ሀ ለ ሐ መ ሠ ረ ሰ ሸ ቀ በ ተ ቸ ኀ ነ ኘ አ ከ ኸ ወ ዐ ዘ ዠ የ ደ ጀ ገ ጠ ጨ ጰ ጸ ፀ ፈ ፐ
ሀ ፡-፭ኛ ፊደል በግእዝ አልፍ ቤት በአበገደ፤ ስሙ ሆይ፤ ሀውይ። ቍጥሩ ዐምስት፤ አኃዝ ሲኾን ሀ ኀምስት ቱ ይባላል። ዕብራውያን ግን ዐምስትን መደብ አድርገው በራሱ ላይ ነቍጣ እየጨመሩ ዐምስት እልፍ ይሉታል፤ ይኸውም ኀምሳ ምእት ወይም ዐምስት ሺሕ ማለት ነው። ምስጢሩ ኀሙስንና የኀሙስን ፍጥረት መደብ አድርጎ ምስጢረ ጥምቀትን ያሳያል ፡-(ዘፍ፩ ፡-፳–፳፫)።
ሃ ፡-ዝርዝር ጠቃሽ፤ ላንዲት ለሩቅ ሴት፤ በሩቅ ሴት አንቀጽ ለሚነገር ኹሉ።
ሀ -ሃ ፡-የግእዝ ወራሽ ለሩቅ ወንድና ሴት፤ ግእዙ ለወንድ፤ ራብዑ ለሴት ትራስ እየኾነ በተጸውዖ ስም ሲገባ ፥ ን ወደ ይኾናል። ርኢ አዳምሀ ወሔዋንሃ። መጣፍ ግን በጣፎች ስሕተት ወንድና ሴት ሳይለይ ለኹሉም ራብዑን ብቻ ያንባል።ዘካርያስሃ ወኤልሳቤጥሃ። ሃሌታ ሊጣፍ የሚገባው በግእዝ ሀ ሲኾን፤ ሃሌ ተብሎ በራብዕ እንዲጣፍ ይህም እንደዚያ ነው።
ሀ -አ ፡-(ሐ ኀ ዐ) የግስ ዐመል፤ የራብዕ የሳድስ ሥረይ። የአን ፍች እይ፤ ከዚህ ጋራ አንድ ነው። ፪ኛም ፡-(ዕር፪ ፡-ቍ፲፬)።
ሀሀርኤል ፡-ምሥዋዕ፤ የምሥዋዕ ስም፤ ደብረ አምላክ ማለት ነው ፡-(ሕዝ፵፫ ፡-፲፭)። አሪኤልንና አርያልን እይ፤ ከዚህ ጋራ አንድ ነው።
ሀለወ ፡-ጠበቀ፤–ኀሊው ኀለወ።
ሀለየ ፡-ዘፈነ፤–ሐልይ ሐለየ።
ሀለደ ፡-ጨረሰ፤–ኀልዶ ኀለደ።
ሀሊል ፡-(ሀለ የሀልል ይህልል። ዕብ ሀሎል ሄል) ማወደስ ማመስገን፤ መየበብ መዝፈን።
ሀላ ፡-ሀሊባ፤–ድንኳን፤–ኦሆላ ኦሆሊባ።
ሀላዊ ፡-(ዊት ውያን ያት) የሚኖር ነዋሪ፤ ዃኝ። ነፍስሰ ሀላዊት ይእቲ ወኢትትዌለጥ ፡-(ፈላስ)።
ሃሌ ፡-(ሀሌ። ዕብ ሀሌል) ሃሌታ፤ ስብሐት ውዳሴ፤ መዝሙር ግናይ፤ ቅኔ ሐዲስ ምስጋና፤ መዘምራን ሃሌ ሃሌ ብለው የሚመሩት፤ በሃሌታ የሚዠምሩት። አንቀጽ ሃሌታ እንዲሉ። ፡-(ተረት) መዝሙር በሃሌ፤ ነገር በምሳሌ፤ ጠጅ በብርሌ። ሃሌታና እልልታ በምስጢር አንድ ነው፤ አለለን ተመልከት።
ሃሌ ሉያ ፤ (ዕብ ሀልሉ ያህ) ፤ ዕብሑ እግዚአ ፤ ሀልሉ ስብሑ
፤ ያህ እግዚእ
አምላክ
።
ወርኀ ሃሌ ሉያ (ዘፀ፲፫ ፡ ፬)
።
አቢብ ተመልከት ።
(ጥ) ሀልዎ ዎት ፡-(ሀለወ፤ ሀሎ፤ ይሄሉ የሀሉ። ዕብ ሀያህ) መኖር መገኘት፤ መኾን መፈጠር። ኮነንና መጽአን ተመ፤ የዚህ አግዋር ናቸው። እግዚአብሔር አምጻኤ ኵሉ ዓለም እምኀበ ኢሀልዎ ኀበ ሀለዎ። ሀለወ ወኢሀለወ። ዘሀሎ ወይሄሉ። ወሀሎ አሐዱ ብእሲ፤ አለ ኖረ ነበረ ፡-(ፈላስ። ራእ፲፯ ፡-፰። ፩ ፡-፬። የሐ፫ ፡-፩)።
ሀሙዒዳ ፡-(ዕብ ሀሞዔድ) ዕድሜ የተወሰነ ጊዜ ወራት፤ የበዓል የቀጠሮ ቀን። ሄዔኪር ሀሙዒዳ ፡-(ኤር፵፮ ፡-፲፯)። ባለብሉዮች ግን ሰባራ ምቱረ ሥርው ፈሪ ይሉታል።
ሀሴቦን ፡-(ጽር ሄሴቦን) ውስጠ በውስጥ፤ ውሳጣዊ። ኵሉ ክብራ ለወለተ ንጉሥ ሀሴቦን ፡-(መዝ ፡-፵፬)።
ሀረመ ፡-ተወ፤–ሐሪም ሐረመ።
ሀርበደ ፡-(አብደ። ዐረ ዐርበደ፤ ከፋ ክፉ ኾነ) አረበደ፤ ቸኰለ። ተቈጣ እብድ እብድ አለ። ደነገጠ ደነበረ፤ ወገሸ አገረገረ፤ ሸሸ ሮጠ ፈረጠጠ፤ የከብት። ከመ ዕጐልት እንተ ተሀረብድ ሀርበደ ኤፍሬም ፡-(ሆሴ፬ ፡-፲፮)
፡-ተቀናጣ፤ ተቀማጠለ፤ ሰው ልፍጅ አለ፤ የዘመናይ። ወለእመ ቀተለ በሀርብዶ ኢይከውን ኵነኔሁ ከመ ኵነኔ አብዳን ፡-(ፍ ፡-ነ ፡-፵፯)። አንዳንድ መጣፍ በተሀርብዶ ይላል ስሕተት ነው።
ሀበየ ፡-ሾመ ጠበቀ፤–ሐብይ ሐበየ።
ሀቢብ ፡-ወዳጅ፤–ሐቢብ ሐበ፤ ሐበበ ሐቢብ።
ሀቢብ ቦት ፡-(ሀበ፤ ሀበበ የሀብብ ይህብብ። ዐረ፤ ሰበ) ሀብ ሀብ ማለት፤ መስደብ መንቀፍ፤ ማቃለል። መጽሐፍ ግን በሀበበ ፈንታ ተሀበበ ይላል፤ ስሕተት ነው። ይትሀበቡኒ ወይዘነጕጐኒ። ኢትትሀበቦ ለዘይትጋነይ። በማእከለ ቢጹ ይትሀበብዎ ለምታ ፡-(ኤር፳ ፡-፰። ሢራ፰ ፡-፭። ፳፭ ፡-፲፰)።
ሀቢው ዎት ፡-(ሀበወ የሀቡ ይህቡ። ወሀበ፤ ሐበበ) መወጨፍ መዝነብ፤ መንፈስ መተገብ። ዝናምና ጠል መስጠት ማጥገብ፤ ወሀበንና ሐበበን እይ፤ የዚህ ጎሮች ናቸው።
ሀባቢ ፡-መሀበቢ፤ መህብብ፤ መስተሀብብ፤ ፡-(ብት ባን ባት) የሚሳደብ ተሳዳቢ፤ ነቃፊ አቃላይ፤ ሀብ ሀብ ባይ። ኢይኩኑ ነባብያነ ወተናጋርያነ ፅሩዕ ወመስተሀብባነ ፡-(ኪዳ። ሮሜ፩ ፡-፴)።
ሀብ [1]፡-፣–በል ስጥ፤–ውሂብ ወሀበ ይውህብ የሀብ።
[2]፡-»ሀብ፤ ፡-(ቡ ቢ ባ) ንኡስ አገባብ) ትእዛዝ አንቀጽ፤ ፡-(ወሀብከ ትውህብ) ስጥ ዐድል አሳልፍ፤ አምጣ። እስኪ፤ ና፤ በል። ሀቡ ንበል። ሀቡ ንረድ። ሀቡኬ ንግባእ። ሀብኬ ንትኃሠሥ በአይ ፍኖት ተወልደ። ሀባ ናመክሮን፤ ሀባ ንፍትኖን ፡-(ዕዝ፫ ፡-፭። ፬ነገ ፡-፭። ፬ነገ ፡-፫ ፡-፳፫። ቄር ፡-ጰላ። ሄርማ)።
ሀብሀብ [1]፡-ዐስበ ዝሙት፤–ውሂብ ወሀበ።
[2]፡-»ሀብሀብ፤ ፡-(ዕብ ሀብሃብ፤ ጥብስ ሥጋ) የዝሙት ዋጋ ለጋለሞታ የሚሰጥ ፡-(ሕዝ፲፮ ፡-፴፪። መጽ ፡-ምስ)። ወይም ጋለሞታ ና ና ስጥ ስጥ አምጣ ጨምር የምትል።
-
ሀብለ ፤–ዋሸ ዐበለ ፤–ሐቢል ሐብለ።
ሀብለየ ፡-በዘበዘ፤–ሐብለየ ሕብልያ።
