕርመተ በሊዐ ሥጋ ፡ (ፈ ፡ መ ፡ ፭ ፡ ፩። ፍ ፡ ነ ፡ ፵፭። ቀኖ ፡ ግንግ)።
፡ አምልኮ፤ የአምልኮ ደንብ ሥርዐት። ፡ (ቆላ ፡ ፪ ፡ ፲፰። ያዕ፩ ፡ ፳፮ ፡ ፳፯)። ኢይግበር በዓለ አው ሕርመተ ምስሌሆሙ። ሕርመታተ አይሁድ። ወባዕደኒ ብዙኀ ሕርመተ የዐቅቡ ፡ (ቀሌ። መቃ ፡ ገ፲፭። ማር፯ ፡ ፬)።
፡ ሃይማኖት፤ ሕግ ባህል፤ ምስጢሩ ከአምልኮና ከሥርዐት ይገባል። ምንትኑ ሕርመትክሙ። ታቦት ዘሕርመት። ኢየብሩ ሕርመተ አይሁድ። በእንተ ሕጉ ለልዑል ወበእንተ ሕርመትከ። ዘኅቡእ ሕርመታ። ሕርመተ ትምህርት፤ ምስጢር ፡ (ስንክ ፡ ኅዳ፯። ዘፀ፴፩ ፡ ፯። ዮሐ፬ ፡ ፱። ሢራ ፡ ፵፪ ፡ ፪። ሮሜ፲፮ ፡ ፳፭። ኤፌ፮ ፡ ፲፱)።
ሕርም ፡ በቁሙ፤ ቃለ መሐላ ፡ (ዐማርኛ)።
ሕርሰት ፡ ማረስ፤ መታረስ፤ አስተራረስ፤ ዕርሻ ዐረሳ።
ሕርስ ፡ (ሳት) ዕርስ፤ ዕርሻ በሰላ ቅብቅብ ገራህት።
ሕርቱም ፡ ሕርቱም፤ ፡ (ማን ማት ትምት) የጐሰቈለ፤ ጐስቋላ፤ ብልሹ መጥፎ ወራዳ ምናምንቴ ልክስክስ። ሕርቱም አነ። ወልድ ሕርቱም። ብእሲ ሕርቱም። የሐይዉ ሕርቱመ። ውሉድ ሕርቱማን። ትውልድ ሕርቱማን ፡ (ኢሳ፮ ፡ ፭። ዲድ፲ ፡ ቀሌ።ጥበ፲፬ ፡ ፳፰። ሢራ፵፩ ፡ ፭። ኢሳ፶፯ ፡ ፬)። የሐረመ ስሯጽ ስለ ኾነ በሕርምት ፈንታ ሕርትምት ይላል፤ አያሰኝም። ወኢሰደደ ዳግሚተ ዘይእቲ ሕርትምት። ሰብሳብ ርኵስት ወሕርትምት። ረባሕ ርኵስት ወሕርትምት ፡ (ፈ ፡ መ ፡ ፭ ፡ ፬። ፬ ፡ ፬። ፲፰ ፡ ፩)። በትሕርምትም ፈንታ ሕርትምት ይላል ፡ (ስንክ ፡ ታኅ፲፫)።
ሕርትምና ፡ (ናት) ጕስቍልና፤ ጐስቋልነት፤ ምናምንቴነት፤ ክፉ ነገር፤ ውርደት ጥፋት ጕዳት፤ አደጋ መከራ። ይመጽእ ሕርትምና ላዕሌኪ። ወልደ ሕርትምና። ብክዩ ላዕለ ሕርትምናክሙ። ኵሎን ሕርትምናት ፡ (ኢሳ፵፯ ፡ ፲፩። ፪ተሰ ፡ ፪ ፡ ፫። ያዕ፭ ፡ ፩። ፈ ፡ መ ፡ ፪ ፡ ፭)።
ሕርደት ፡ ማረድ፤ መታረድ፤ መተራረድ፤ አስተራረድ፤ ዕርጃ ዕርድነት።
ሕቀ ሕቅ ፡ ሐቅ፤ ሕቍ፤–ሐቀቀ።
ሕቀት ፡ ሕቅታ ስርቅታ፤ ፀአተ ነፍስ፤ መጨረሻ ትንፋሽ።
ሕቁር ፡ (ራን ራት ቅርት) የተቈፈረ፤ የተመረመረ። የተናቀ የተነቀፈ፤ ቀላል ንቁፍ። ወኮኑ ሕቁራነ። በእንቲኣከ ሕቁር ፡ (ዘፀ፩ ፡ ፯። ተረ ፡ ቄር፯)።
ሕቁይ ፡ (ያን ያት ቂት፤ ቅይት) የተፋጨ የተጋጨ፤ የተፋተገ።
ሕቁፍ ፡ (ፋን ፋት ቅፍት) የታቀፈ፤ የተቃቀፈ፤ ዕቅፍ ዕቅፍቅፍ፤ በቅፍ የተያዘ፤ የተያያዘ ፡ (መጽ ፡ ምስ)።
ሕቍ ፡ (ቋት። ዕብ አልሞግ፤ ብ አልሙጊም፤ አልጉሚም) ሰንደል፤ እጅግ ክቡር ዕንጨት፤ ህንዳዊ ዛፍ መልካም ሽታ ያለው፤ እንደ አብኖስ በውድ የሚሼጥ የሚገዛ። አምጽኡ ሎቱ ወርቀ ወዕፀወ ሕቍ ፡ (፪ዜና ፡ ፲ ፡ ፲፩)። ቂጵርስስ አርዝ ፅፀ መዐዛ በማለት ፈንታ ሕቍ ይላል፤ የመላሽ ስሕተት ነው ፡ (ማሕ፩ ፡ ፲፮ ፡ ፲፯። ፪ዜና ፡ ፪ ፡ ፰። ራእ፲፰ ፡ ፲፪) ባለብሉዮች ግን፤ ዞጲ አብኖስ ሰኖባር ይሉታል።
ሕቅ ፡ (ቃት) ቅጽልና ንኡስ አገባብ። ጥቂት፤ ታናሽ ወራዳ የተናቀ። አምጽኢ ሊተ ሕቀ ማየ በግምዔ። ርእየ ሕቀ ደመና። እምድኅረ ዘመን ሕቅ። አንሰ ሕቅ ወንኡስ በቅድሜከ። ሕቀ አሕጸጽኮ። ታዕርፉ ሕቀ። ሕቀ ክመ ፡ (፫ነገ ፡ ፲፯ ፡ ፲። ፲፰ ፡ ፵፬። ፊልክ ፡ ፬። ፪ነገ ፡ ፯ ፡ ፲፱። መዝ ፡ ፰። ማር፮ ፡ ፴፩)።
፡ እጅግ ብዙ ዐያሌ፤ በጣም፤ ፈጽሞ። ዘበሕቁ ኀጺር። ኢታስተርኢ በሕቁ። ኢትርሐቁ በሕቁ። መስየ በሕቁ። ጸለየ በሕቁ። በሕቁ ጥቀ፤ ፈጽሞ ፡ (ዘሌ፳፩ ፡ ፲፰። ፲፫ ፡ ፬። ኢያ፰ ፡ ፬። ጦቢ፪ ፡ ፪። ስንክ። ቄር። ጰላ)።