»ሀብት ፡-(ታት) በቁሙ፤ አሰጣጥ፤ ስጦታ፤ ዕድል ፈንታ፤ ጸጋ ብዕል፤ ምጽዋት ዳረጎት፤ ጕርሻ እጅ መንሻ፤ በከንቱ የሚሰጥ። ወሀቦሙ ሀብተ ወፈነዎሙ። ሀብትከ ልከ ይኩንከ። ኵሉ ሀብት ሠናይ እምላዕሉ። ሀብታተ መንፈስ ቅዱስ። በእንተ ሀብታት ፡-(ዘፍ፳፭ ፡-፮። ዳን፭ ፡-፲፯። ያዕ፩ ፡-፲፯። ፊልክ ፡-፻፸፬። ፍ ፡-ነ ፡-፳፮)። ውበት ውብነት፤ መልክ ደም ግባት፤ የተፈጥሮ ሀብት።
ሀብአ ፡-ዐባ ሸሸገ፤–ኀቢእ ኀብአ።
ሀትሒላ ፡-(ዕብራ) መዝሙር ምስጋና። መልአከ ሀትሒላ ፡-(ነሐ፲፩ ፡-፲፯)።
ሀኖስ ፡-(ጽር አኖስ ያኖስ) ከፊለ ስም የውቅያኖስ ክፋይ፤ ብጥብጥ ባሕር፤ የሚታወክና የሚናወጽ፤ የሚደምፅና የሚደረጽ። ይኸውም ከጠፈር በላይ ያለው ሢሶው ውሃ ነው፤ አንዱ እጅ ጠፈር አንዱ እጅ ውቅያኖስ እንዲባል፤ ይህ ደግሞ ሀኖስ ይባላል ፡-(ዘፍ፯ ፡-፲፩። ኩፋ ፡-፭። ሱቱ ፡-ዕዝ፮ ፡-፵፩)። ወበውእቱ መዋዕል ይወፅእ መቅሠፍቱ ለእግዚአ መናፍስት፤ ወይትረኀዉ ኵሎሙ መዛግብተ ማያት ዘመልዕልተ ሰማያት ወዲበ አንቅዕት እለ መትሕተ ሰማያት። ወይዴመሩ ኵሎሙ ማያት ዘምስለ ማያት ዘመልዕልተ ሰማያት፤ ማይሰ ዘመልዕልተ ሰማይ ተባዕታይ ውእቱ፤ ወማይ ዘመትሕተ ምድር አንስቲያዊት ይእቲ ፡-(ሔኖ ፡-፵፩)። ብዙዎች መተርጕማን ግን ፪ቱን እጅ ውሃ ጠፈር አደረገው ይላሉ እንጂ፤ ከጠፈር በላይ ብጥብጥ ባሕር አለ አይሉም።
ሀዑቢም ፡-(ዕብራ) ወፍራሞች፤ ደንዳኖች። ወፍሮች ድንዳኔዎች ፡-(ሕዝ፵፩ ፡-፳፮)።
ሀከከ [1]፡-(ሆከ) አወከ፤ አሸበረ። ሆከንና ዐከወን ተመልከት።
[2]፡-ሀከከ፤–ዐከከ፤ ፎከተ፤–ሐኪክ ሐከከ።
ሀከክ ፡-ሁክት ሽብር፤ ጠብ ክርክር፤ ቱማታ ፍጅት። ዕለተ ሀከክ። ማየ ሀከክ። አኮ በሀከክ ወበትዝልፍት። እለ ይገብሩ ሀከከ። እስመ በሀከክ ኀደርክሙ ወበሀከክ ይወድቁ ደቂቅከ ፡-(ኢሳ፳፪ ፡-፭። መዝ ፡-፻፳፫። ግብ፲፱ ፡-፴፮። ሮሜ፲፮ ፡-፲፯። ኩፋ ፡-፲)።
(ጥ ) ሀካይ ፡-(ያን ያት) የታከየ ሀኬተኛ፤ ሰነፍ ታካታ ሥራ ፈት ፡-(ምሳ ፮ ፡-፮። ፲ ፡-፬። ማቴ፳፭ ፡-፳፮)። በሀካይ ፈንታ ተሀካዪ ይላል። ኢትኩን ተሀካዬ ፡-(ምሳ፮ ፡-፫)።
ሀኬት ፡-በቁሙ ስንፍና ቸልታ፤ ንዝህላልነት፤ ተንኰል ክፋት። በሀኬት ወበፅርዐተ ዕደው ይወድቅ ናሕስ። እመ ዘረከባ እምሕሠማት ኮነ በሀኬተ ዚኣሁ። ሶበ ተሀጕለ ንዋየ አመጋቢ በእደ መጋቢ ዘእንበለ ጽልሑት ወኢሀኬት ፡-(መክ፲ ፡-፲፰። ፍ ፡-ነ ፡-፳፰ ፡-፴)።
ሀክይ ፡-(ሀከየ የሀኪ ይህኪ። ሀየየ፤ አከየ) መስነፍ መታከት መድከም መሰልቸት፤ ሥራ መተው መጥላት፤ መለገም ቸል ማለት። መጽሐፍ ግን በሀየየ ፈንታ ተሀየየ እንዲል፤ በሀከየም ፈንታ ተሀከየ ይላል። ዘይጻሙ በሥጋሁ ወይትሀከይ በነፍሱ። ኢናፅርዕ ቅኔ እደዊነ ወኢንትሀከይ። ኢትትሀከዩ ለንስሓ። ኢትትሀከይ ገቢረ ሠናይ። ኢይትሀከይ መዊተ ፡-(አርጋ። ዲድ ፡-፲፫። ቀሌ። ምሳ፫ ፡-፳፯። ግብ፳፭ ፡-፲፩)።
ሀወለ ፡-ቀላቀለ፤–ሐወለ።
ሀዊብ ቦ ት ፡-(ሆበ የሀውብ ይሁብ። ዕብ አዌህ) መፈለግ መሻት፤ መዞር መንከርተት ለማግኘት፤ የምግብ።
ሀዊክ ኮት ፡-(ሆከ የሀውክ ይሁክ። ዐከወ፤ ሀከከ) ማወክ መነቅነቅ ማንቀሳቀስ፤ ማገበር መጐስጐስ ማነሣሣት፤ ማሳዘን ማስጨነቅ ባለመከራ ማድረግ። ሆኮሙ ከመ ማዕበለ ባሕር። ኢተክህሎሙ ከመ ይሁክዋ ለሐመር እመካና። ተመሰሎሙ ለእለ ይለክፉ ምንተኒ በአጽባዕቶሙ ወየሀውኩ ኵለንታሁ። ሆከቶ ጸጋ እግዚ ከመ ይሑር ኀበ ገዳመ አስቄጥስ። ፈቃድከ ትሁክ ቅድስተ ሲኖዶሰ። የሀውኮሙ ለአሕዛብ ፡-(ሢራ፳፱ ፡-፲፰። ስንክ ፡-ኅዳ፳፰። አፈ ፡-ድ፪። ስንክ ፡-ጥቅ፳። ተረ ፡-ቄር፲፪። ኢዮ፲፪ ፡-፳፫)። ሖሰንና ኮሶን እይ፤ የዚህ አግዋር ናቸው።
ሀዋኪ ፡-(ኪት ክያን ያት) የሚያውክ አዋኪ፤ ሁከተኛ ነቅናቂ በጥባጭ። ሀዋኪ በግዕዙ። ሞገድ ሀዋኪ። ጸልዩዪ ውስተ ማኅበርነ ኢይባእ ሀዋኪ ፡-(መጽ ፡-ምስ። ተረ ፡-ቄር። ደራሲ)።
ሀውል ፡-(ዕብ ሄቤል) ላበት እንፏለት ከሞቀ ገላ ካፍ የሚወጣ። ከንቱ ነገር ዕብለት፤ ዋዛ ፈዛዛ ሣቅ ሥላቅ፤ ስድብ ነቀፋ።
ሀውለየ ፡-(ተቀ ግ) አፌዘ ሣቀ ተሣለቀ፤ ነቀፈ ሰደበ አረከሰ፤ ከንቱ አደረገ። ከመ ዝ የሀወልይዎ ለእግዚ፤ ወእለ ጸጋ ትስብእቱ ይመይጡ ውስተ ሀውልዮ። ተሀወልዮኑ ለእግዚ ቃል በዘሐመ። ኢተሀውልዮ ለዐቃቤ ሥራይ እመ በትሕትና አሕየወ። ኢየሀውልይዎኬ ለክርስቶስ ኃጥኣን። ኢተሀውሊኬ ሕማማቶ። እመ አረሚ ሀውለይዎ ለምስጢር ፡-(ተረ ፡-ቄር። ፭። ፲። ፲፰)።
ሀውክ ፡-በቁሙ፤ ሁከት እውክታ ንውጽውጽታ፤ መከራ ጭንቅ፤ ሽብር ድብልቅልቅ። ሀውከ ሞገድ። ከመ ያህድእ ኵሎ ሀውከ ወሐዘነ ፡-(ተረ ፡-ቄር፬ ፡-፲፬። ሔኖ፴፱ ፡-፪። ያዕ፫ ፡-፲፮)።
ሀየለ ፡-በረታ፤–ኀይሎ ኀየለ።
ሀየል ፡-(ላት። ዕብ አያል። ሱር አያላ። ዐረ ኢየል) ዋሊያ ዋላ፤ ቀንዳም ቀንደ ገላላ፤ ባለብዙ ዐጽቅ ባለተቀጥላ፤ ነዊኀ ዐፅም እግረ ሽመላ፤ የፌቆ ወገን የበረሓ እንስሳ። ዘያረትዖን ከመ ሀየል ለእገርየ። ወከመ ወሬዛ ሀየል። ህየ ተጋብኣ ሀየላት እስመ ሀየል ቀታሊሁ ለከይሲ። ሀየላት ወለዳ በውስተ ገዳም ፡-(መዝ ፡-፲፯። ማሕ፪ ፡-፱። ተረ ፡-ቄር፰። ኤር፲፬ ፡-፭)።