ሕቅረት ሐቅረት ፡ መቃለል፤ ማቃለል ማስተሐቀር። አቀላለል፤ ቅለት። በፍና ሐቅረት ፡ (ቄር ፡ ጰላ)።
ሕቅፈት ፡ ማቀፍ መታቀፍ፤ አስተቃቀፍ። በእንተ ሕቅፈተ ሕፃን ፡ (ፍ ፡ ነ ፡ ፴፫)።
ሕበጥ ፤ (ጣት) ፤ ዕበጥ ዕባጭ ቍስል መግል የያዝ ያረገዘ። ትዕቢት ኵራት። አዝልፎ ስካር ያመጽእ ኮብሰ ወፈፅንተ ወቍስለ አማዑት ወሕበጠ አላ። ቍስል ወሕበጥ። ተፈወሱ ዝኵ ሕበጠ (ፍ ፡ ነ ፡ ፶። ፈ ፡ መ ፡ ፩ ፡ ፬። ተረ ፡ ቄር)።
ሕቡል ፡ (ላን ላት ብልት) ያበለ፤ የታበለ። ክፉ መጥፎ፤ ቍጡ ብስጩ፤ ዋዘኛ ዋሾ። ሕቡል ንጉሥ መኰንን ዐመፃ፤ ሕቡል ምክሩ። ወሕቡላንሰ። ነፍሳተ ሕቡላን። ሕቡል እንዘ ይትቀሠፍ ፡ (ኪዳ። ምሳ፲፪ ፡ ፳፬። ፲፫ ፡ ፱። ፲፱ ፡ ፳፭)።
ሕቡስ ፡ (ዐረ መሕቡስ) የታበሰ ሐብስ የገባ። ፂውው ወሕቡስ ፡ (ዮሴፍ)።
ሕቡይ ፡ (ያን ያት ቢት) የተዋሰ፤ የውሰት የተውሶ። ወዝንቱኒ ሕቡይ ፡ (፬ነገ ፡ ፮ ፡ ፭)።
ሕቢት ሕብየት ፡ ሕቢት፤ ሕብየት፤ መዋስ መሾም፤ ዋስትና ሹመት። ኢተሀብ ርእሰከ ለሕቢት። ከመ ዘይትሐበይ ሕቢተ ለዐርኩ ፡ (ሢራ፳፪ ፡ ፳፮። ምሳ፲፯ ፡ ፲፰)።
ሕብሉይ ፡ (ያን ያት ሊት) የተዘረፈ፤ የተበዘበዘ ብዝብዝ። የተዛረፈ።
ሕብል ፡ (ላት) ዕብለት ውሸት፤ ሐሰት ጕሕሉት፤ ተንኰል ክፋት፤ አሉታ ክዳት። ዘይዘርዕ ሕብለ የአርር እከየ። ወበከመ ብዝኀ ሕብሎሙ ስድዶሙ። ልሳንከ ፀፈራ ለሕብል። መጽአ እኁከ በሕብል። ከመ የአኀዝዎ በሕብል ፡ (ምሳ፳፪ ፡ ፰። መዝ ፡ ፭። ፵፱። ኩፋ ፡ ፳፮። ማቴ፳፮ ፡ ፬)።
ሕብልያ ፡ ብዝበዛ ዘረፈ፤ ቅሚያ ምርኮ። እሬስዮሙ ሕብልያ ወበርበረ። ወይከውኑ ሕብልያ ለእለ ይትቀነዩ ሎሙ። አንስትያነ ወደቂቅነ ይከውኑ ሕብልያ ፡ (ዮዲ፪ ፡ ፯። ዘካ፪ ፡ ፱። ዘኍ፲፬ ፡ ፫ ፡ ፴፩)። ፍግ ፋንድያ ዐዛባ፤ መሬት የሚያሠባ። ይከውኑ ሕብልያ ውስተ ገጸ ምድር ፡ (ኤር፰ ፡ ፪)።
ሕብረ ሰማይ ፡ (ዐረ ሐጀር ጀሃነም) በቁሙ፤ ሰማይ የሚመስል፤ የኵሕል ወገን ደንጊያ ቀለም፤ ለቍስል ለቂጥኝ የሚበጅ እንደሳት እንደ በርበሬ የሚፈጅ የሚተኵስ፤ ለብልቦ አንገብግቦ የሚፈውስ። ለዐይነ ማዝም ይበጃል እያሉ አሳርረው ከኵል ጨምረው ይኳሉታል። ግእዝ የማያውቅ ባላገር ግን በሕብር ፈንታ ክብር ይላል። ፡ (ሙሾ፤ ባሏ መንኖ ጥሏት ስለ ኼደ ፥ ጐዣሚት) እኔማ ሳልሰማ ቂጥኝ አውጥተው፤ ክብረ ሰማይ ብለው ኼዱ አቶ ይግዛው። ፡ (ተሰጥዎ) እሳት ነው እሳት ነው ክብረ ሰማይም፤ ሰማዕት የሚያቃጥል እንደ ቂጥኛም።
ሕብረ ሢራ ፡ ሰንጠረዥ፤ የሰንጠረዥ ዐይነት ጨዎታ፤ መጨዋቻው ቀለም የተቀባ እንደ ሥዕል እንዳሻንጕሊት ያለ ፡ (ፍ ፡ ነ ፡ ፵፫ ፡ ፲፪)።
ሕብረ ከብድ ፡ ጕበትማ፤ የጥቍር ቀይ፤ ደባባ ደባሳ ፡ (ዘፀ፴፭ ፡ ፳፭። ዘኍ፬ ፡ ፯ ፡ ፲፫)።
ሕብሩት ፡ (ታን ታት ርት) የተወለወለ የተሰነገለ፤ የታደሰ የተኰላ ጥሩ። ሕብሩት እምዛሕእ ጌጋይ ፡ (ደራሲ)።
ሕብር ፡ (ብ ሕበር፤ ሕብራት። ዐረ ሒብር) በቁሙ፤ ቀለም ስባቅ ዐለላ፤ መልክ ዐይነት፤ የቀለም ጌጥ ሽልማት፤ ልዩ ልዩነት ያለው። በዓለ ሕብር። ጥምዐተ ሕብር። ጸፍጸፍ ዘዘ ዚኣሁ ሕብሩ። ጥበብ እንተ ብዙኅ ሕብሪሃ። ሕብራት ቀይሓት ፡ (ፍ ፡ ነ ፡ ፳፫። መሳ፭ ፡ ፴። አስቴ፩ ፡ ፮። ኤፌ፫ ፡ ፲። ፈላስ ፡ ገ፲፮)።
ሕብቁቅ ፡ (ቃን ቃት ቅቅት) ያደፈ የረከሰ፤ እድፋም ነውረኛ። ሕብቁቃን ወርኩሳን። ሕብቁቃን ዲያቆናት። ሕብቅቅት ፡ (፪ጴጥ ፡ ፪ ፡ ፲፫። ሄርማ)።
ሕብቃቄ ፡ ማደፍ፤ እድፍ ርኩስ፤ ነውር ገመና። ዘእንበለ ሕብቃቄ። ንዝህላል ወፍርዛዜ፤ ሕብቃቄ ወዛውዕ ፡ (ያዕ፩ ፡ ፳፯። አንቀ ፡ ንስ)።