ሀዪድ ዶት ፡-(ሄደ፤ ሀየደ የሀይድ ይሂድ) መቀማት መንጠቅ፤ በምክንያት መውሰድ። እነሥአከ ወአሀይደከ። ወየሀይደክሙ ገራህተክሙ። ኢትትዐገሉ ወኢትሂዱ መነሂ ፡-(፩ነገ ፡-፪ ፡-፲፪። ፰ ፡-፲፬። ሉቃ፫ ፡-፲፬)።
፡-ማንጸብረቅ፤ መሳብ መበዝበዝ። ለብሰ ዳዊት ዘየሀይድ ዐይነ። አሣእኒሃ ሀየደ አዕይንቲሁ። ዕበየ ብርሃኑ የሀይድ አዕይንተ ፡-(፪ነገ ፡-፮ ፡-፲፬። ዮዲ፲፮ ፡-፱። ቀሌ)።
፡-መሄድ መራመድ፤ እግርን ማንሣት መንጠቅ። ምስጢሩ ያው መውሰድ ነው፤ ኬደ መርገጥ መደፍጠጥን ሄደ አነሣሥን ያሳያል፤ ኬደ ሖረ የግእዝ ሄደ ያማርኛ። ነጠቅ ነጠቅ አርግ እንዲሉ ቶሎ ቶሎ ሂድ ሲሉ።
ሀዪጵ ጶት ፡-(ሄጰ የሀይጵ ይሂጵ። ዐረ ሀበ፤ ሀፈ) መነቅነቅ መስበቅ፤ የሾተል የጦር። መሳብ መንደፍ፤ መወርወር ማወንጨፍ፤ መውጋት መግመስ መፈንከት። ህይጶተ ቀስት ወደርብዮ ኵያንው። ነደፈ ወሄጶ ለንጉሥ ማእከለ ሰንብዑ። ፈነወ ሐጾ ወሄጶ ጥቦ። የሀይጱ ሥዕርተ ወኢይስሕቱ። ወፀፎ በእብን ወሄጶ ውስተ ፍጽሙ ፡-(መቃ ፡-ገ፲፬። ፪ዜና ፡-፲፰ ፡-፴፫። ኩፋ ፡-፴፰። መሳ፳ ፡-፲፮። ሢራ፵፯፤ ፬)።
ሀያዪ ፡-(ተሀያዪ) ቸል ባይ ቸልተኛ፤ ታጋሽ። ጳውሎስ ሐዋርያ ኮነ ተሀያዬ ስብሐተ፤ ኀሳረ ወጽዕሰተ ፡-(ፊልክ ፡-፵፮። ፶፬። ፻፩)።
ሀያዲ ፡-(ዲት ድያን ያት) የሚቀማ ቀማኛ፤ ነጣቂ ወሳጅ ፡-(ሉቃ፲፰ ፡-፲፩። ፩ቆሮ ፡-፭ ፡-፲ ፡-፲፩። ፮ ፡-፲)። እምእደ ሀያዲሁ። ሀያዴ ንዋየ ባዕድ። ሰራቂ ወዐማፂ ወሀያዲ ወመሣጢ። ሀያድያን ፡-(ኤር፳፪ ፡-፫። ቀሌ። ፈ ፡-መ ፡-፲፯ ፡-፪። ፍ ፡-ነ ፡-፵፭)።
ሀይመነ ፡-(ሱር ሃይሜን። ዐረ ሀይመነ) አመነ ታመነ። ንባቡ ከየማን ፍችው ከአሚን የወጣ ነው፤ የመነንና አይመነን ተመልከት።
ሀይማኒ ፡-(ኒት ንያን ያት) ያመነ የሚያምን፤ የሚታመን፤ አማኒ ተአማኒ።
ሃይማኖተ አበው ፡-፤ የሊቃውንት መጽሐፍ፤ ድርሳን መልእክት፤ የኋላ ሰዎች ከየመጣፉና ከየቋንቋው ለቅመው ተርጕመው እንደ ፍትሐ ነገሥት ለብቻው አንድ ክፍል መጣፍ ያደረጉት ታላቅ ምእላድ፤ በቅዳሴ ጊዜ የሚነበብ።
ሃይማኖተ ንስጡር ፡-ንስጥሮሳዊ ባህል እንደ አይሁድ እንደ ሙሐመድ፤ ቃል ሥጋ ኮነን የሚነቅፍና የሚያጸይፍ፤ ቃል በሰው ዐደረ እንጂ ሰው አልኾነም፤ ሰው ኹኖ አልተቀባም ብሎ የቃልን ሰው መኾን መሲሕነቱን የሚክድ ፡-(ቄር)።
ሃይማኖተ እስላም ፡-እስላማዊ ባህል፤ ሰው ሠራሽ ትምርት ከኦሪት ከወንጌል የማይገጥም ፡-(አቡሻ ፡-፶)።
ሃይማኖት ፡-(ሱር ሃይማኑታ) የዑደት የምሕላ ጸሎት ከቤተ ክሲያን ውጭ በዙሪያው በገረገራው የሚባል፤ እንደ ጥምቀት እንደ ጕዞ ፍታት ያለ፤ ወረብ ለዘብ፤ የታቦት ዘፈን። ሀይመና ሀይመን እንዲል ፡-(ያረርጌ ጨፋሪ)።
፡-በቁሙ፤ ማመን መታመን፤ እምነት ጽኑ ተስፋ፤ የአምልኮት ባህል፤ በልብ በረቂቅ ሐሳብ የሚሣል። ሃይማኖተ ዕቁብ ምስለ ቢጽከ። ብእሲ ዘተአምር ከመ ቦ ሃይማኖት። እለ አዕረፉ በሃይኖተ ክርስቶስ ፡-(ሢራ፳፪ ፡-፳፫። ፳፯ ፡-፲፪። ዲድ ፡-፴፬)።
ሃይማኖት ርትዕት ፡-ኦርቶዶክሳዊት፤ የኦርቶዶክስ ባህል ፡-(ቅዳ)።
ሃይማኖት ቅድስት ፡-ምስጢረ ሥላሴ፤ ምስጢረ ሥጋዌ ፡-(ይሁ ፡-፳)።
ሀይከል ፡-(ዕብ ሄካል ሱር ሄካላ። ዐረ ሀይከል) ታላቅ ቤት አዳራሽ ሰቀላ፤ ቤተ መቅደስ፤ ከዚያውም ፵ው ክንድ መካከለኛው ክፍል፤ ጽርሕ። ሀይከለ ቍድስ ፡-(ዮሴፍ)።
፡-መቅደስ ምሥዋዕ መንበረ ታቦት፤ በተገናኝ ማደሪያ ማለት ነው። ሲያበዛ ሀይከላት፤ ሀያክል ይላል።
ሀይብ ፤–በቁሙ ዐይብ ፤–ሔበ ሐይብ።
ሀይወ ፡-ዳነ፤–ሐዪው ሐይወ።
ሀይይ ዮት ፡-(ሀየ፤ ሀየየ የሀይይ ይህየይ። ሀከየ) ቸል ማለት፤ መናቅ ማቅለል፤ መተው መጣል። መጽሐፍ ግን በሀየየ ፈንታ ተሀየየ ይላል፤ አያሰኝም። ኢትትሀየይ ትእዛዘ እምከ። ተሀየዩ ሥርዐተ። አሙንቱ ተሀየዩ ወኀለፉ። ትትሄይ ኀጣይአ ሰበእ። ለዕቡያን ይትሄየዮሙ እግዚ ፡-(ምሳ፩ ፡-፯። ቀሌ። ማቴ፳፪ ፡-፭። ጥበ፲፩ ፡-፳፬። ያዕ፬ ፡-፮።
ሀይድ ፡-ቅሚያ፤ ንጥቂያ፤ ምክንያት ያለው አውሳሰድ ፡-(መዝ ፡-፷፩። ኢሳ፷፩ ፡-፰)።
ሀደመ ፡-ተረተ፤–ሐድሞ፤ ሐደመ።
ሀደየ ፡-(ዐረ ሀደይ) አበሰለ አሟከከ፤ የሥጋ ያጥነት የሚቀቀል ኹሉ።
ሀዲም ሞት ፡-(ሀድመ፤ ሀደመ የሀድም ይህድም። ዕብ ራዳም) ማንቀላፋት፤ በንቅልፍ መያዝ መወሰድ፤ መስነፍ መታከት እንቅልፋም መኾን። መጨለም መክበድ፤ ሌሊት ውድቅት መኾን የጊዜ። መጽሐፍ ግን በሀድመ ፈንታ ተሀድመ ይላል። ዘኒ ተሀድሙ። እምቅድመ ይብራህ ብርሃነ መዓልት ወእምቅድመ ይትሀደም ሌሊት ፡-(ዕዝ፮ ፡-፴፩። ቅዳ ፡-አፈ)።
ሀዲእ ኦት ፡-(ሀድአ የሀድእ ይህዳእ። ዐረ ሀደአ) ዝም ጸጥ ዳ ጫ ማለት፤ ከሁከት ማረፍ፤ መርጋት መጨመት፤ መቆም መገታት። ዝኅነን ተመ፤ የዚህ ጎር ነው። ወሀድኡ አይሁድ በመዋዕለ ስምዖን። ውእቱሰ ኢይትናዘዝ ወኢየሀድእ። ሀድአት ልባ እምሐዘን። በመዋዕሊሁ ሀድአት ወአርመመት ምድረ ይሁዳ። ዝኅነ ሞገድ ወሀድአ ማዕበል ፡-(ዮሴፍ። ስንክ መስ፳፰። ፪ዜና ፡-፲፬ ፡-፩። መጽ፤ ምስ። ዘፀ፬ ፡-፳፰–፴፬)። ዳታ ዳተኛ ማለት ከዚህ ወጥቷል።