ሕብጠት ፡ በቁሙ ዕብጠት፤ ማበጥ አስተባበጥ ፡ (ፈ ፡ መ ፡ ፫ ፡ ፫)።
ሕቱት ፡ (ታን ታት ትት) የተመረመረ፤ የተፈተነ፤ ዕውቅ።
ሕኑጽ ፡ (ጻን ጻት ንጽት) የታነጠ የተሠራ፤ ጥርብ ዝግጁ። አህጉር እለ ሕኑጻት አረፋቲሆን። ጥቅም ዘሕንጽት በእብነ በረድ ፡ (፪ዜና ፡ ፳፩ ፡ ፫። ሔኖ፲፬ ፡ ፱)።
ሕናግ ፡ (ትግሬ) ትናግ፤ ትናጋ ላንቃ። ሒክን እይ።
ሕንቁቅ ፡ (ቃን ቃት ቅቅት) ኵሩ፤ ድልድል ቅምጥል፤ ብስክስክ እንቅብር። ፡ (ተረት፤ ትግራይ) ሕንቅቅት መርዓቲ እንተ ሰዐምዋ ትበኪ።
ሕንቃቄ ፡ (ቅያት) ክፉ ዐመል፤ ኵራት፤ መደላደል መቀማጠል፤ መቅለጥ መቅበጥ መቅበጥበጥ፤ ተድላ ሥጋንና ምግበ ሥጋን ብቻ መውደድ። እየነን እይ፤ የዚህ ጎር ነው። ኢይኩን ላዕሌክሙ ነውር እኩይ ወሕንቃቄ፤ አፍቅሮተ ተድላ ወመባልዕት ከመ ይስሐብክሙ ፍትወተ ከንቱ። ንኅድግ ሥላቀ ወሕንቃቄ። ማዕርገ ሕንቃቄ። ወይኅድግ ሕንቃቅያተ ፡ (መቃ ፡ ገ፳፬። አፈ ፡ ተ፳፬። ማር ፡ ይሥ፩ ፡ ፲፩)።
ሕንቅርት ፡ (ጽር ኾኔፍቲሪዮን) ከውር፤ ያንጥረኛ አጐዶ፤ ታናሽ ጉድጓድ የክሰል ምድጃ። ሕ ባዕድ ኹኖ አለቦታው ገብቷል፤ ነቈረን እይ። ደዮ ውስተ ሕንቅርት ፡ (ዘካ፲፩ ፡ ፲፫)። ዕብራይስጡ ግን ፡ (ሀሽሊኬሁ ኤል ሀዮጼር) ግድፎ ኀበ ለሓኵ ይላል፤ የፈጣሪን ቦታ መቅደስንና ዐጸደ ለብሓዊን ባንድነት ያሳያል። ፪ኛ ደግሞ በለሓኵ ፈንታ ፡ (ሀኦጻር ብሎ) መዝገብ፤ ቤተ መዛግብት፤ ግምጃ ቤት ሙዳየ ምጽዋት ይላል እንጂ | አንጥረኛንና ከውርን አያሳይም ፡ (ማቴ፳፯ ፡ ፫–፯)። ሀዮጼር ያለውን ሀኦጻር ማለት ፥ ዮድና አሌፍ ይዋረሳሉና፤ ስለዚህ ነው።
ሕንቡብ ፡ ያፈራ ፍሬያም ፍሬያማ። ያበጠ፤ ያፈረጠመ ፡ (ሲኖዶ)።
ሕንባል ፡ (ላት። ዐረ ሐንበል) ኮረቻ ምቹ ድብዳብ፤ መደላድል። የዳባ ቀሚስ የነት በርኖስ፤ የቈርበት ልብስ፤ ዐጥፍ ግላስ። ሕንባላተ ገመል። ኵሉ ሕንባላት ዘላዕሌሁ ነበረ ፡ (ዘፍ፴፩ ፡ ፴፬። ዘሌ፲፭ ፡ ፱)።
ሕንባብ ፡ ሕንባብ፤ ፡ (ባት። ዐረ ሐብ፤ ዔናብ) የንጨት ፍሬ ሥጋማ፤ እንደ ወይን እንደ ዘይት እንደ ተምር ያለ፤ አጋምን እንዦሪን ቀጋን የመሰለ ክብ እንክብል፤ ለፈሳሽም ቅንጣት ይነገራል። ሕንባበ ፍሬሃ። ኢትትቀረም ሕንባባተ ወይንከ ዘወድቀ። ሕንባባት እምውስተ አስካል። ሕንባባተ ዘይት ከልኤቲ። ሕንባባተ ሮማን። ሕንባበ ማይ። ሕገባባተ ነጠብጣብ። ሕንባባተ በረድ ፡ (አርጋ። ዘሌ፲፱ ፡ ፲። ሱቱ ፡ ዕዝ፱ ፡ ፳፬። ኢሳ፲፯ ፡ ፮። ስንክ ፡ ጥር፲፫። ቅዳ ፡ ግሩ። ኢዮ፴፰ ፡ ፳፰። ሄርማ)።
ሕንብርብሬ ፡ (ሕበር፤ ሓበረ። ዕብ ሐባርቡሮት) ለምጥ ቋቍሻ፤ ድል፤ ቡሬነት ዝንጕርጕርነት። ብርህት ወጸዐድዒድ ሕንብራ ይእቲ። ወዘሕንብርብሬኒ። የኀድግኑ ነምር ሕንብርብሬሁ ፡ (ዘሌ፲፫ ፡ ፴፱። ፲፬ ፡ ፶፮። ኤር፲፫ ፡ ፳፫)። በነቢር ዘይቤ ሲፈቱት ግን፤ ብጕር ዕትራት ኪንታሮት ጢ ያሰኛል።
ሕንብርት ፡ (ነበረ፤ ንብርት) በቁሙ ዕንብርት የሆድ መካክል የዕትብት ሥር መብቀያው። ሰላም ለሕንብርትከ ማእከለ ጠባይዕ ዘተመልአከ። ማእከለ ከርሥ ሀላዊ። ሕንብርተ ከርሡ ፡ (ደራሲ። ኢዮ፵ ፡ ፲፩)።
፡ አንዠት፤ የሆድ ውስጥ፤ ማሕፀን። ኅቡረ ወፃእነ እምሕንብርትኪ ፡ (ኩፋ ፡ ፴፭)።
፡ የምድር ጕብር፤ ተራራ ኰረብታ ገመገም። ደብረ ጽዮን ማእከለ ሕንብርታ ለምድር። ናሁ ሕዝብ ይወርድ እምኀበ ሕንብርተ ምድር። እለ ይነብሩ ውስተ ሕንብርተ ምድር ፡ (ኩፋ ፡ ፰። መሳ፱ ፡ ፴፰። ሕዝ፴፰ ፡ ፲፪)።