ሀገሪታዊ ፡-ዝኒ ከማሁ፤ ዐጀም አረመኔ። ጽሑፍ አልቦ ውስተ ልበ ንጹሓን ፍልጠት ማእክለ አይሁዳዊ ወሀገሪታዊ ገብር ወአግዓዚ ፡-(ፊልክ ፡-፹፯)።
ሀገሪት ፡-ያቀኗት የቈረቈሯት፤ የተወለዱባት አገር ርስት ጕልት። ወዳጅ ዘመድ፤ ዐብሮ አደግ ያገር ሰው፤ ተወራራሽ ወንድም። በላ ለጥበብ እኅትየ አንቲ ወለአእምሮ ሀገሪተከ ረስያ ፡-(ምሳ፯ ፡-፬ )።
፡-አንባ ኰረብታ፤ ዕርድ ምሽግ። ሀገሪት ይእቲ ለኵሎሙ እለ ይቀርብዋ ፡-(ምሳ፫ ፡-፲፭)።
፡-ማኅበር ጉባኤ፤ ድርገት። እንዘ ሀለዉ በምድር ሀገሪተ ይኩኑ ምስለ ሰማያውያን ፡-(ቀሌ)።
፡-ባላገር ባለጌ፤ አረመኔ ያልተማረ ያልሠለጠነ፤ ዐጀም። ኢሐቃል ወኢሀገሪት ፡-(ቆላ፫ ፡-፲፩)።
ሀገራዊ ፡-ያገር፤ ባላገር፤ ባላባት አቅኚ፤ ሹም ሽማግሌ፤ አውራ ቀንድ፤ ወይም ዕድር፤ ልማድ። ፡-(ተረት) ያገር ዕድር ለንጉሥ ያስቸግር። ምግብና ሀገራዊት ፡-(ፍ ፡-ነ ፡-፲)።
ሀገር ፡-(ብ አህጉ(ጕ) ር፤ ራት) በቁሙ፤ አገር መንደር፤ ከተማ ገጠር፤ ብዙ ቤቶች የተሠሩበት፤ ብዙ ሰዎች የሚኖሩበት፤ በያቅኝውና በየክፍሉ ገዥ አዛዥ፤ ዳኛ መልከኛ ያለው፤ ታላቁም ታናሹም። ኢትክል ተከብቶ ሀገር እንተ ተሐንጸት መልዕልተ ደብር። ሀገር ቅድስት። ሀገረ እስራኤል። ውስተ አህጕር ወአዕጻዳት ፡-(ማቴ፭ ፡-፲፬። ሢራ፳፬ ፡-፲፬።ኤር፫ ፡-፰። ማር፮ ፡-፴፮)።
ሀገየ ፡-ባጀ፤–ሐግይ ሐገየ ሐጋይ።
ሀጕል ፤ (ላት)
፤ ጥፋት ጕዳት
፤ ችግር ዕጦት። ፍኖት እንተ ትወስድ ውስተ
ሀጕል። ወልደ ሀጕል። ሀጕል ዐቢይ። በሀጕልክሙ እሥሕቅ
(ማቴ፯ ፡ ፲፫። ዮሐ፲፯ ፡ ፲፪። ግብ፳፯ ፡ ፲። ምሳ፩ ፡ ፳፮)። አጥፍኦ አህጕሎ በማለት
ፈንታ ሀጕል ይላል። ጊዜ ለኀሢሥ ወጊዜ
ለሀጕል (መከ፫ ፡ ፮)።
ሀጕል ሎት ፡-(ሀጕለ ሀጐለ የሀጕል ይሀጐል) ማጣት መቸገር፤ የያዙትን የረዘዙትን፤ ወይም የሹትን የተመኙትን አለማግኘት። ከመ ኢትህጐል ርስተከ። ህጐል ወርቀከ እምትህጐል ዐርከከ። ሀጕለ አዕይንቲሁ ጦቢት። ሀጕሉ ዕሌቶሙ። የሀጕሉ ተስፋሆሙ ፡-(ሢራ፬ ፡-፮። ፳፱ ፡-፲። ጦቢ፯ ፡-፯። ማቴ፮ ፡-፪። ዲድ ፡-፳፭)።
ህጕሬ ፡-ቀይ ቀለም፤–ሕጕሬ።
ሀጊር ፤ ሮት ፤ (ሀገረ የሀግር ይህግር። ዕብ ሀጌር) ፤ ዐዲስ ቦታ መሻት መፈለግ ፤ መመርመር ፤ ማቅናት
፤ መቈርቈር
፤ ምንጩን
መማስ ዱሩን መጣስ ፤ መከተም መመንደር ፤ መዲና መሥራት።
ሀጊናህ ፡-(ዕብራ) የቀና ቀጥ ያለ፤ የተካከለ፤ ባለዕርከን፤ ፍኖተ መዘምራን ፡-(ሕዝ፵፪ ፡-፲፪)።
ሀግረተ ፡-(ተቀ ፡-ግ) ተጋ፤ ዐሰበ ተወዘወዘ፤ በትጋት በሐሳብ ተያዘ በሀግረተ ፈንታ ጋህረተ ይላል፤ የጣፊ ስሕተት ነው። ከመ ትትጋህረቱ ለመፍቅደ ልብየ ፡-(አርጋ ፡-፬)።
ሀፊው ዎት ፡-(ሀፈወ የሀፉ ይህፉ። ዐረ ሀውፍ፤ ሁፍ፤ ውዑይ ነፋስ) መውዛት መድከም፤ መሞቅ በላበት መጠመቅ። ፈተወት ትትኀፀብ፤ እስመ ሀፈወት። እስከ የሀፍዉ። ጾመ ወጸለየ ደክመ ወሀፈወ። በጸዊረ መስቀሉ ሀፈወ፤ እስመ ክቡድ ውእቱ ፡-(ዳን፩ ፡-፲፭። ሥር ፡-ጳኵ። ግንዘ። ቅዳ ፡-ግሩ)።
ሀፍ ፡-(ዕብ ዚዓህ) ወዝ ላበት፤ ድካም ፡-(ዘፍ፫ ፡-፲፱። ሉቃ፳፪ ፡-፵፬)። አብዝኀ ስግደተ እስከ ይውሕዝ ሀፉ ከመ ማይ። ዘእንበለ ጻማ ወሀፍ። ፈንዉ ሲሳዮሙ እምንዋይክሙ ወሀፈ ገጽክሙ ፡-(ገድ ፡-ተክ። አፈ ፡-ተ፫። ዲድ ፡-፳፭)።
፡-ሙቀት፤ ሐሩር። ቍር ወሀፍ። ብሔረ ጽምእ ወሀፍ። ሀፍ ወሞቅ ፡-(ዘፍ፰ ፡-፳፪። ዘዳ፴፪ ፡-፲። ሔኖ፹፪ ፡-፲፮)።
ሀፓሊ ፡-መሀፕል፤ መሀፒል፤ እየመታ የሚያጥብ ዐጣቢ። ገራህተ መሀፒል። ዘኢይክል መሀፒል አጻዕድዎ ከማሁ ፡-(ኢሳ፯ ፡-፫። ፴፮ ፡-፪። ማር፱ ፡-፫)።
ሀፐለ ፡-(ዐረ አበለ፤ ወበለ) ዐጠበ፤ መታ ደበደበ። በመርገጥና በመጠቅጠቅ ፈንታ በዱላ እየመቱ የሚያጥቡት ዕጥበት አለና፤ ዕጥበቱንም። አመታቱንም ባንድነት ያሳያል።
ሁ [1]፡-ሁ፤ ፡-(ሁ–ኑ) ጥያቄ፤ የጥያቄ ቃል፤ ንኡስ አገባብ፤ ፍችው ን። በቃል መጨረሻ እንደ ዝርዝር ትራስ እየኾነ ይገባል። ኢኮነሁ ከመ ዝ። እምኔሁ ይሴወር። ትስአሉኒሁ መጻእክሙ ፡-(ዓሞ፪ ፡-፲፩። ኢዮ፴፰ ፡-፯። ሕዝ፳ ፡-፫)። ቦሁ አመ ነገሩክሙ። አልቦሁ አመ አንበብክሙ። አኮሁ አነ ዘአወልድ እያለም በነባር አንቀጽ ይገባል። ኑ ደግሞ ሁ በገባበት ይገባል፤ አገባቡን በቦታው እይ። አንዳንድ ጊዜም ሁ ምናልባት ይኾናል። እመሰ ትብሉሁ። ሶበሁ የአምር በዓለ ቤት። እመ አንተሁ ክርስቶስ ፡-(ኢሳ፷፮ ፡-፯። ማቴ፳፬ ፡-፵፫። ፳፮ ፡-፷፫)።
[2]፡-ሁ፤ ፡-(ውእቱ) ባዕድ ዝርዝር ጠቃሽ፤ ዐጸፋ፤ ምእላድ፤ ላንድ ለሩቅ ወንድ፤ በሩቅ ወንድ አንቀጽ ለሚጠራ ኹሉ። ርሱ ያ ማለት ነው፤ ብእሲሁ፤ ሰውዮው ያ ሰው። ሃ ሆሙ ሆን እያለ በሩቆች ብቻ ይረባል። ኪያ ኪያሁ፤ ለል ለሊሁ ቅድሜሁ ድኅሬሁ፤ ቀደሳሁ ወደሳሁ፤ የመሰለው ኹሉ። ዝ ዝንቱ ከዘ እንደ ወጣ ውእቱም ከሁ ወጥቷል፤ የርባታ መደቦች የሚባሉ ዐሥሩ ሰራዊት ሳይቀሩ ኹሉም የሁ ዘር ናቸው።
ሁል ፤–ርኵስ ፤–ሐዊል ሖለ ሐወለ
፤ ሑል።
ሁስጱ ፡-(ጽር ሒሶፖስ) የቀነበጥ ችቦ፤ ለባልብ። አዛብን ተመልከት፤ ከዚህ ጋራ ፩ ነው፤ ባለብሉዮች ግን ለይተው ስምዛ አሸክት ይሉታል። ቈጽለ ሁስጱ። ሐምለ ሁስጱ ፡-(ዘሌ፲፬ ፡-፬ ፡-፯። ፫ነገ ፡-፬ ፡-፱። ዮሐ፲፱ ፡-፳፬። ዕብ፱ ፡-፲፱)።