ሕንከት ፡ ማፈር፤ መቍረጥ ቈረጣ። ዝንቱ ፍና ፈውስ ውእቱ ወአኮ ሕንከት ፡ (ተረ ፡ ቄር፩)።
ሕንካ ፡ (ዕብ ሐኑካ) ቅዳሴ ቡራኬ ያዲስ ቤት ምረቃ፤ የታቦት የመቅደስ የቤተ ክሲያን ዕቃ መሾምና መክበር የግዜር ገንዘብ መኾን። በዓለ ሕንካ ፡ (ዮሴፍ)።
ሕንካሴ ፡ ማንከስ፤ መጠራጠር። ጥርጥር፤ ጥርጠራ። ከመ ይሕየው ሕንካሴክሙ ፡ (ዕብ፲፪ ፡ ፲፻)።
ሕንክ ፡ (ነባርና ትእዛዝ አንቀጽ) ዕንካ ውሰድ ተቀበል። ሕንክሙ ብልዑ ፡ (ማቴ፳፮ ፡ ፳፮)።
፡ ስጥ ዐድል፤ ዕንካችኹ በል። ሀብን እይ፤ የዚህ ጎር ነው።
ሕንክስና ፡ ዐንካስነት፤ ተጠራጣሪነት። ሕንክስናሆሙ። ፡ (፪ነገ ፡ ፳፪ ፡ ፵፮)።
ሕንጸት ፡ ማነጥ መታነጥ፤ አስተናነጥ፤ ሕንጻ። ዕንጨት ማለት ከዚህ የወጣ ነው። ቀዳሚት ሕንጸታ ለእየሩሳሌም። ሥዩማን ላዕለ ግብረ ሕንጸት። በመዋዕሊሁ ተፈጸመ ሕንጸታ ለቤት። እምጊዜ ሕንጸተ ቤት ዳግማይ ፡ (ቀሌ። ስንክ ፡ መስ፲፮። ዮሴፍ)።
ሕንጻ ፡ (ጻት) የቤት የዋሻ ሥራ መልክና ቅርጥ ያለው፤ ቤት ግንብ ዋሻ። ውሉድ ወሕንጻ ሀገር ያዐብዩ ስመ። ሕንጻሁ ለምኵራብ። አኮ ለሰብእ ዛቲ ሕንጻ ዘእንበለ ለእግዚ። አንትሙ ሕንጻ እግዚ። አዳም ሕንጻ ላሊበላ ኢይብላዕ እምዕፅ ፡ (ሢራ፵ ፡ ፲፱። ማቴ፳፬ ፡ ፩። ፩ዜና ፡ ፳፱ ፡ ፩። ፩ቆሮ ፡ ፫ ፡ ፬። ቅኔ)። ድሕንጻን እይ፤ የዚህ ዘር ነው።
ኅንጻጽ ፡ (ጻት) ጥርጣሪ፤ እንጥርጣሪ ንፋሽ ገለባ ልቃሚ ብጣሪ። ኑፋቄና ኅንጻጽ ባማርኛ ይተባበራሉ። ፡ (ግጥም፤ አቶ ሰይፉ ከድተዋል ተብለው ከታሙ በኋላ በፍቅር መጥተው ሲገናኙ) አለጊዜው ጊዜ ማን እሸት አምጥቷል፤ በዚህ በቤታችኹ ጥርጣሪ መልቷል። የእሳት ፍንጣሪ፤ የምጣድ ብልጭልጭታ። ቀለምጺጸን እይ።
ሕንጼ ፡ ዝኒ ከማሁ፤ ሕንጻ ሕንጸት። ሕንጼሃ ወሡራሬሃ አዳም። አመ ሕንጼሃ ለኢየሩሳሌም ፡ (ድጓ። ስንክ ፡ ኀዳ፳፮)።
ሕንጽዋል ፡ ጌንጭ ገረማ ሲናር፤ ዐረማሞ፤ ክፉ ዐረም። ህየንተ ሥርናይ ክርዳድ፤ ወህየንተ ሰገም ሕንጽዋል ፡ (ኢዮ፴፩ ፡ ፵)።
ሕንፉጽ ፡ የተነፈሰ፤ የተንዘረዛረ። ዕንፉጭ ግርድ ንፋሽ፤ ብጣሪ።
ሕከክ ፡ በቁሙ፤ ዕከክ የገላ የቈበርት ደዌ። በአበቅ እኩይ ወበሕከክ ዘአልቦ ፈውስ ፡ (ዘዳ፳፰ ፡ ፳፯)።
ሕኩክ ፡ (ካን ካት ክክት) የታከከ። ያከከ፤ ዕከክ የወረሰው።
ሕዋስ ፡ (ሳት። ዐረ ሐስ። ዕብ ሑሽ። ሱር ሓሽ)። በቁሙ፤ ገላ አባል፤ ኅሊና፤ የአፍኣ የውስጥ የሥጋ የነፍስ መሣሪያ የሚላወስ የሚንቀሳቀስ፤ ይልቁንም ዐይንና ዦሮ አፍና አፍንጫ እጅ። ዳግመኛም በነዚህ ባምስቱ የሚሠራ ፭ቱ ዐይነት ሥራ፤ ማየትና መስማት መቅመስና ማሽተት መዳሰስ፤ በቋንቋ ኹሉ ፭ ሕዋስ ይባላል። ሕዋሳትሰ ዐሠርቱ እሙንቱ፤ ኀመስቱ ዘአፋኣ ወኀምስቱ ዘውስጥ። ወሕዋሳጸ ዘውስጥ እሙንቱኬ፤ ልቡና ወአእምሮ ወፈሊጠ እኩይ እምሠናይ ፥ ወለብዎ ፥ ወተገሥጾ። ወሕዋሳትሂ እለ ያስተርእዩ እሙንቱኬ፤ ሰሚዕ ወርእይ ወአጼንዎ ወጥዒም ወገሲስ ፡ (ፈላስ ፡ ገ፶፫)። በግእዝ ልማድ ግን እሊህን ዐሥሩን የሕዋሳት ግብር ማለት እንጂ ሕዋሳት ማለት አይመችም፤ ጸያፍ ይኾናል፤ ሕዋስ የሚባል መሣሪያው ብቻ ነው። በነዚህ ባ፭ቱ ላይ ድግሞ እግርና አባለ ዘር ሲጨመሩ ሕዋሳተ አፍኣ ይባላሉ።
ሕዋር ፡ (ራት) በረንዳ ወልወል ደጀ ሰላም፤ መውጫ መግቢያ መመላለሻ፤ በታላቅ ቤትና በቤተ ክሲያን ደጅ አፍ ወይም በዙሪያው ገጥሞ ተያይዞ የሚሠራ፤ ዐልፎ ዐልፎ ዐምድ የቆመበት ከበታቹ ዕርከኖች ያሉት፤ ዕርከን ተረግጦ የሚገቡት። ኤላምን እይ። አንሶሰወ በሕዋረ ሰሎሞን። ወባቲ ኀምስቱ ሕዋራት ፡ (ዮሐ፲ ፡ ፳፫። ፭ ፡ ፪። ግብ፫ ፡ ፲፩)።