ሁከት ፡-(ታት) በቁሙ፤ ማወክ፤ መታወክ፤ መታመስ መተራመስ፤ ሽብር። ሁከተ ማይ። ተሀውኩ ዐቢየ ሁከተ። ሁከተ ነፍስ። ቃል ወሁከት። ሰይጣን መፍቀሬ ሁከት። ከመ በድምፀ ምጽአትከ ኢይኩን ሁከት ፡-(ዮሐ፭ ፡-፫። ሔኖ፰ ፡-፩። ጥበ፲፯ ፡-፰። አስቴ ፡-፩። ቀሌ። ኪዳ)።
ሁጅራ ፡-(ዐረ ሂጅረት) ሠግር፤ ቀመር። ዓመተ እልሁጅራ ፡-(አቡሻ ፡-፲፩)።
ሂ ፡-(ሂ–ኒ) ዋዌ፤ ፍችው ም ደግሞ፤ ግን ስንኳ። ሂ–ሂ ኒ–ኒ፤ ወይም ሂ–ወ–ሂ ኒ ወ–ኒ እያለ ብቻውንም ከወም ጋራ ይገባል። አነኒ አንተሂ። አቡየሂ ወአነሂ። እመሂ ሠርከ ወእመሂ መንፈቀ ሌሊት። ከሃሊ አንሰ ተጽናሰሂ ወተደልዎሂ፤ ርኂበሂ ወጸጊበሂ፤ ሐሚመሂ ወተፈሥሖሂ ፡-(ፊልጵ፬ ፡-፲፪)። ግንና ስንኳ ሲኾን አገባቡ እንደ ወ ነውና፤ የወን አፈታት ተመልከት።
ሂደት ፡-መቀማት ፡-(ጥቀ) መቀማት አቀማም አወሳሰድ፤ ቅሚያ ንጥቂያ ፡-(አርጋ)። መሄድ መራመድ፤ አካሄድ አረማመድ፤ እግር አነሣሥ።
ሂጰት ፡-መንደፍ መነደፍ፤ አነዳደፍ ነደፋ ውርወራ፤ ንድፊያ ውጊያ፤ ውግታት ግምሳት። አኮ በዘቀስት ሂጰት ፡-(ቄረ ፡-ገ፯)።
ሄ [1]፡-ጊዜ፤ ቦታ ወገን ማእዝን ዙሪያ እየኾነ ከኵል ጋራ ይነገራል። ኵልን ተመ፤ ኔ ከአሐቲ በቀር በሌላ እንዳይገኝ፤ ሄ ደግሞ ከኵል በቀር በሌላ አይገኝም።
[2]፡-ሄ፤ ፡-(ዕብ ሄእ) ስመ ፊደል ኃምስ፤ ሀ። እንሆ እንካ ማለት ነው ፡-(መዝ፻፲፰ ፡-፴፫–፵። ሰቈ፩ ፡-፭። ፪ ፡-፭። ፫ ፡-፲፪። ፬ ፡-፭)። ህና ሆ እንደ ሌሎቹ የተለየ ሥራ የላቸውም።
ሄላ ፡-የወይን ዘለላ፤ የበሰለ ደሙ የመላ። አጥባትኪ ከመ ሄላ ዘእምኔሆን ይውሕዝ ሐሊብ ፡-(አርጋ። ማሕ፯ ፡-፰)። እኄላን ተመ፤ የዚህ መንቲያ ነው፤ ባለብሉዮች ግን ምንጭ የበለስ ቋንጣ የሰሌን ፍሬ ይሉታል። ንባቡ ሀየላዊ፤ ምስጢሩ መስተፍሥሒ ከመ ሀየል። አስካል ሄላ መባሉ በምላሴ እንጂ ቃል በቃል አይዶለም።
ሄላንሳን ፡-ክቡር ልብስ፤–ቂላኖስ።
ሄሴፎት ፡-(ዕብ ሀአሲፎት) የጥራጊ የጕድፍ መጣያ፤ ያዛባ የፍግ መቈለያ፤ ባለብሉዮች ግን ግናይ ይሉታል። አንቀጸ ሄሴፎ ፡-(ነሐ፲፪ ፡-፴፩)።
ሄርማ ፡-የመጽሐፍ ስም፤ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ የጣፈው፤ እንደ ሣልስ ቆሮንቶስ ያለ ከቍጥር ያልገባ ትርፍ፤ ወሪድየ ብሔረ ሮሜ ብሎ የሚዠምር። ስምነቱ ሄርሜን ከማለት የወጣ ነው፤ ሄርሜናዊ ያሰኛል፤ ጸሓፊው ሄርሜን ስለ ተባለ መጽሐፉም ሄርማ ተብሏል።
ሄርሜን ፡-(ጽር ሄርሚን) ጣዖት ስመ ጣዖት፤ በመንታ መንገድ ላይ የሚያቆሙት። መሪ አስተማሪ፤ ትርጁማን አፈ በሃማን ማለት ነው ፡-(ግብ፲፬ ፡-፲፪)።
ሄሮድስ ፡-(ዕብ ሆርዶስ) የሰው ስም፤ ኤዶማዊ የእስራኤል ንጉሥ፤ በዘመነ ልደት የነበረ ፡-(ማቴ፪ ፡-፩)።
ሄሮድያኖስ ፡-(ጽር ሄሮዲዎስ) ያሞራ ስም፤ ሽመላ ሽመላዊ፤ እግረ ሽመል ዐንገተ ግመል፤ እግሩ ሽመል የሚያካክል። ፡-(ተረት) ካህንና ሽመላ ያልዘራውን ይበላ። ሄሮድያኖስ በሰማይ የአምር ዕድሜሁ ፡-(ኤር፰ ፡-፯። ዘሌ፲፩ ፡-፲፱። መዝ ፡-፻፫። ዘካ፭ ፡-፱)።
ሄዔኪር ፡-(ዕብ ሄዔቢር) አሳለፈ አሻገረ፤ አስተላለፈ የጊዜ የወራት። ሐተታውን በቢዶን ፍች እይ፤ ባለብሉዮች ግን ደካማ ዘበጽሐ ጊዜሁ ኅሱር ይሉታል ፡-(ኤር፵፮ ፡-፲፯)።
ሄከ ፡-አላመጠ፤–ሐዪከ ሔከ።
ሄጠ ፡-ሸነገለ፤–ኀዪጥ ኄጠ።
ሄጰ ፡-ወጋ ገመሰ፤–ሀዪጵ።
ሄጶዲያቆን ፡-(ጽር ሂፖዲያኮኖስ) የዲያቆን ተወራጅ፤ ንፍቀ ዲያቆን ፡-(መጽ ፡-ምስ)።
ሄጶዴጤን ፡-(ጽር ሂፖዲቲስ። ዕብ ምዒል) ልብሰ ተክህኖ፤ የላይ ልብስ ታላቅ ቀሚስ እጀ ሰፊ መቋረፊያ። ጶዴሬን እይ፤ ከዚህ ጋራ ፩ ነው ፡-(ዘፀ፴፮ ፡-፴። ዘሌ፰ ፡-፯)።
ሄጶጳ ፡-(ጽር ሄፖፓ፤ ሄፖፕስ) ስመ ዖፍ ንኡስ፤ መጠኑ የርግብ የዋኖስ፤ ቍንጯም
አፈ ረዥም የሾለቅ ዐይነት ዝንጕርጕር ኰሳኵስ። ባለብሉዮች ግን ዐቢይ አሞራ ይሉታል ፡-(ዘሌ፲፩ ፡-፲፱። ዘዳ፲፬ ፡-፲፰)።
ህሉና ህልውና ፡-ነዋሪነት፤ አነዋወር ኑሮ። ህሉና ሥላሴ። ህሉና መለኮት ፡-(ቅዳ)።
ህላሊ ፡-ሠርቃዊ ወርኃዊ፤ የጨረቃ ወር። አውራኀ ህላል፤ ህላሊ ፡-(አቡሻ ፡-፳፭)።
ህላል ፡-(ዐረ ሂላል) ሠርቀ ወርኅ፤ ልደተ ወርኅ፤ ሐዲስ ለጋ ጨረቃ።
ህላዌ ፡-(ውያት) መኖር መኾን፤ አናዎር፤ ኑሮ። ንዜኑ ህላዌሁ ለአብ ምስለ ወልዱ፤ ወህላዌሁ ለወልድ ምስለ አቡሁ። ሠለስቱ ህላዌ በአካላት ወአሐዱ ህላዌ በመለኮት ፡-(ቅዳ ፡-ግሩ። ሃይ አበ ባለ)። ይህ ቃል ለሦስቱ ኹሉ የተለየ የአካል ህላዌና ግብር እንዳላቸው ያሳያል፤ ትርጓሜውም ይህ ነው። ወላዲ የአብ አካል፤ መውለድ ማሥረጽ ግብሩ፤ ከዊነ ወላዲ ወይም ወላዲነት ህላዌው፤ ባማርኛ ባሕርይ ይባላል፤ ልዩነት ያለው ገጽ ቁመት አቋቋም መልክ ማለት ነው። ተወላዲ የወልድ አካል፤ መወለድ ግብሩ፤ ተወላዲነት ህላዌው። ሠራጺ የመንፈስ ቅዱስ አካል፤ መሥረጽ ግብሩ፤ ሠራጺነት ህላዌው፤ ሠለስቱ ህላዌ ይህ ነው። ወአሐዱ ህላዌ ያለውም፤ መውለድና ማሥረጽ መወለድ መሥረጽ በዚያው ባንዱ ባሕርይ ባንዱ መለኮት ነውና፤ ባሕርይ የሦስቱ መሣሪያ መኾኑንና አንድነቱን መደብ አድርጎ እንደ አካላት ወላዲ ተወላዲ ሠራጺ አለመባሉን ያሳያል። ምስጢሩ፤ ባሕርይ ሳይከፋፈል፤ አካል ሳይቀላቀል፤ ስምና ግብር ሳይፋለስ የአካል ህላዌ ሳይፈርስ፤ ባንድነትና በሦስትነት ጸንቶ መኖር ነው። ፫ መለኮት የሚሉ ግን፤ ወላዲ ባሕርይ ተወላዲ ባሕርይ ሠራጺ ባሕርይ እያሉ የአካላትን ስምና ግብር ለባሕርይ ሰጥተው ይፈታሉ።