፡ ዕቃ ቤት፤ ጓዳ ታዛይ በቤት ዙሪያ ወይም ግራና ቀኝ ከቤቱ ጋራ ዐብሮ የሚናስ የሚነደቅ፤ በላይ አንድ ኹኖ በውስጥ የተለየ ታናሽ ጠባብ ክፍል ዕልፍኝ። ኤስኬዴሬን እይ፤ ከዚህ ጋራ አንድ ነው። ለትኩን እንከ ቤተ ክርስቲያን ኑኃ መንገለ ምሥራቅ፤ ወክልኤ ሕዋራት ውስተ ገበዋቲሃ በአምሳለ ሐመር። ሕዋር ማእከላዊ። ወናሁ ሕዋራት ፡ (ዲድ ፡ ፲፪። ስንክ ፡ መጋ፲፫። ሕዝ፵ ፡ ፲፯)።
ሕዋይ ሐዋይ ፡ ምሼት ደግዝታ ጭልምልምታ፤ የሠርክ ሠርክ የማታ ማታ። እምከመ መስየ ወኮነ ሕዋየ ፡ (ማቴ፲፮ ፡ ፪)።
ሕዋጼ ፡ (ጽያት) መጐብኘት ፡ (ጥጐ) መጐብኘት፤ አጐብኛኘት ጕብኘታ ጥየቃ፤ ስለላ ጥበታ ፡ (ጥበ፫ ፡ ፯ ፡ ፱)። ዚኣከ ጥበበ ወዘዚኣከ ሕዋጼ። ሐውጽዎሙ በሕዋጼ እግዚአብሔራዊት ፡ (ኪዳ። ፍ ፡ ነ ፡ ፮)።
ሕዉል ፡ (ላን ላት ውልት) የተቀላቀለ ቅልቅል፤ ኅቡር ፡ (ስንክ ፡ ሠኔ፳፫። ጥር፳፯)።
ሕዉስ ፡ (ሳን ሳት ውስት) የተላወሰ የተንቀሳቀሰ፤ የተነቃነቀ ንቅንቅ።
ሕዉር ፡ (ራን ራት ውርት) የኼደ፤ የተኼደ የተኼደበት፤ የተካኺያደ። የተሠራ የተደረገ፤ ግቡር ሕኑጽ።
ሕዉጽ ፡ (ጻን ጻት ውጽት) የተጐበኘ የተሰለለ፤ ጕብኙ።
ሕዙል ፡ (ላን ላት ዝልት) የታዘለ፤ ዕዝል ቅጥል። ሕዙላን በክነፊሁ ፡ (ገድ ፡ ተክ)።
ሕዙብ ፡ (ባን ባት ዝብት) የታዘበ፤ የተሰበሰበ፤ የታሰበ የተጠረጠረ። ወዕለታኒ ሕዝብት እኪት ፡ (ኢሳ፳፰ ፡ ፲፱)።
ሕዙን ፡ (ናን ናት ዝንት) ያዘነ የተቈረቈረ፤ የከፋው ሐዘንተኛ። ብእሲ ሕዙን። ልብ ሕዙን። ኵሉ ሕዙነ መንፈስ። ሕዙን ገጽክሙ። ሕዙናን በእንቲኣሁ ፡ (ሢራ፯ ፡ ፲፩። ዘዳ፳፰ ፡ ፷፭። ፩ነገ ፡ ፳፪ ፡ ፪። ዘፍ፵ ፡ ፯። ግንዘ)።
ሕዝል ፤ ዕዝል ፤ የዜማ ስም ፤ የግእዝ ድርብና ታዛይ ኹለተኛ። ዕዝልን እይ ፤ ሊጣፍ የሚገባው በሕ ነበረ ፤ ሐና ዐ ተወራራሾች ስለ ኾኑ ሕ በዕ ተለውጧል ፤ ይህን የመሰለ ብዙ ቃል አለ።
ሕዝባዊ ፡ (ዊት ውያን ያት) በቁሙ፤ የሕዝብ ወገን፤ ካህን ያይዶለ ማይምን፤ ጨዋ ባላገር። በእንተ ተግሣጽ ወትእዛዘ ሕዝባውያን። ወለእመ ኮነ ሕዝባዌ ፡ (ፍ ፡ ነ ፡ ፲፩። ፲፪። ዲድ። ኪዳ። ቀሌ)።
ሕዝብ ፡ (ብ ሕዘብ፤ አሕዛብ) በቁሙ፤ ወገን ነገድ፤ የተሰበሰበ ብዙ ሰው፤ ጉባኤ ሸንጎ፤ ልቅሶኛ ሰርገኛ ገበያተኛ። ያንዲት አገር ያንዲት ከተማ ወይም ያንድ ብሔር ያንድ መንግሥት ሰው፤ ቋንቋውና ሕጉ አንድ የኾነ፤ ባንድ ሕግ የሚኖር። ውስጠ ብዙነት ስላለው ባንድም በብዙም በወንድም በሴትም ይነገራል። ሕዝብ ዐቢይ። ዝ ሕዝብ አብድ ወአኮ ጠቢብ። ሕዝብ ጽንዕት። ከመ ትፃእ ዮም አሐቲ ሕዝብ እምእስራኤል። ሕዝብ ነኪራን ወእኩያን ፡ (ዘፍ፲፪ ፡ ፪። ዘዳ፴፪ ፡ ፮። ሚክ፬ ፡ ፯። መሳ፳፩ ፡ ፫። ኢሳ፲፰ ፡ ፪)። ስሕቱ ግብጽ በበ ሕዘቢሆሙ። ሕትቶሙ ለአበው በበ ሕዘቢሆሙ። ተደሙ ሰብኡ ወሕዘቢሁ አንከሩ። ለምንት አንገለጉ አሕዛብ። ይገኙ ለከ አሕዛብ እግዚኦ። አግረረ ለነ አሕዛበ ወሕዝበ ታሕተ እገሪነ ፡ (ኢሳ፲፱ ፡ ፲፫። ኢዮ፰ ፡ ፰። ስንክ ፡ ታኅ፲። መዝ ፡ ፪። ፵፬። ፵፮)።
ሕዝብና ሕዝበት ፡ ሕዝብነት ወገንነት፤ ሕዝብ መኾን። እስመ ተኀድገ ሕዝብናከ ፡ (ተረስዐ ሕዝበትከ) እስራኤል ፡ (ኢሳ፪ ፡ ፮)። ዕብራይስጡ ግን ፡ (ኪ ናጣሽታ ዐምኻ ቤት ያዕቆብ) እስመ ገደፍከ ሕዝበከ ቤተ ያዕቆብ ይላል።
ሕዝእ ፡ (ኣት፤ አው ሕዝአት፤ ታት) መሰምሪያ ማሰምሪያ፤ ማደሪያ በረት ምሳግ፤ ዋሻ ጐሬ። በኵሉ ፍኖት መጽያሕት ሕዝአቶሙ ወይከውን ሕዝአቶሙ ህየ። ዕጐልት በውስተ ሕዝአቶሙ ጠፍአ። ዕርግ እምሕዝአትከ። ተኀብኡ ሕዝብ ውስተ በኣታት ወውስተ ሕዝአታት ፡ (ኢሳ፵፱ ፡ ፱። ሕዝ፴፬ ፡ ፲፬። ዮኤ፩ ፡ ፲፯። ዘፍ፵፱ ፡ ፱። ፩ነገ ፡ ፲፫ ፡ ፮)።
፡ መግቢያ በር፤ ወሰን ደንበር፤ ርስት ጕልት። ወለምድረ ናምሩድ በውስተ ሕዝአቱ። ወሖሩ ካም ወውሉዱ ውስተ ምድር እንተ ሕዝአት ሎቱ ዘረከቦ በመክፈልቱ ፡ (ሚክ፭ ፡ ፮። ኩፋ ፡ ፲)።
ሕየብ አብው ሕበይ ፡ (ዕብ ሖቢት፤ በርሚል። ሱር ሓቢታ። ዐረ ኀቢየት፤ ኂባእ) የሸክላ ዕቃ፤ ቡይት መንቀል ኵስኵስት የዘይት ገንቦ ማድጋ ፊቀን ዝንግሪር ጋን፤ ሆደ ሰፊ አፈ ጠባብ።ርእሰ ሕበይ ስሳ ምእት ዐሠርቱ ወኀምስቱ፤ ወመሥረበ ማይሂ ተስዓ ወአሐዱ ፡ (ታሪ ፡ አኵ)።
ሕዩስ ፡ (ሳን ሳት ይስት) የተነቀፈ የተነቃቀፈ፤ ንቁፍ፤ ስዱብ ነውረኛ።
ሕያው ፡ (ውት ዋን ዋት) በቁሙ፤ ነዋሪ ደኅና ባለጤና፤ ነፍስና ደመ ነፍስ እስትንፋስ ያለው ተንቀሳቃሽ ፍጥረት ገና ያልሞተ በሕይወት ያለ። ኵሉ ዘሕያው። ሕያውኑ ዓዲሁ አቡነ ፡ (ሢራ፲፮ ፡ ፴። ዘፍ፵፭ ፡ ፫)። ጭራሽ ለባሕርዩ ሕማም ሞት ኅልፈት ጥፋት መለወጥ ማርጀት የማይሰማማው። ቅዱስ ሕያው ዘኢይመውት። መልአክ ዘሕያው። ነፍስ ሕያውት ፡ (አዋል)። ሕያዋነ ሕይወት ዘለዓለም ዘኢይመውት ፡ (ሔኖ፲፭ ፡ ፬ ፡ ፮)።
፡ መሐላ፤ ቃለ መሐላ። ሕያው እግዚ ከመ አነ እትሐመወኪ። ሕያው አነ ከመ ትሰረገዊዮሙ። ሕያው ነፍስከ ከመ ኢትወድእ አመትከ ፡ (ሩት ፡ ፲፫። ኢሳ፵፱ ፡ ፲፰። ዮዲ፲፪ ፡ ፬)። ሕያዉ ሕያዎ ሕያወ በሕያው እያለ ደቂቅ ይኾናል። ዕጓለ መሕያው፤ ሕያው ከመሬት ያስገኘው መዋቲ ሰው አዳም፤ ዕጓልን እይ።
ሕያውና ፡ ሕያውነት፤ ሕያው ደኅና ባለጤና መኾን። እንዘ ሀሎከ አንተ በሕያውናከ ዝየ ፡ (አዋል)።
ሕይወት ሒወት ፡ (ታት) መዳን፤ መኖር። በቁሙ፤ደኅንነት፤ አናዎር ኑሮ፤ ዘመን ዕድሜ፤ ተወልዶ እስኪሞቱ ተሹሞ እስኪሻሩ የሚኖሩት። ሕይወት እንተ አልባቲ ሞት።ይኄይስ መዊት አመራር ሕይወት። ጸላእኩ ሕይወትየ ምስለ አዋልደ ከነዓን። እሴብሖ ለእግዚ በሕይወትየ ፡ (ሱቱ ፡ ዕዝ፭ ፡ ፲፫። ሢራ፴ ፡ ፲፯። ዘፍ፳፯ ፡ ፵፮። መዝ ፡ ፻፵፭)።
፡ ትንሣኤ፤ ተሐድሶ ጤና፤ ምስጢሩ ደኅንነት ካለው ይገባል። ዛቲ ይእቲ ቀዳሚት ሕይወት። ሕይወተ ሙታን። ፡ (ራእ፳ ፡ ፭። ግብ፲፯ ፡ ፴፪። ዮዲ፲፩ ፡ ፫)።
፡ ገንዘብ ጥሪት። ይእቲ አብአት ኵሎ ሕይወታ ወካልኣንሰ እምተረፎሙ ፡ (ፍ ፡ ነ ፡ ፲፮)።
፡ መሐላ፤ ቃለ መሐላ፤ ምጥንታ። ሕይወተ ፈርዖን ከመ ኢትወፅኡ። ሕይወተ ነፍስከ ከመ አነ ይእቲ ፡ (ዘፍ፵፪ ፡ ፲፭ ፡ ፲፮። ፫ነገ ፡ ፩ ፡ ፳፮)።
ሕዳሴ ፡ ማደስ መታደስ፤ አስተዳደስ ዕደሳ፤ ሐዲስነት።
ሕገ ፡ (ዐቢይና ደቂቅ አገባብ) እንደ። ሕገ ጾመ ሙሴ ተመጣዌ ሕግ፤ ጾመ ኢየሱስኒ ሠራዔ ሕግ ፡ (ዘረፋ)። ኢተአምሩኒ ሕገ ንነግረክሙ፤ እንድንነግራችኹ። ደቂቅ ሲኾን ሕገ ሰብእ እነብብ። ሕገ ሰብእ እብለክሙ። ሕገ ሰብእ አናሕሲ ለነ እያለ በብትን ይገባል። ፡ (ሮሜ፫ ፡ ፭። ፮ ፡ ፱። ሊጦን)። ፡ (ዕር፲፱ ፡ ቍ፸፭)።
ሕገ ሥጋ ፡ ልማድ ፈቃድ፤ ግዳጅ። ይፌጽም ሕገ ሥጋ ፡ (ስንክ ፡ ነሐ፲፬)።
ሕገ ጠባይዕ ፡ (434) ባሕርያዊ ሕግ፤ ፍጡር ኹሉ በባሕርዩ ዐውቆ የሚሠራው፤ መውለድ መዋለድ፤ በየጥቂቱ ማደግ፤ መራብ መጠማት ምግብ መሻት፤ የመሰለው ኹሉ ፡ (አፈ ፡ ድ፳፯። ሮሜ፪ ፡ ፲፭)።
ሕጕሬ ፡ (ዐረ ሐጀሪ፤ እብናዊ) ቀይ ቀለም፤ ወርቅማ እንደ ኵል ደንጊያነት ያለው፤ ሳይደቈስ ወርቅ የሚመስል፤ ቅላቱ ፍጹም ደማቅ። ወቀብዖ በሕጕሬ ወሤረዮ ወአቅየሐይሐ ሕብሮ ፡ (ጥበ፲፫ ፡ ፲፬)።