[1]፡-አካል ገጽ፤ አቋቋም ቁሙት፤ አኳኾን ኹነታ። አካል ማለት ባሕርይና ግብርን መልክንና ስምን ኹሉን ሰብስቦ የሚይዝ፤ ሰብሳቢ ገዥ አዛዥ ባለቤት ማለት ነው፤ የአካልን ፍች ተመልከት። እግዚአብሔር በዓለ ሠለስቱ ህላዌ አሐዱ በባሕርይሁ ወሥልጣኑ ወመለኮቱ። እስመ አበዊነ ሰመይዎ በዝንቱ ገጸ መካን ፡-(በአንቀጸ ተዋሕዶ) ለህላውያት አካላተ፤ አትናቴዎስኒ ረሰየ ህላዌ አሐደ አካለ ዘእግዚአብሔር ቃል ዘተሠገወ። እስመ ህላዌ ይትበሀል በእንተ ክዋኔ ወአካል፤ ወክዋኔሂ ይትበሀል ከመ ውእቱ ህላዌ ዘያስተጋብእ ኵሎ፤ ወአካልሰ ዘአሐዱ ህላዌ ውእቱ። ተውሕዶ አንድ የኾነ አካል ማለት ነው፤ ገጽ አቋቋም ቁመት ያልነው የአካል ባሕርይ ይባላል፤ አካል ያለገጽ ያላቋቋም አይገኝምና። እስመ በዝየ ይሰመይ አካል ህላዌ አካሉ ለወልድ፤ ወአኮ ውእቱ ህላዌ ዘያስተጋብኦሙ ለሥሉስ ቅዱስ፤ ወበእንተ ዝ ተሠገወ እግዚ ቃል ፡-(አክሲ። ሃይ ፡-አበ ፡-ብን። ዲዮ። መቃር)። ህላዌን የአካል ባሕርይ ማለት አካልን አቋቋም ብሎ ነው።
[2]፡-ባሕርይ፤ ጠባይ። ብሕረንና ጠብዐን ተመልከት። ኅቡረ ህላዌ ምስለ አብ በመለኮቱ፤ ኅቡረ ህላዌ ምስሌነ በትስብእቱ። ወኢተወለጠ ህላዌ ቃል ኀበ ህላዌ ሥጋ ወህላዌ ሥጋ ኀበ ህላዌ ቃል፤ ዳእሙ ይሄልዉ ክልኤቱ ህላውያት በበ ህላዌሆሙ እንበለ ውላጤ ፡-(ተረ ፡-ቄር። ሃይ ፡-አበ መጠሊ)። ህላዌ በአንቀጸ ተዋሕዶ አካል ስለ ኾነ አሐዱ እንዲባል በአንቀጸ ተዐቅቦም ባሕርይ ስለ ኾነ ክልኤቱ ይባላል፤ እውነተኛው የሊቃውንት ዐዋጅ ይህ ነው። ወኢተዋሐደ በመንፈቀ ህላዌ ወኢኮነ ካልኦ እንስሳ በአንትጎ፤ አላ ምሉእ ወፍዱም፤ በአሐዱ ህላዌ ይገብር ዘክልኤቱ ህላውያት ፡-(ሃይ ፡-አበ ፡-ኤፍ)። አሐዱ ያለው አካል፤ ክልኤቱ ያለው ባሕርይ እንደ ኾነ አስተውል።ባሕርያት ፪ እንደ ሆኑ የባሕርያት ፍሬ ግብራትም ፪ ናቸው፤ ተወላዲው ፩ አካል ሲኾን ልደቱ ፪ እንዲባል፤ ግብሩም ሠሪው አንድ ሲኾን እንደ መሣሪያው እንደ ባሕርይ ፪ ይባላል። ግብርን አሐዱ ማለት ልደትንም አሐዱ ያሰኛል፤ ልደት ቅሉ ግብር ነውና ፪ መባሉ ስለዚህ ነው፤ ግብር ባሕርይን፤ ገቢር አካልን ይከተላል። ቦቱ መንክራት ወዓዲ ቦቱ ሕማማት ወውእቱ አሐዱ ህላዌ፤ በመለኮቱ ይገብር መንክራተ ወበትስብእቱ ይትዌከፍ ሕማማተ። ርኢከኑ ዘከመ እፎ ሎቱ ክልኤቱ ግብራት ኅቡረ። ወዐቀበ እሎንተ ክልኤተ ግብራተ በኵሉ ዘመን። ወኢንቤ ከመ መንክራት ለአሐዱ ወሕማማት ለካልኡ፤ አላ እሙንቱ ለዝንቱ አሐዱ ባሕቲቱ፤ ከመ አምላክነ ወእግዚእነ ኢየሱስ ክርስቶስ አሐዱ አካል ሥግው ወአሐዱ ህላዌ ዘኀብረ ኵለንታሁ ለወልድ ዘውእቱ ቃል ወነፍስ ወሥጋ ወልቡና ወምግባር። ህላዌ ዘኀብረ ኵለንታሁ ያለውን ቃል ሥጋ ነፍሰ ልቡና ምግባር ብሎ ቈጠረ፤ ልቡና ምግባር የሌለው ሌላ ህላዌ ይኾናል እንጂ የሰው ህላዌ አይባልምና ፡-(ሃይ ፡-አበ ፡-ጎር። ኤጲ። መቃር)።
[3]፡-ጠቅላይ ስም፤ ኵላዊ አስተጋባኢ፤ ስምነቱ ካቶሊክ እንደ ማለት ነው። ለፈጣሪ ሳይቀር በሰማይ በምድር ላለ ፍጥረት ኹሉ ይነገራል። ወአእአምሩ እስመ ስመ ህላዌ ይትበሀል በገጸ መካን ህየንተ ህላዌ ኵሉ ዘመድ ፡-(ሃይ ፡-አበ ፡-ዲዮ)። አስተጋባኢ ስም ስለ ኾነ እንደ ጠባይዕ ለአካል በሚመችበት አካል፤ ለባሕርይ በሚመችበት ባሕርይ ይባላል። ባማርኛ ሌላ ስም ታጥቶለት እንጂ በአካልና በባሕርይ መካከል ሌላ የተለየ ማእከላዊ ስም ያስፈልገው ነበር። በምድር ያለ የፍጥረት ኹሉ ሥር አራቱ ባሕርያት ናቸው፤ ማይ መሬት ነፋስ እሳት፤ እሊህ አራቱ እየተዋሐዱ ሌላ ዐይነት ባሕርይ፤ ሥጋን ዕንጨት ያስገኛሉ። የተለየ የባሕርይ ስሙ ሥጋ ዕንጨት ነው፤ ባራቱ ባሕርያት ተውሕዶ ሥጋ ኹኖ ዕንጨት ኹኖ የቆመበት ውሳጣዊ አስተጋባኢ ስሙ ህላዌ ተብሏል። «ጽርኣውያን ህላዌን ወስያ፤ ባሕርይን ፊሲስ ይሉታል። ላቲናውያንም ህላዌን ሱብስታንስያ፤ ባሕርይን ናቱራ ይሉታል»። አካል ለባሕርይ አይነገርም፤ ባሕርይም ለአካል አይነገርም፤ ህላዌ ግን ኹለቱ አንድ ኹነው የቆሙበት አስተጋባኢ ስም ስለ ኾነ ለኹለቱ ኹሉ ይነገራል። የወጣበት የስምነቱ ምስጢር ግን አጥብቆ አጥልቆ ሲመረመር ፥ አኳዃንንና አቋቋምን የተዋሕዶውን ጽናትና አናዎር ያሳያል እንጂ ፥ አካልን ብቻ ባሕርይንም ብቻ አያሳይም። የንጨት ኹሉ ባሕርይ አንድ ሲኾን ህላዌው እየቅል ነው፤ ብርቱ አለ ግብዝ አለ፤ ካራቱ ባሕርያት የተፈጠረ ኹሉ እንዲህ ነው። የመላእክትና የነፍስ ባሕርይ ግን መሠረት የለውም እምኀበ አልቦ ነው፤ መላእክትን ዘይሬስዮሙ መንፈሰ ወነደ እሳት ቢላቸው፤ የሚራቀቁ የሚማወቁ ተለኣክያን ማለት ነው እንጂ ፥ እኛ ከምናውቀው ነፋስና እሳት ማለት አይዶለም፤ ከዚህስ ቢኾን እንደ መጠኑ ባየናቸው በሰማናቸው ነበር። አካላውያን ኹነው ተፈጥረዋል፤ ባሕርያቸው ከአካላቸው አይቀድምም፤ የአካላቸው አኳኾን ህላዌ ይባላል፤ የነፍስም እንደ መላእክት ነው። የነፍስ ባሕርይ ወደ ሥጋ ባሕርይ ወደ ግዘፍ ሳይሳብ፤ የሥጋም ባሕርይ ወደ ነፍስ ባሕርይ ወደ ርቀት ሳይሳብ፤ ነፍስና ሥጋ ተውሕደው ፩ አካል ፩ ህላዌ ፩ ሰው ይገኛል። እስመ ክዋኔሁ ለሰብእ ውእቱ ግብር እለ ኢይትማሰሉ በበይናቲሆሙ ወኢየኀብሩ፤ ወቃልኒ ኢየተኀር ምስለ ሥጋ በከመ ኢተኀብር ነፍስ ምስለ ሥጋ እንዘ ብእሲሁ አሐዱ እምነፍስ ወሥጋ ወአሐዱ ገጽ እምዘኢየኀብሩ ግብራት። ነፍስና ሥጋ ተውሕደው አንድ ኹነው የቆሙበት አካል ህላዌ ይባላል፤ ለቃልም በተለየ አካሉ የተለየ ህላዌ አለው፤ አስቀድመን እንደ ተናገርነ።
[4] መኖሪያ መኗሪያ። ምስጢሩ አናዎር ካለው ይገባል። ኀበ ህላዌሁ ተመይጠ ልሳኑ ውቁይ፤ ኀበ ህላዌሁ አግብኦ ፡-(ስንክ ፡-ጥር፭) ዳግመኛም ባሕርይ ያላካል፤ አካል ያለባሕርይ ብቻ ብቻውን አይኖርምና አንዱ ላንዱ ቦታ መኾኑን ያሳያል።
[5]፡-ሥራ፤ ግብር። ህላዌ ግፍዕ፤ የግፍ ሥራ ግዙፍ ግፍ ፡-(ሔኖ፺፩ ፡-፭)። እንዲህ ከኾነ የህላዌንና የጠባይዕን ፍች በየስልቱ ማስተዋል ይገባል፤ ኹለቱ ኹሉ ፩ ናቸውና።
ህልው ፡-(ዋን ዋት ሉት) ያለ የኖረ፤ የነበረ፤ የሚኖር ነባር፤ ቀዋሚ እውነት። ፈጠረ ፍጥረተ ይኩን ህልወ። መድኀኒነ ዘህልው እምቅድመ ዓለም። ብዕል ህልው። ንርአይ ለእመ ነገሩ ህልው። ህልወ ቃለ። አማን ህልወ እብለክሙ ፡-(ጥበ፪ ፡-፲፯። ዲድ ፡-፴፮። ዮሴፍ። ምሳ፳፪ ፡-፳፩። ዮሐ፲፮ ፡-፯)።
ህርብድና፤ መቀማጠል፤ ቅምጥልነት፤ የቅንጦት ሥራ። ወለእመ ኮንከ ዘመነንካሁ ለህርብድና ጉዳይ እምእለ ይንዕውዎ ፡-(ማር ፡-ይሥ፪ ፡-፲፪)።
ህቦ ፡-ወጨፎ እንዳሸዋና እንደ ጠጠር ያለ የዝናብ ቅንጣት፤ ጠል ጤዛ ጠፈጠፍ፤ ከዝናም በኋላ በሣር በቅጠል ላይ የሚታቈር የሚንቈረዘዝ፤ ሕንባበ ማዶ። ፡-(ግጥም) የተንቈረዘዘው ደምኸ እንደ ጤዛ፤ የስብስቴ ግንቡል ጊዮርጊስ ወሬዛ። እንዘ ይትኀደግ ህቦ። እምነቅዐ ቅዳሴከ እርወይ ወእሰቀይ ህቦ ፡-(ዘፀ፲፮ ፡-፲፫። ደራሲ)።
ህኩክ ፡-(ካን ካት ክክት) ህዉክ፤ ወጪ ወራጅ፤ ወላዋይ። ኅሲና ህክክት ፡-(ፊልክ ፡-፶፬)።
ህዉክ ፤ (ካን ካት ውክት) ፤ የታወከ ሁከታም ፤ ሁከተኛ ፤ ርጋታ ጸጥታ የሌለው። ዘክልኤ ልቡ ህዉክ ውአቱ
በኵሉ ፍኖቱ። ህዉካን ወጽሩዓን እለ አልቦሙ ምግባረ
ሠናይ (ያዕ፩ ፡ ፰። ቀሌ)።
ህየ [1]፡-የቦታ ዐጸፋ፤ በዚያ ከዚያ ወደዚያ፤ ሩቅን ያሳያል፤ እንደ ከሃ ነው። ተከለ ገነተ ወሤሞ ህየ። ህየ ይሠየማ ወህየ ይትዐቀባ ነፍሳቲሆሙ ለጻድቃን። ቦ ዘይወፅእ እምሥራቅ ወየሐውር ለምዕራብ ከመ ይስቂ በህየ። ተንሥእ ወፃእ ሐቅለ ወበህየ እንግረከ ፡-(ዘፍ፪ ፡-፰። ቅዳ ግሩ። አት። ሕዝ፫ ፡-፲፱)።
[2]:-በዚያ ከዚያ፤–ሀይይ ሀየ፤ ሀየየ።
(ጥ) ህየት ፡-ቸል ማለት፤ ቸልታ ስንፍና። እምህየት ወእምፅርዐት ፡-(ሊጦን)።
ህየንተ ፡-ስለ ፈንታ፤–ሀየየ ሀየ።
ህየንተ ፤ (ህየ እንተ) ፤ ዐቢይና ደቂቅ አገባብ። ህየና እንተ ተጋጥሞ አንድ
ኅርመት ኹኗል ፤ እ ስለ ተጐረደ
መጋጠሚያው አያስታውቅም ፤ ይህን የመሰለ ብዙ አለ። ስለ በ
ፈንታ እንደ ይኾናል ፤
ስለና በ ፈንታ አንድ ወገን ናቸው
፤ ምስጢሩ እንደ ፍዳ ነው ፤ ለውጥ ሤጥ ቤዛ ካሳ ዕዳ
ብድር ያሳያል። በአንቀጽ ሲገባ ዘን
በር ከፋች ያደርጋል ፤ አንዳንድ ጊዜም
ብቻውን ይገባል። ምንተ ተዐስዮሙ ህየንተ ዘገብሩ። ህየንተ ዘትረድኦ አቅበጽካሁ። ህየንተ ተቀንዩ። ህየንተ ጻመወ (ሢራ፯ ፡ ፳፰። ቀሌ። ኵፋ ፡ ፵፰። ስንክ ፡ ጥቅ፬)። በዘርና
በስም ሲገባ
፤ ፈደዩኒ እኪተ ህየንተ
ሠናይት። ህየንተ አበውኪ ተወልዱ ለኪ ደቂቅ። ተቀንየ ያዕቆብ ህየንተ
ራሔል ይላል። እንደ ሲኾን ፤ ህየንተ
ቈፅለ ዕፅ ከማሁ አነ። አሕመልምል ሊተ ነፍስየ ህየንተ
ዕፅ ትክልት ማእከለ ገነት ይላል
(አርጋ)።
ህየንቴሁ ሃ ብሎ ሲዘረዝር ፤ ስለ ርሱ
ፈንታ ፤ በርሱ ፈንታ ፤
እንደ ርሱ ያሰኛል። ሀቦሙ
ህየንቴየ ወህየንቴከ (ማቴ፲፯ ፡ ፳፯)። (ዕር፲፱ ፡ ቍ፷፱)።
ህዩይ ፡-(ያን ያት ይይት) ቸል የተባለ፤ የተናቀ። ቸል ያለ ቸልተኛ፤ ሰነፍ። መንዘህልልሰ ወህዩይ። ፍናዊሆሙ ለህዩያን ፡-(ፊልክ ፶፬። ምሳ፲፫ ፡-፲፭)።
ህዩድ ፡-(ዳን ዳት ይድ) የተቀማ የተነጠቀ፤ ገንዘብ ሰው።
ህዱኣዊ ፡-ዝምተኛ ጸጥተኛ፤ ጭምት። ልብ ህዱአዊ ፡-(ፊልክ ፡-፻፩)።
ህዱእ ፡-(ኣን ኣት ድእት) ዝም ጸጥ ያለ፤ ያረፈ የረጋ፤ ሁከት የሌለው፤ በከመ መንግሥትየ ህዱእ። ህዱኣን ወዕሩፋን። ይኩን ህዱአ አዕይንት። ዘኢኮነ ህዱአ በቃሉ ወበምግባሩ። ከመ በህዱእ ወበጽምው ይኩን ንብረትነ ፡-(አስቴ ፡-፫። መሳ፲፰ ፡-፯። ፈ ፡-መ ፡-፳፮ ፡-፰። ቀሌ። ድጓ)።
ህዳር ፡-በቁሙ፤–ኅዳር።
ህድመት ፡-ህድመት፤ ማንቀላፋት። ክቡድ እንቅልፍ፤ እንደ ሞት ያለ። ወደየ እግዚ ህድመተ ላዕሌሁ ወኖመ። ሞት ውእቱ ህድመት ወንዋም። ከመ ሞት በህድመት ክቡድ። ኢወሀቡ ለአዕይንቲሆሙ ምንተጊ ህድመተ ፡-(ኩፋ ፡-፫። አፈ ፡-ተ፬። አርጋ። ስንክ ፡-ኅዳ፲፯)።