ሕጕር ፡ (ራት) የፍሬ ፍሬ፤ በወይንና በተምር ሕንባብ ውስጥ የሚገኝ ቅንጣት፤ ውስጡ ዐጥንቱ ከራራው ጠንካራው እንዳሸዋና እንደ ጠጠር ያለው። ዘእምውስተ ዘቢብ ሕጕር ፡ (ዘኍ፮ ፡ ፬)። ባለብሉዮች ግን፤ ንባቡን ሕጉር ይሉና ፍችውን የተነጐረ ይሉታል።
ሕጉግ ፡ (ጋን ጋት ግግት) የታገገ የተደነገገ፤ ውሱን ሥሩዕ ጽሑፍ።
ሕጋዊ ፡ (ዊት ውያን ያት) በቁሙ፤ የሕግ፤ ባለሕግ፤ ሕግ የሚጠብቅ በሕግ የተጋባ። ሰብሳብ ሕጋዊ። ብእሲት ሕጋዊት ፡ (ፈ ፡ መ ፡ ፰ ፡ ፩። ፍ ፡ ነ ፡ ፳፬ ፡ ፩)።
ሕግ ፡ (ብ ሕገግ፤ ጋት) በቁሙ፤ የተወሰነ የተጣፈ ሥርዐት፤ እውነተኛ ፍርድ፤ ያገር ልማድ ለማድረግ የሚያዝ ከማድረግ የሚከለከል፤ አድርጉ አታድርጉ የሚል። ዐሠርቱ ቃላተ ኦሪት ስድስቱ ቃላተ ወንጌል ፡ (ዘዳ፮ ፡ ፭። ዘፀ፳ ፡ ፩–፲፯። ዘሌ፲፱ ፡ ፲፰። ማቴ፭ ፡ ፳፩–፵፰)። ከነዚያውም ሕግ የሚባለው አታድርግ አታድርግ የሚለው ነው፤ አድርግ የሚለው ግን ትእዛዝ ይባላል። ሰሌዳተ እብን ዘሕግ ወዘትእዛዝ። ሕገገ ኦሪት። ክልኤቱ ሕገጋት። ዘየአምር ሕገጋተ ምኔት ፡ (ዘፀ፳፬ ፡ ፲፪። ሮሜ፪ ፡ ፳፩። ፈ ፡ መ ፡ ፪ ፡ ፮። ፍ ፡ ነ ፡ ፲)።
ሕጥሜ ፡ ሥንቆ፤–ኅጥሜ።
ሕጸት [1] ፡ ማነስ መጕደል፤ አጐዳደል ጐደሎነት፤ ጕድለት። ዘእንበለ ተውሳክ ወኢሕጸት። አልቦ ላዕለ እግዚ ተወስኮ ወኢሕጸት። ሕጸተ አእምሮ አግዚ። ሕጸተ ሃይማኖት። በእንተ ሕጸተ ምክሮን ለአንስት ፡ (ዮሴፍ። ቀሌ። ጥበ፲፫ ፡ ፩። ኪዳ። ዮሴፍ)።
[2] ፡ መጕደል፤–ሐጺጽ ሐጸ።
ሕጸጽ ፡ በቁሙ፤ ጕዳይ ጕዴለት፤ ቅሬታ ቅሪት፤ እንከን፤ ስሓ፤ ጸያፍ። በሕጸጸ ወርኅ። እፌጽም ሕጸጸ ሕማሙ። ሕጸጸ ነፍስ ይትወለድ እምሕጸጸ አሚን። እንከሰ ሕጸጽ ውስተ ማዕርገ ክህነት ፡ (ሔኖ፸፰ ፡ ፰። ቆላ፩ ፡ ፳፬። አፈ ፡ ድ፲፬። ፲፫።
ሕጹር ፡ (ራን ራት ጽርት) የታጠረ የተቀጠረ፤ የተከበበ። ሕጹር በጽጌ። ሀገር ሕጽርት ፡ (ማሕ፯ ፡ ፫። ኢሳ፩ ፡ ፰)።
ሕፁን ፡ (ናን ናት ፅንት) ያደሀ የጠባ፤ የታቀፈ በክንድ የተያዘ።
ሕፁይ ፡ (ያን ያት ፂት) የታጨ፤ የተጫጨ፤ ባለጮኛ። ድንግል እንተ ይእቲ ሕፂት፤ አው ተፍኅረት ለብእሲ ፡ (ፈ ፡ መ ፡ ፮ ፡ ፰)።
ሕጹጻን ፡ የመጽሐፍ ስም፤ ዜና መዋዕል። ትራፋት ነገሥት ማለት ነው፤ በነገሥት የሌሉ ከነገሥት የቀሩ ጥቃቅን ቃሎች ታናናሽ ታሪኮች ስላሉበት፤ ስሙ ሕጹጻን ተብሏል፤ ይኸውም ፪ ክፍል ነው። ወክልኤቱ ሕጹጻን። ሕጹጻን ቀዳማዊ። ካልእ ፡ (ፍ ፡ ነ ፡ ፪። ዜና ፡ ፩። ፪)።
ሕጹጽ ፡ (ጻን ጻት ጽጽት። ዕብ ሐጺ፤ እኩሌታ) ያነሰ የጐደለ፤ ታናሽ ጐደሎ፤ ደካማ ምኑን። ሕጹጽ አነ እምነ ዕደው ጻድቃን። ኩኑ ፍጹማነ ወአኮ ሕጹጻነ። ብእሲት ሕጽጽት እምፍጥረተ አንስት። አርባዕቱ ሕጹጻን ውስተ ምድር ፡ (ማር ፡ ይሥ፴፭። ግንዘ። ፍ ፡ ነ ፡ ፳፬ ፡ ፯። ምሳ፳፬ ፡ ፶፱)።
ሕፃን ፡ (ናት) በቁሙ፤ ዐራስ ጨቅላ፤ ጡት ያልተወ ራሱን ያልቻለ ታናሽ ለጋ ርጥብ ልጅ ወንድ፤ ሴት። ያደገውም ቢኾን እስኪባልቅ ድረስ ሕፃን ይባላል፤ ደቦል ጕብል አሽከር ብላቴና ማለት ነው። ሕፃን ጥብሉል። እለ ይእዜ ተወልዱ ሕፃናት። ሕፃን ንስቲት። ሕፃን ንኡስ። ሕፃን ውእቱ ወልደ ዐሠርቱ ወአርባዕቱ ዓመት። ወሬዛ ወሕፃን ፡ (ሉቃ፪ ፡ ፲፪። ፩ጴጥ ፡ ፪ ፡ ፪። ኢሳ፲፩ ፡ ፮ ፡ ፰። ኩፋ ፡ ፲፩። ፩ዜና ፡ ፳፱ ፡ ፩)። ሕፃንና ዕጣን ባማርኛ ይተባበራሉ፤ ፡ (ሙሾ፤ በክፋ ቀን ልጇን እንደ ድመት ዐንቃ የበላች ሆዳም፤ ቀን በወጣ ጊዜ ስትቈዝም) አላስገባም ብሎ ቢያባረኝ ወዳጄ፤ ክፋ ቀን አወጣኝ የወልድኩት ልጄ። ዝባድ ለመነገድ ከመውረድ መተማ፤ ዕጣኑ ይሻላል ለለት እራትማ። ዳግመኛ ለመውጣት በሌላ መንገድ፤ ተመልሶ ገባ ልጅ ከናቱ ሆድ። ልጅ የሚችለውን ዐዋቂ እንዳይችል፤ በኒቆዲሞስ ፊት ይመስክር ወንጌል። የልጆች ተረት፤ ምን እናት ታስጠላ ድመት።