ህድአት ፤ ዝም ጸጥ
ማለት። ዝምታ ጸጥታ ፤ ዕረፍት ርጋታ ፤ ዳታ ቀስታ
ዝግታ ፤
ጭምትነት። ህድአት ወአርምሞ።
መፍቀሬ ህድአት። መፍትው ለነ ንሑር በህድአት። መፍትው
ለአንስት ይትርአያ
በአርኣያ ህድአት።
ፈታሒ ዘአጥረየ ህድአት ወትዕግሥት (ጥበ፲፰ ፡ ፲፬። ዮሴፍ።
አፈ ፡ ተ፴፬። ፈ ፡ መ ፡ ፴፬። ፍ ፡ ነ ፡ ፵፪ ፡ ፪)።
ህጉል ፡-(ላን ላት ጕልት) የታጐለ የተጓጐለ፤ መና የቀረ። የጠፋ ጥፋ ብልሹ፤ ከንቱ ከቦታው የታጣ፤ የኰበለለ። ሕዝብ ህጕላነ ምክር። ከመ ኢይኩን ህጉለ ዕሴትከ። ዘይትአመን በብዕሉ ህጉል። መድኀኒሆሙ ለህጉላን። ህጉላነ ሚጥ ፡-(ዘዳ፴፪ ፡-፳፰። ሢራ፰ ፡-፲፱። ሲኖዶ። ዮዲ፱ ፡-፲፩። ኪዳ)።
ህጕለት ፡-መታጐል፤ መቅረት። መጥፋት አጠፋፍ፤ ጥፋት ፡-(ሔኖ፰ ፡-፬። ፳፪ ፡-፲፪)። ህጕለተ ነፍስ ፡-(ሲኖዶ)።
ህጕሬ ፡-ቀይ ቀለም፤–ሕጕሬ።
ህግሩት ፡-የተጋ ትጉ፤ ዐሳቢ ተቈርቋሪ ፡-(አርጋ)።
ህግርትና ፡-ትጋት ሐሳብ፤ ትጉህነእት ዐሳቢነት ፡-(መጽ ፡-ምስ)።
ሆሄ [1]፡-(ሆይ ሄ) ስመ ፊደል መልከአ ፊደል፤ ሀ። ሆይ የግእዝ፤ ሄ የዕብራይስጥ ነው።
[2]፡-ሆሄ፤ ፡-(ዐረ ሁወ ሄ) ውእቱ ሄ ማለት ነው። የኦሪትን ክፍልና ብሔር፤ ከዘፍ እስከ ዘዳ በፊደል ቍጥር ሲቈጥር፤ ወለመጻሕፍተ ኦሪትኒ ፡-(ትእምርታቲሆሙ) በክልኤቱ ፊደላት እሙንቱ፤ ወፊደለ ትእምርተ ኦሪት ቀዳማዊ ትአ፤ ወዳግማዊ ትቤ፤ ወሣልስ ትጋ፤ ወራብዕ ትዳ፤ ወኃምስ ትሄ ካለ በኋላ፤ ውእቱ ሄ እንደ ማለት ወሆሄ ኍልቈ መጻሕፍት ይላል ፡-(ፍ ፡-ነ ፡-መቅ)። ይህም ሄ ፭ኛ ፡-ፊደል ነውና ብቻውን ያ፭ቱ መጻሕፍት ቍጥር ነው ያሰኛል። አይሁድም ፭ቱን መጻሕፍት በዝርዝር ሖማሽ፤ በአኃዝ ሄ ይሏቸዋል፤ ፭ ማለት ነው።
ሆህያት ፡-ፊደሎች፤ የፊደል ስሞችና መልኮች፤ ከሀ እስከ ሆ ወይም እስከ ፐ ያሉት መላው ባንድነት። ፊደላተ ዔቦር በኵራቸውና መክብባቸው አሌፍ ስለ ኾነ በመክብባቸው ስም አሌፋት ተብለው እንዲጠሩ፤ ፊደላተ ግእዝም ከሰላማ ወዲህ መክብባቸው ሆሄ ፡-(ሆይ ሄ) ስለ ኾነ በሆሄ ሆህያት ይባላሉ። ቃሉ የብዙ ሲኾን ላንድም ለብዙም ይነገራል፤ ላንድ ሲነገር ሰባትነቱን ፥ ለብዙ ሲነገር መላዉን ያሳያል። ሆህያተ ፊደል እስመ ሆህያተ ቤት ወዋዌ አሐዱ ውእቱ። በከመ ሆህያተ አልፋ ትከውን ኀበ ኵሎሙ ሆህያት። ወለለ ማኅደር ስምዮሙ በሆህያተ ጽርእ እምአልፋ ወቤጣ ወጋማ፤ አ በ ገ ፡-(አፈ ፡-ድ፰ ፡-፱። ሥር ፡-ጳኵ) ወይቤ ጠቢብ ቀሪጦን፤ እስመ ሴት ቀዲሙ ዘከሠተ ሆህያተ ጽሕፈት ወአዖቀ ልሳነ ዕብራዊ ፡-(ጊ ፡-ወ ፡-ሐ ፡-ገ፮)።
ሆሙ ፡-(ሁ) የሩቅ ወንደች ዝርዝር ጠቃሽ። የሁን አፈታት እይ።
ሆሜር ፡-መስፈሪያ፤–ሖሜር።
ሆሳዕና ፡-(ዕብ ሆሺዓህ–ናእ) አንቀጽና ጥሬ፤ አድኅነነአ፤ አድነና፤ አድነንኮ፤ እባክኸ አድነን፤ የአን ፍች ተመልከት ፡-(ማር፲፩ ፡-፲። ዮሐ፲፪ ፡-፲፫)።
፡-መድኀኒትነት፤ መድኀኒት መኾን፤ ወይም መባል። ሆሳዕና ለወልደ ዳዊት። እምሆሳዕናሁ አርአየ ተኣምረ ወመንክረ ፡-(ማቴ፳፩ ፡-፬። ቅዳ ፡-ጎር)።
፡-የበዓል ስም፤ የሰሌን በዓል፤ ሰሌን ይዘው እያመሰግኑ የሚያውዱበት፤ ለብሉዩ የመጸለት ፯ኛ ቀን፤ ለሐዲሱ ግን ከትንሣኤ በፊት ያለ እሑድ። ፡-(የዶሮች ዘፈን) በሆሳዕና ተሰበሰብና፤ በሳምንቱ አለብነ ሞቱ። ዋዜማ ዘሆሳዕና። በሳኒታ ሆሳዕና በሰኑይ ዕለት ፡-(ድጓ። ዲድ ፡-፳፱)።
፡-ሰሌን የሰሌን ቅጠል፤ ቈጽለ ዘይት፤ ባርሰነት ኵሓ፤ የመሰለው ኹሉ፤ የሆሳዕና ለት የሚያዝ። ዘይቶን ወሆሳዕና። ልብሱ እምልሕጸ ሆሳዕና ወቈጽሉ፤ ሰሌን ፡-(ስንክ ፡-መስ፫)።
ሆሴዕ ፡-(ዕብ ሆሼዕ) የሰው ስም፤ ነቢይ ንጉሥ። አድኀነ ባልሐ፤ ረድአ አውፅአ እመሥገርት ማለት ነው ፡-(ሆሴ፩ ፡-፩። ፬ነገ ፡-፲፭ ፡-፴)።
ሆባይ ፡-(ያት፤ አህቡይ) አንጨት አሞራ፤ ሳቢሳ ጭላት፤ ጥንብ ፈላጊ ፡-(ዘሌ፩ ፡-፲፬። ዘዳ፲፬ ፡-፲፫። ኢዮ፴፱ ፡-፳፮። ሔኖ፹፱ ፡-፲። ፺ ፡-፪ ፡-፬ ፡-፲፩ ፡-፲፫)። ስምንቱ አስተጋባኢ ነው፤ ለሚከንፍና ለሚረብ ለሚያንዣብብ ኹሉ ይኾናል።
፡-(ዕብ ቆፍ። ሱር ቁፋ። ዐረ ቂርድ) ዝንጀሮ ጨላዳ፤ በብዙ ወገን ሰው የሚመስል፤ ነጨና ጥቍሬ ፪ ዐይነት ያለው። በአምሳለ ሆባይ፤ ሆባያት አጽዐቅዎሙ። ወይጠለ አስገድከ ወሆባየ አክነስከ ብፁዕ አንተ አባ ዮሐኒ። ወአህቡየ ፡-(ገድ ፡-ተክ። መዋሥ። ፪ዜና ፡-፱ ፡-፳፩)።
፡-(ዐማርኛ) በቁሙ፤ ሆ ባይ፤ ሆ አሆ የሚል ጨፋሪ፤ እንደ ዝንጀሮ የሚያወካ።
ሆን ፡-(ሁ ሆሙ) የሩቅ ሴቶች ዝርዝር ጠቃሽ።
ሆይ ፡-(ዐማራ ወዕብራ) በቁሙ፤ የጥሪ ቃል በቅርብ ላለ ሰሚ፤ አቤቱ ቶ፤ ንጉሥ ሆይ። ፍችው በጭራሽ እንደ ኦ ነውና፤ ኦንና ኦኦን ተመልከት።
ሆይ ሀውይ ፡-(ዕብ ሆዌ፤ ውስጠ ዘ) ስመ ፊደል ኃምስ ሀ። ሀላዊ ህልው ዘሀሎ፤ ወይም ከዋኒ ክዉን ዘኮነ ማለት ነው፤ ሀለወና ኮነ በዕብራይስጥ አንድ ወገን ናቸው፤ ሀያህ ይህዬህ ብሎ ሀለወ ይሄሉ፤ ኮነ ይከውን ያሰኛልና ሆይ ሀውይ አህያ ይሆዋ ከዚህ የወጣ ነው።
No comments:
Post a Comment