ሕፃንና ፡ ሕፃንነት ዐፍላ ጕብዝና ልጅነት።
ሕፄ ፡ ዝኒ ከማሁ፤ ማጨት መታጨት፤ ማጫ መስጠት መቀበል። ዕድሜ ሐዘን ይከልእ እምአውስቦ፤ ወኢይከልእ እምሕፄ ወእምፍኅረት ፡ (ፍ ፡ ነ ፡ ፳፬ ፡ ፪)።
፡ ማጫ መታጫ የጋብቻ ዐረቦን፤ ወንድ ለሴት አባት የሚሰጠው ገንዘብ። ሕፄሃ ለመርዓት። እመ ፈቀደ ፈኃሪ አው ዘተፍኅረት ምንኵስና እምድኅረ ወሀበ ሕፄ ይደልዎ ለፈኃሪ ዘወሀባ ቅድመ ከመ ይንሣእ፤ ወለፍኅርቱኒ ከመ ታግብእ ዘነሥአቶ ዘእንበለ ካዕበት። ይደሉ አውስቦ ዘእንበለ ትልወት ወኢሕፄ ፡ (ፍ ፡ ነ ፡ ፳፬ ፡ ፫)። ሴትም ወደ ባሏ የምትወስደው ገንዘብ ሕፄ ይባላል፤ መዳሪያ ማለት ነው። ዘጸሐፈ ትእዛዘ የሀብ ለአዋልዲሁ ለለ አሐቲ መክፈልተ ሕፄሆን ፡ (ፍ ፡ ነ ፡ ፵፩ ፡ ፬)።
ሕፅነት ፤ ማደግ ፤ ማሳደግ ፤ እድገት አስተዳደግ። ለዝንቱ ቅዱስ ሐፀኖ ሠናየ ሕፅነተ ቴዎፍሎስ እኅወ እሙ። ዜያሤኒ ሕፅነተ ደቂቁ (ቄር ፡ ገ፪። ፍ ፡ ነ ፡ ፭)።
ሕፅን ፡ (ዕብ ሖጼን። ዐረ ሒፅን) በቁሙ፤ ማቀፊያ መታቀፊያ፤ ጭን ደረት፤ የደረትና የእጅ መካከል፤ ብብት ጐን ግብጣ እንብርቢጣ። የቀሚስ ሠላጤ በሠላጤው ላይ የሚሰፋ ኪስ ጀብ፤ ጥግ ቅርብ አጠገብ፤ የቦታ። ውስተ ሕፅነ እሞሙ። አንበሮሙ ውስተ ሕዝኑ። ደይ እዴከ ውስተ ሕፅንከ። ሕፅነ ልሳነ ባሕር ፡ (ሰቈ፪ ፡ ፲፪። ማር፲ ፡ ፲፮። ዘፀ፬ ፡ ፮ ፡ ፪። ኩፋ ፡ ፰)።
ሕፅየት ፡ ማጨት፤ መታጨት፤ መተጫጨት፤ አስተጫጨት። እለ ይመሥጡ ወለተ ሕፅየት ፡ (ሕፅይተ) አው ዘኢተሐፅየት ፡ (ፍ ፡ ነ ፡ ፵፰)።
ሕፍን ፡ ዕፍኝ ጥርኝ፤ ውስጥ እጅ ዝርጉ ጠፍጣፋው ጣቶች የሚያፍኑት የሚዘጉት፤ ላንድም ለኹለትም ይኾናል። መኑ ዘሰፈሮ ለማይ በሕፍኑ። ሠናይ ምልአ እድ በዕረፍት እምነ ክልኤ ሕፍን በዐመፃ። ምልአ ሕፍኑ። ይንሣእ ርእሶ በስመ ሥላሴ ፡ (ኢሳ፵ ፡ ፲፪። መክ፬ ፡ ፮። ዘሌ፪ ፡ ፪። ፍ ፡ ነ ፡ ፫)።
፡ የገንዘብ ስም፤ ፪ ድሪም፤ ስጢጥራን እይ። ቀርቡ እለ ክልኤ ሕፍነ ይነሥኡ ወይቤሉ ኢይሁብኑ ክልኤ ሕፍነ ፡ (ቄር። ማቴ፲፯ ፡ ፳፬)።
ሖመር [1] ፡ (ዐረ ሑመር) የዛፍ ስም፤ ፍሬው ጥቍር ጣፋጣ ሖምጣጣ። ወይም የባሕር ፉል፤ ታላላቅ ባቄላ፤ ጠንቋዮች እንደ ጠጠር እየበተኑ የሚያሟርቱበት። ተጠይሮ በአንጽፎ ሐመድ ወፍሬ ዕፅው ወሖመር ወበቀልት ወኅጠታተ ዛጐል ፡ (ፍ ፡ ነ ፡ ፵፮)። ፋወለን እይ።
[2] ፡ እንቡጥ ከነፍሬው። ሖሞረ ጽራእ፤ የጽራእ እንቡጥ የብርብራ ዐይነት፤ ወፍራም ረዣዥም ጥፍጥ፤ ሰውም እንስሳም የሚበላው፤ ፍሬው እጅግ ታናናሽ ከራራ ደረቅ። ባለሐዲሶች ግን ቃሞ ተረር ይሉታል። የጽራእን ፍች ተመልከት ፡ (ሉቃ፲፭ ፡ ፲፮)።
ሖሜር ፡ (ዕብራ) የመስፈሪያ ስም፤ የእኽል መስፈሪያ፤ ዐሥር ኢፍ የሚይዝ፤ ታላቅ ዐሥረ ፈጅ ፡ (ሕዝ፵፭ ፡ ፲፫ ፡ ፲፬። ሆሴ፫ ፡ ፪)።
ሖሠ ፡ ቀላቀለ፤–ኀዊሥ ኆሠ።
ሖሰ ፡ ቀላቀለ፤–ኀዊሥ ሖሠ ኁሠት።
ሖር [1] ፡ (ዐረ ሐውር) የሰውም ስም፤ ኸያጅ ዘዋሪ። አባ ሖር እንዲሉ።
[2]:-ብስ ነዳላ –ኀረወ ኆር።
ሖከ ፡ አወከ፤–ሀዊክ ሆከ።
ሖጻ [1] ፡ አሸዋ ድቡሽት፤–ኀዊጽ ኆጻ።
[2] ፡ አሸዋ፤–ሐጸ ኀጠ ኆጻ።
No comments:
Post a Comment